የዮሐንስ ወንጌል 6

AMHEVGአማርኛ71 ጥቅሶች8:13 አዳምጥ
አዳምጥ 8:13 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው።

2በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።

3ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ።

4የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር።

5ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን፦ “እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?” አለው።

6ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ።

7ፊልጶስ፦ “እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኳ እንዲቀበሉ የሁለት መቶ ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም፡” ብሎ መለሰለት።

8ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ፦

9“አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል?” አለው።

10ኢየሱስም፦ “ሰዎቹን እንዲቀመጡ አድርጉ፡” አለ። በዚያም ስፍራ ብዙ ሣር ነበረበት። ወንዶችም ተቀመጡ፡ ቍጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር።

11ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ፥ አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡአቸው እንዲሁም ከዓሣው በፈለጉት መጠን።

12ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፦ “አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ፡” አላቸው።

13ሰለዚህ አከማቹ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።

14ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ፦ “ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው፡” አሉ።

15በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ።

16በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ፥

17በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር። አሁንም ጨልሞ ነበር፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር፤

18ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ።

19ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ።

20እርሱ ግን፦ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።

21ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች።

22በነገው በባሕር ማዶ ቆመው የነበሩ ሕዝቡ ከአንዲት ጀልባ በቀር በዚያ ሌላ ጀልባ እንዳልነበረች፥ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው እንደ ሄዱ እንጂ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ እንዳልገባ አዩ፤

23ዳሩ ግን ሌሎች ጀልባዎች ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በሉበት ስፍራ አጠገብ ከጥብርያዶስ መጡ።

24ሕዝቡም ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ እንዳልነበሩ ባዩ ጊዜ፥ ራሳቸው በጀልባዎቹ ገብተው ኢየሱስን እየፈለጉ ወደ ቅፍርናሆም መጡ።

25በባሕር ማዶም ሲያገኙት፦ “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት።

26ኢየሱስም መልሶ፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።

27ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።”

28እንግዲህ፦ “የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ?” አሉት።

29ኢየሱስ መልሶ፦ “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው፡” አላቸው።

30እንግዲህ፦ “እንኪያ አይተን እንድናምንህ አንተ ምን ምልክት ታደርጋለህ? ምንስ ትሠራለህ?

31‘ይበሉ ዘንድ ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ አባቶቻችን በምድረ በዳ መና በሉ።” አሉት።

32ኢየሱስም አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤

33የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።”

34ስለዚህ፦ “ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን፡” አሉት።

35ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፡ በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።

36ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ።

37አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤

38ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።

39ከሰጠኝም ሁሉ አንድን ስንኳ እንዳላጠፋ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣው እንጂ የላከኝ የአብ ፈቃድ ይህ ነው።

40ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”

41እንግዲህ አይሁድ፦ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና።

42“አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ፦ ከሰማይ ወርጃለሁ፡ እንዴት ይላል?” አሉ።

43ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ “እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ።

44የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

45ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።

46አብን ያየ ማንም የለም፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ በቀር፥ እርሱ አብን አይቶአል።

47እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።

48የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ።

49አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤

50ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው።

51ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው።”

52እንግዲህ አይሁድ፦ “ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል?” ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ።

53ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም።

54ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

55ሥጋዬ እውነተኛ መብል፡ ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና።

56ሥጋዬን የሚበላ፣ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል፤ እኔም በእርሱ እኖራለሁ።

57ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።

58ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል።”

59በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ።

60ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ፦ “ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል?” አሉ።

61ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው፦ “ይህ ያሰናክላችኋልን?

62እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?

63ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።

64ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ።” ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።

65ደግሞ አለ፦ “ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም።”

66ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።

67ኢየሱስም ለአሥራ ሁለቱ፦ “እናንተ ደግሞ ልትሄዱ ትወዳላችሁን?” አለ።

68ስምዖን ጴጥሮስ፦ “ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤

69እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል አውቀናልም፡” ብሎ መለሰለት።

70ኢየሱስም፦ “እኔ እናንተን አሥራ ሁለታችሁን የመረጥኋችሁ አይደለምን? ከእናንተም አንዱ ዲያብሎስ ነው፡” ብሎ መለሰላቸው።

71ስለ ስምዖንም ልጅ ስለ አስቆሮቱ ይሁዳ ተናገረ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነ እርሱ አሳልፎ ይሰጠው ዘንድ አለውና።

ማብራሪያ

ዮሐንስ 6:1-14 ዮሐንስ ብዙዎችን ስለመመገቡ ተአምር ይተርካል፤ ይህም ለሚከተለው ንግግር ማጣቀሻ እንዲሆንለት ነው። ይህ ተአምር በሕዝቡ ላይ ያሳደረውን ውጤት አስተውል። ተራዎቹ አይሁድም ቢሆኑ መሲሑ ወደ ዓለም እንደሚመጣና ታላቅ ነቢይም እንደሚሆን ይጠባበቁ ነበር። ፈሪሳውያን ሕጉን ስለማያውቁ ይንቋቸው ነበር፤ ነገር ግን የሕጉ ፍጻሜ የሆነውን እርሱን እነርሱ ከሁሉም በላይ ያውቁ ነበር። ሆኖም ግን ሰዎች ክርስቶስን ያን ነቢይ እንደሆነ ቢያውቁም እንኳ፣ አሁንም መስሚያቸውን ሊደፍኑ ይችላሉ።

፮፥፲፭-፳፩ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ግዴታቸውን እየፈጸሙ ሳሉ፣ ክርስቶስም ስለ እነርሱ ይጸልይ ነበርና፤ ሆኖም በመከራ ውስጥ ነበሩ። በክርስቶስ የሆኑትም እንኳ በዚህ ዘመን አደጋዎችና መከራዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። ደመናና ጨለማ የብርሃንና የቀን ልጆችን ብዙ ጊዜ ይከባል። ኢየሱስ በባሕር ላይ ሲመላለስ ያያሉ። የመጽናናትና የመዳን መቅረብ እንኳን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት የፍርሃት ምክንያት ይሆናል። ኃጢአተኞችን 'የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ' ከሚለው ቃል ይልቅ ሊያሳምን የሚችል ኃይለኛ ነገር የለም፤ ቅዱሳንን ደግሞ 'የምትወደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ' ከሚለው ቃል ይልቅ የሚያጽናና የለም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ከተቀበልን፣ ሌሊቱ የጨለመ ቢሆንም፣ ነፋሱም ብርቱ ቢሆንም፣ ብዙም ሳይቆይ ወደ ወደብ እንደርሳለንና ራሳችንን ማጽናናት እንችላለን።

6:22-27 እዚያ እንዴት እንደደረሰ ለጥያቄያቸው ከመመለስ ይልቅ፣ ኢየሱስ ጠያቂነታቸውን ነቀፈ። መዳንን በተሾሙት መንገዶች በመፈለግ ረገድ ሙሉ ትጋት መደረግ አለበት፤ ሆኖም ግን፣ የሰው ልጅ ስጦታ ሆኖ ብቻ መፈለግ ያለበት ነው። አብ እርሱን አትሞታል፣ አምላክ መሆኑንም አረጋግጦታል። አብ የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በኃይል አውጇል።

6:28-35 በክርስቶስ የማያቋርጥ እምነት መለማመድ፣ መዳንን እንደምንሻ ኃጢአተኞች ከእኛ ከሚጠበቀው ታዛዥነት እጅግ አስፈላጊውና አስቸጋሪው ክፍል ነው። በእርሱ ጸጋ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ በእምነት ሕይወት እንድንኖር ስንችል፣ ቅዱስ ባሕርያት ይከተላሉ፣ እናም ተቀባይነት ያላቸው አገልግሎቶች ሊከናወኑ ይችላሉ። እግዚአብሔር፣ እርሱም አባቱ፣ ለአባቶቻቸው የተፈጥሮ ሕይወታቸውን ለመደገፍ ከሰማይ ምግብን የሰጣቸው፣ አሁን ግን ለነፍሳቸው መዳን እውነተኛውን እንጀራ ሰጣቸው። ወደ ኢየሱስ መምጣት እና በእርሱም ማመን ተመሳሳይ እንደሆነ ያመለክታሉ። ክርስቶስ እርሱ እውነተኛው እንጀራ እንደሆነ ያሳያል፤ እንጀራ ለሥጋ እንደሆነ እርሱም ለነፍስ ነው፣ መንፈሳዊውን ሕይወት ይመግባል እንዲሁም ይደግፋል። እርሱ የእግዚአብሔር እንጀራ ነው። አብ የሚሰጠው፣ የነፍሳችን ምግብ እንዲሆን ያደረገው እንጀራ። እንጀራ የሚመግብው ሕያው አካል በኃይሉ ብቻ ነው፤ ክርስቶስ ግን እርሱ ራሱ ሕያው እንጀራ ነው፣ በገዛ ኃይሉም ይመግበል። የተሰቀለው የክርስቶስ ትምህርት አሁንም ለሚያምን ሰው እንደ ቀድሞው ሁሉ የሚያበረታና የሚያጽናና ነው። እርሱ ከሰማይ የወረደው እንጀራ ነው። ይህም የክርስቶስን አምላክነትና ሥልጣኑን እንዲሁም በእርሱ አማካይነት ወደ እኛ የሚፈሰውን መልካም ነገር ሁሉ መለኮታዊ ምንጭ ያመለክታል። በማስተዋልና በቅንዓት፣ "ጌታ ሆይ፣ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን" እንል ዘንድ ይሁን።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6