1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2“ዛሬም ደግሞ የኅዘን እንጕርጕሮዬ ገና መራራ ነው፤ እጁ በልቅሶ ጩኸቴ ላይ ከብዳለች።
3እርሱን ወዴት እንዳገኘው ምነው ባወቅሁ! ወደ ተቀመጠበትስ ስፍራ ምነው በደረስሁ!
4በፊቱ ሙግቴን አዘጋጅ ነበር፥ አፌንም በማስረጃ እሞላው ነበር።
5የሚመልስልኝም ቃል ምን እንደ ሆነ አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም አስተውል ነበር።
6በኃይሉ ብዛት ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን? እንኳን! ያደምጠኝ ነበር።
7ቅን ሰው ከእርሱ ጋር በዚያ ይከራከር ነበር፤ እኔም ከፈራጄ ለዘላለም እድን ነበር።
8“እነሆ፥ ወደ ፊት እሄዳለሁ፥ እርሱም የለም፤ ወደ ኋላም እሄዳለሁ፥ እኔም አላስተውለውም፤
9ወደሚሠራበት ወደ ግራ ብሄድ አልመለከተውም፤ በቀኜም ይሰወራል፥ አላየውምም፤
10የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ።
11እግሬ ወደ እርምጃው ተጣብቆአል፤ መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ፈቀቅም አላልሁም።
12ከከንፈሩ ትእዛዝ አልተመለስሁም፤ የአፉን ቃል በልቤ ሰውሬአለሁ።
13“እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው? ነፍሱም የወደደችውን ያደርጋል።
14በእኔ ላይ የተወሰነውን ይፈጽማል፤ እንደዚህም ያለ ብዙ ነገር በእርሱ ዘንድ አለ።
15ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፤ ባሰብሁም ጊዜ ከእርሱ ፈራሁ።
16እግዚአብሔር ልቤን አባብቶታልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል።
17ከጨለማው የተነሣ፥ ድቅድቁም ጨለማ ፊቴን ከመክደኑ የተነሣ አልደነገጥሁም።