የዮሐንስ ወንጌል 12

AMHNIVአማርኛ50 ጥቅሶች7:41 አዳምጥ
አዳምጥ 7:41 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የፋሲካ በዓል ስድስት ቀን ሲቀረው ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሣው አልዓዛር ወደሚኖርበት፣ ወደ ቢታንያ መጣ።

2በዚያም ለኢየሱስ ሲባል ራት ተዘጋጀ። ማርታ ስታገለግል፣ አልዓዛር ከእርሱ ጋር በማእድ ከተቀመጡት አንዱ ነበር።

3ማርያምም ዋጋው ውድ የሆነ፣ ግማሽ ሊትር ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በጠጒሯ አበሰች፤ ቤቱንም የሽቱው መዓዛ ሞላው።

4ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ ኋላ አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ግን በመቃወም እንዲህ አለ፤

5“ይህ ሽቱ በሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ገንዘቡ ለድኾች ለምን አልተሰጠም?”

6ይህን የተናገረው የገንዘብ ከረጢት ያዥ በመሆኑ፣ ከሚቀመጠው ለራሱ የሚጠቀም ሌባ ስለ ነበር እንጂ ለድኾች ተቈርቊሮ አልነበረም።

7ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ሽቱ ለቀብሬ ቀን የታሰበ ስለ ሆነ እንድታቈየው ተዋት፤

8ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔን ግን ሁል ጊዜ አታገኙኝም።”

9በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁድ ኢየሱስ በዚያ መኖሩን ዐውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ብለው ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ ከሙታን ያስነሣውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር።

10ስለዚህ የካህናት አለቆች አልዓዛርን ጭምር ለመግደል ተማከሩ፤

11ይህም በእርሱ ምክንያት ብዙ አይሁድ ወደ ኢየሱስ እየሄዱ ያምኑበት ስለ ነበር ነው።

12በማግሥቱም ለበዓሉ የመጣው ብዙ ሕዝብ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ፤

13የዘንባባም ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ሆሣዕና!” “በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው!” “የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው!”

14ኢየሱስም የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤

15“የጽዮን ልጅ ሆይ፤ አትፍሪ፤ እነሆ፤ ንጉሥሽ በአህያ ግልገል ተቀምጦ ይመጣል።”

16ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሁሉ በመጀመሪያ አላስተዋሉም፤ ስለ እርሱ የተጻፉትንና ለእርሱም የተደረጉትን ልብ ያሉት ኢየሱስ ከከበረ በኋላ ነበር።

17አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ ከሙታን ባስነሣበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች መነሣቱን ይመሰክሩ ነበር።

18ብዙ ሰዎችም ይህን ታምራዊ ምልክት ማድረጉን ስለ ሰሙ ሊቀበሉት ወጡ።

19ስለዚህም ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው፣ “እንግዲህ ምን ማድረግ ይቻላል? አያችሁ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።

20ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከወጡት መካከል የግሪክ ሰዎችም ነበሩ።

21እነርሱም በገሊላ ከምትገኘው ከቤተ ሳይዳ ወደ ሆነው ሰው፣ ወደ ፊልጶስ መጥተው፣ “ጌታው፤ እባክህን፣ ኢየሱስን ለማየት እንፈልጋለን” አሉት።

22ፊልጶስም፤ ለእንድርያስ ሊነግረው ሄደ፤ እንድርያስና ፊልጶስም ለኢየሱስ ነገሩት።

23ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓቱ ደርሶአል፤

24እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።

25ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።

26የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔም ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል፤ የሚያገለግለኝንም አባቴ ያከብረዋል።

27“አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚች ሰዓት ታድነኝ? የለም፤ ይሁን የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና።

28አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው።” ከዚያም፣ “አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።

29በዚያ የነበሩት፣ ድምፁን የሰሙት አያሌ ሰዎች፣ “ነጐድጓድ ነው” አሉ፤ ሌሎች ደግሞ፣ “መልአክ ተናገረው” አሉ።

30ኢየሱስም እንዲህ አለ፤ “ይህ ድምፅ የመጣው ስለ እኔ ሳይሆን ስለ እናንተ ነው፤

31ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህም ዓለም ገዥ አሁን ወደ ውጭ ይጣላል።

32እኔ ግን ከምድር ከፍ ከፍ ባልሁ ጊዜ ሰውን ሁሉ ወደ ራሴ እስባለሁ።”

33ይህን የተናገረው በምን ዐይነት ሞት እንደሚሞት ለማመልከት ነበር።

34ሕዝቡም፣ “እኛስ ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕግ ሰምተናል፤ ታዲያ፣ ‘የሰው ልጅ ከፍ ከፍ ማለት አለበት’ እንዴት ትላለህ? ይህስ ‘የሰው ልጅ’ ማን ነው?” አሉት።

35ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ “ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።

36የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በዚህ ብርሃን እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደ ጨረሰ ተለያቸው፤ ተሰወረባቸውም።

37ኢየሱስ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ በፊታቸው ቢያደርግም እንኳ፣ አሁንም አላመኑበትም፤

38ይኸውም ነቢዩ ኢሳይያስ፣ “ጌታ ሆይ፤ ምስክርነታችንን ማን አመነ? የጌታ ክንድስ ለማን ተገለጠ?” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው።

39ስለዚህ ማመን አልቻሉም፤ ይህም ኢሳይያስ በሌላ ቦታ እንዲህ ሲል እንደ ተናገረው ነው፤

40“ዐይናቸውን አሳውሮአል፤ ልባቸውንም አደንድኖአል፤ ስለዚህ በዐይናቸው አያዩም፤ በልባቸውም አያስተውሉም፤ እንዳልፈውሳቸውም አይመለሱም።”

41ኢሳይያስ ይህን ያለው የኢየሱስን ክብር ስላየ ነው፤ ስለ እርሱም ተናገረ።

42ይህም ቢሆን፣ ከአለቆች መካከል እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤ ይሁን እንጂ ፈሪሳውያን ከምኵራብ እንዳያስወጧቸው ስለ ፈሩ ማመናቸውን አይገልጡም ነበር።

43ይህም የሆነው በእግዚአብሔር ከመመስገን ይልቅ በሰው መመስገንን ስለ ወደዱ ነው።

44ከዚያም ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “ማንም በእኔ ቢያምን በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ማመኑ ነው፤

45እኔንም የሚያይ የላከኝን ያያል።

46በእኔ የሚያምን በጨለማ እንዳይኖር ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።

47“ቃሌን ሰምቶ በማይፈጽመው ላይ የምፈርደው እኔ አይደለሁም፤ ዓለምን ላድን እንጂ በዓለም ላይ ልፈርድ አልመጣሁምና።

48በማይቀበለኝና ቃሌን በሚያቃልል ላይ የሚፈርድበት አለ፤ የተናገርሁት ቃል ራሱ በመጨረሻው ቀን ይፈርድበታል፤ ምክንያቱም

49እኔ ከራሴ አልተናገርሁም፤ ነገር ግን የላከኝ አብ ምን እንደምናገርና እንዴት እንደምናገር አዘዘኝ።

50የእርሱ ትእዛዝ ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርስ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህም የምለው ሁሉ አብ እንድናገረው የነገረኝን ብቻ ነው።”

ማብራሪያ

ዮሐንስ 12:1-11

ክርስቶስ ማርታን በብዙ አገልግሎት ከመጠመዷ የተነሳ ስትጨነቅ ቀደም ሲል ነቅፎአት ነበር። ነገር ግን በአንድ አቅጣጫ ከልክ በላይ በመሄዳቸው ምክንያት ሲነቀፉ በንዴት ወደ ሌላኛው ጽንፍ እንደሚሮጡ አንዳንድ ሰዎች እርሷ አገልግሎቷን አላቋረጠችም። ይልቁንም፣ አሁንም እያገለገለች የክርስቶስን የጸጋ ቃላት ትሰማ ነበር። ማርያም የፍቅር ምልክት ለክርስቶስ ሰጠች፤ እርሱም ለእርሷና ለቤተሰቧ የእውነተኛ ፍቅሩን ምልክቶች ሰጥቶ ነበርና። የእግዚአብሔር የተቀባው (ክርስቶስ) የእኛም የተቀባው ሊሆን ይገባል። እግዚአብሔር ከባልንጀሮቹ ይልቅ የደስታን ዘይት በላዩ ላይ ካፈሰሰ፣ እኛም የእኛን እጅግ የላቀ የፍቅራችንን ቅባት በላዩ ላይ እናፍስስ። በይሁዳ ውስጥ አስቀያሚ ኃጢአት በሚያምርና በሚታመን ሰበብ ተሸፍኖአል። በእኛ መንገድ አገልግሎት የማያደርጉ ሰዎች ተቀባይነት ያለው አገልግሎት አያደርጉም ብለን ማሰብ የለብንም። የሚገዛው የገንዘብ ፍቅር የልብ ስርቆት ነው። የክርስቶስ ጸጋ በአምላካዊ ቃላትና ድርጊቶች ላይ ደግ አስተያየቶችን ያኖራል፤ ከጎደለው ነገር መልካሙን ያወጣል፤ ከመልካሙም ደግሞ እጅግ ብዙ ያደርጋል። ዕድሎች በጥሩ ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፤ አጭር የመሆን ዕድል ያላቸው ደግሞ በመጀመሪያ እና በታላቅ ጉልበት መሆን ይኖርባቸዋል። የአልዓዛርን ሕይወት በመግደል የድንቅ ሥራውን ተጨማሪ ውጤት ለማደናቀፍ መመካከር፣ የሰው ልብ በእግዚአብሔር ላይ ካለው ተስፋ የቆረጠ ጠላትነት በስተቀር ሊብራራ የማይችል እንደዚህ ያለ ክፋት፣ ተንኮልና ስንፍና ነው። ጌታ ወደ ሕይወት ያመጣውን ሰው እንዲሞት ወሰኑ። የወንጌል ስኬት ብዙውን ጊዜ ክፉ ሰዎችን እጅግ ያበሳጫል፤ ስለዚህም ሁሉንም ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር ላይ ድል ለማግኘት እንደተስፋፉ አድርገው ይናገራሉ እንዲሁም ይሠራሉ።

12:12-19

የክርስቶስ በድል ወደ ኢየሩሳሌም መግባት በሁሉም ወንጌላውያን ተመዝግቧል። በእግዚአብሔር ቃልም ሆነ በመለኮታዊ አድራጎቱ ውስጥ ያሉ ብዙ ታላላቅ ነገሮች፣ ደቀ መዛሙርት የእግዚአብሔርን ነገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቁ አይገባቸውም ነበር። የክርስቶስ መንግሥት መንፈሳዊ ባሕርይ ትክክለኛ ግንዛቤ፣ ስለ እርሱ የሚናገሩትን ቅዱሳት መጻሕፍትን በስህተት እንዳንጠቀም ይከለክላል።

12:20-26።

በቅዱስ ስርዓቶች ላይ፣ በተለይም በወንጌል ፋሲካ ላይ ስንገኝ፣ የነፍሳችን ታላቅ ምኞት ኢየሱስን ማየት፤ የእኛ አድርገን ማየት፣ ከእርሱ ጋር ህብረትን ማቆየት፣ እና ከእርሱ ጸጋን መቀበል መሆን አለበት። የአህዛብ ጥሪ አዳኙን አከበረ። የስንዴ ቅንጣት ወደ መሬት ካልወደቀች በስተቀር ምንም ፍሬ አያፈራም። እንዲሁ ክርስቶስ ሰው ሳይሆን ብቻውን የሰማይ ክብሩን ሊይዝ ይችል ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6