1“ነገር ግን፥ ኢዮብ ሆይ፥ ንግግሬን እንድትሰማ፥ ቃሌንም ሁሉ እንድታደምጥ እለምንሃለሁ።
2እነሆ፥ አፌን ከፍቻለሁ፥ አንደበቴም በትናጋዬ ተናግሮአል።
3ቃሌ የልቤን ቅንነት ያወጣል፤ ከንፈሮቼም የሚያውቁትን በቅንነት ይናገራሉ።
4የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ።
5ይቻልህ እንደ ሆነ መልስልኝ፤ ቃልህንም አዘጋጅተህ በፊቴ ቁም።
6እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ እኔ ደግሞ ከጭቃ የተፈጠርሁ ነኝ።
7እነሆ፥ ግርማዬ አታስፈራህም፡ እጄም አትከብድብህም።
8“በጆሮዬ ተናግረሃል። የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፥ እንዲህም ብለሃል፦
9‘እኔ ያለ መተላለፍ ንጹሕ ነኝ፤ ያለ ነውር ነኝ፥ ኃጢአትም የለብኝም፤
10እነሆ፥ ምክንያት አግኝቶብኛል፥ እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል፤
11እግሬን በግንድ አጣበቀ፥ መንገዴንም ሁሉ ተመለከተ።’
12“እነሆ፥ አንተ በዚህ ጻድቅ አይደለህም፤ እግዚአብሔር ከሰው ይበልጣል ብዬ እመልስልሃለሁ።
13አንተ፦ ‘ለቃሌ ሁሉ አይመልስልኝም፡’ ብለህ፥ ስለ ምን ከእርሱ ጋር ትከራከራለህ?
14እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።
15በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥
16በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥
17ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ፡ ከሰውም ትዕቢትን ይሰውር ዘንድ፤
18ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል።
19ደግሞ በአልጋ ላይ በደዌ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱንም ሁሉ ያደነዝዛል።
20ሕይወቱም እንጀራን፥ ነፍሱም ጣፋጭ መብልን ትጠላለች።
21ሥጋው እስከማይታይ ድረስ ይሰለስላል፤ ተሸፍኖ የነበረውም አጥንት ይገለጣል።
22ነፍሱ ወደ ጕድጓዱ፥ ሕይወቱም ወደሚገድሉአት ቀርባለች።
23“የቀናውን መንገድ ለሰው ያስታውቀው ዘንድ፥ ከሺህ አንድ ሆኖ የሚተረጕም መልአክ ቢገኝለት፥
24እየራራለት፦ ‘ቤዛ አግኝቻለሁና፡ ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው፡’ ቢለው፥
25ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል።
26ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ እርሱም ሞገስን ይሰጠዋል፡ ፊቱንም በደስታ ያሳየዋል፤ ለሰውም ጽድቁን ይመልስለታል።
27እርሱም በሰው ፊት እየዘመረ፦ ‘እኔ በድያለሁ፥ ቅኑንም አጣምሜአለሁ፤ የሚገባኝንም ብድራት አልተቀበልሁም፤
28ነፍሴ ወደ ጕድጓድ እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች፡’ ይላል።
29“እግዚአብሔር ይህን ሁሉ፡ ሁለት ጊዜና ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፤
30ይህም ነፍሱን ከጕድጓድ ይመልስ ዘንድ፥ በሕያዋንም ብርሃን ያበራ ዘንድ ነው።
31“ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ።
32ነገር ቢኖርህ መልስልኝ፤ ትጸድቅ ዘንድ እወድዳለሁና ተናገር።
33ያለዚያም እኔን ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።”