የዮሐንስ ወንጌል 16

AMHNIVአማርኛ33 ጥቅሶች5:04 አዳምጥ
አዳምጥ 5:04 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1“ይህን ሁሉ የነገርኋችሁ እንዳትሰናከሉ ነው።

2ከምኵራብ ያስወጧችኋል፤ እንዲያውም የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዳገለገለ የሚቈጥርበት ጊዜ ይመጣል።

3ይህን ሁሉ የሚያደርጉባችሁ፣ አብን ወይም እኔን ስላላወቁ ነው።

4አስቀድሜ ይህን የነገርኋችሁ ጊዜው ሲደርስ እንድታስታውሱ ነው፤ ከእናንተ ጋር ስለ ነበርሁ፣ ይህን ከመጀመሪያው አልነገርኋችሁም።

5“እንግዲህ ወደ ላከኝ እሄዳለሁ፤ ይሁን እንጂ ከእናንተ፣ ‘የምትሄደው የት ነው?’ ብሎ የሚጠይቀኝ የለም።

6ይህን በመናገሬም ልባችሁ በሐዘን ተሞልቶአል፤

7ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤

8በሚመጣበትም ጊዜ ዓለምን ስለ ኀጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ይወቅሳል።

9ስለ ኀጢአት ሲባል፣ ሰዎች በእኔ ስለማያምኑ ነው፤

10ስለ ጽድቅ፣ ወደ አብ ስለምሄድና ከእንግዲህ ስለማታዩኝ ነው፤

11ስለ ፍርድም፣ የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው።

12“ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም።

13የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤

14የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል።

15የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።”

16“ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ።”

17ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ፣ “ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም፣ ‘ወደ አብ ስለምሄድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ፤

18“‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም” እያሉ ይጠያየቁ ነበር።

19ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ?

20እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።

21ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች፤

22ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።

23በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።

24እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል።

25“እስከ አሁን የነገርኋችሁ በምሳሌ ቢሆንም እንኳ፣ ከእንግዲህ ግን ስለ አብ በምሳሌ ሳይሆን በግልጽ የምናገርበት ጊዜ ይመጣል።

26በዚያ ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ ይህም በእናንተ ፈንታ አብን እለምናለሁ ማለቴ አይደለም፤

27ስለ ወደዳችሁኝና ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል።

28ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ አሁን ግን ዓለምን ትቼ ወደ አብ እሄዳለሁ።”

29ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አሉ፤ “አሁንም እኮ ያለ ምሳሌ በግልጽ እየተናገርህ ነው።

30አሁን ሁሉን ነገር እንደምታውቅና ማንም ሊጠይቅህ እንደማያስፈልግ ተረድተናል፤ ይህም ከእግዚአብሔር እንደ ወጣህ እንድናምን አድርጎናል።”

31ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንስ አመናችሁ ማለት ነው?

32እነሆ፤ ሁላችሁም በየፊናችሁ የምትበታተኑበት ጊዜ ይመጣል፤ ያም ጊዜ አሁን ነው። እኔንም ብቻዬን ትተዉኛላችሁ፤ ይሁን እንጂ አባቴ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም።

33“በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”

ማብራሪያ

16:1-6 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ስለሚመጣው መከራ አስቀድሞ በማስጠንቀቅ፣ ፍርሃቱ ድንገተኛ እንዳይሆንባቸው አቀደ። በእውነት የእግዚአብሔር አገልግሎት ጠላቶች የሆኑ ሰዎች ለእርሱ ቅንዓት እንዳላቸው ማስመሰል ይቻላቸዋል። ይህ ግን የአሳዳጆችን ኃጢአት አያቀልም፤ በክፋት ሥራዎች ላይ የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት ክፋት በፍጹም አይለወጥም። ኢየሱስ በመከራው ውስጥ እንደሆነ ሁሉ፣ ተከታዮቹም በመከራቸው ውስጥ የቅዱሳት መጻሕፍትን ፍጻሜ ሊመለከቱ ይገባል። አስቀድሞ ያልነገራቸው እርሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ ሊያስተምራቸው፣ ሊመራቸውና ሊያጽናናቸው ስለነበረ ነው፤ ያኔ የመንፈስ ቅዱስን መገኘት ተስፋ አያስፈልጋቸውም ነበር። መከራዎች ከየት እንደሚመጡ መጠየቅ ያስደነግጠናል፤ ወዴት እንደሚሄዱ መጠየቅ ግን ያረካናል፤ ምክንያቱም ለበጎ እንደሆነ እናውቃለንና። የኀዘንተኞች ክርስቲያኖች የጋራ ስህተትና ሞኝነት የደመናውን ጨለማ ጎን ብቻ ማየት፣ እንዲሁም የደስታንና የሐሤትን ድምፅ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ነው። የደቀ መዛሙርትን ልብ በኀዘን የሞላው ለዚህ ጊዜያዊ ሕይወት የነበራቸው ከመጠን ያለፈ ፍቅር ነበር። በእግዚአብሔር ያለንን ደስታ ከዓለም ፍቅርና ከእርሱ በሚመጣው የዓለም ኀዘን የበለጠ የሚከለክለው የለም።

16:7-15 የክርስቶስ መሄድ የአጽናኝ መንፈስ ለመምጣት አስፈላጊ ነበር። መንፈስ ቅዱስን መላክ የክርስቶስ ሞት ፍሬ ነበር፤ ይህም እርሱ መሄዱ ነበር። ሥጋዊ መገኘቱ በአንድ ጊዜ በአንድ ስፍራ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን መንፈሱ በየቦታው፣ በሁሉ ስፍራ፣ በሁሉ ጊዜ፣ በስሙ ሁለት ወይም ሦስት በተሰበሰቡበት ሁሉ አለ።

እዚህ የመንፈስ ቅዱስን ተግባር እንመልከት፤ በመጀመሪያ መገሰጽ ወይም ማሳመን ነው። የማሳመን ሥራ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፤ እርሱ ሙሉ በሙሉ ሊያደርገው ይችላል፣ ከእርሱ በቀር ማንም የለም። መንፈስ ቅዱስ የሚከተለው መንገድ በመጀመሪያ ማሳመን ከዚያም ማጽናናት ነው። መንፈስ ቅዱስ ዓለምን ስለ ኃጢአት ያሳምናል፤ ዝም ብሎ ስለእርሱ አይነግራቸውም። መንፈስ ቅዱስ ዓለምን የኃጢአት መኖርን፤ የኃጢአትን ጥፋተኝነትን፤ የኃጢአትን ሞኝነትን፤ የኃጢአትን ርኩሰት (በእርሱም ለእግዚአብሔር የተጠላን መሆናችንን)፤ የኃጢአትን ምንጭ (የረከሰ ተፈጥሮአችንን)፤ በመጨረሻም የኃጢአትን ፍሬ፣ ማለትም መጨረሻው ሞት መሆኑን ያሳምናል።

መንፈስ ቅዱስ ዓለም ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ጥፋተኛ መሆኑን ያረጋግጣል። ዓለምን ስለ ጽድቅ ያሳምናል፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ ጻድቁ ክርስቶስ መሆኑን። ደግሞም ስለ ክርስቶስ ጽድቅ፣ ለእኛ ለጽድቅና ለመዳን የተሰጠንን። እንዴት እንደሚያገኙትና በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆነው እንዴት ተቀባይነት እንደሚያገኙ ያሳያቸዋል። የክርስቶስ ዕርገት ቤዛው ተቀባይነት ማግኘቱንና ጽድቅ መጠናቀቁን ያረጋግጣል፤ ይህም አማኞች የሚጸድቁበት ነው። ስለ ፍርድ ደግሞ፣ የዚህ ዓለም ገዢ የተፈረደበት ስለሆነ። ሁሉንም ክፋት ያመጣው እርሱ ኃይሉ ሲሰበር፣ ሁሉ መልካም ይሆናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6