የዮሐንስ ወንጌል 11

AMHNIVአማርኛ57 ጥቅሶች7:53 አዳምጥ
አዳምጥ 7:53 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በማርያምና በእኅቷ በማርታ መንደር በቢታንያ ይኖር የነበረው አልዓዛር ታሞ ነበር።

2ይህች ወንድሟ አልዓዛር የታመመባት ማርያም፣ በጌታ ላይ ሽቱ አፍስሳ እግሩን በጠጕሯ ያበሰችው ነበረች።

3እኅትማማቾቹም፣ “ጌታ ሆይ፤ የምትወደው ሰው ታሞአል” ብለው መልእክት ላኩበት።

4ኢየሱስ ይህን በሰማ ጊዜ፣ “ይህ ሕመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ለእግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት የሚያደርስ አይደለም” አለ።

5ኢየሱስም ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር።

6ሆኖም አልዓዛር መታመሙን በሰማ ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ቈየ።

7ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፣ “ወደ ይሁዳ እንመለስ” አላቸው።

8እነርሱም፣ “መምህር ሆይ፤ ከጥቂት ጊዜ በፊት አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩህ እየፈለጉህ ነበር፤ እንደ ገና ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት።

9ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ብርሃን አይደለምን? ከዚህ ዓለም ብርሃን የተነሣ ስለሚያይ በቀን የሚመላለስ አይሰናከልም፤

10የሚሰናከለው ግን በሌሊት የሚመላለስ ነው፤ ብርሃን የለውምና።”

11ይህን ከነገራቸው በኋላ፣ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ እኔም ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው።

12ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ ተኝቶ ከሆነስ ይድናል” አሉት።

13ኢየሱስ ይህን የነገራቸው ስለ ሞቱ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እንቅልፍ ስለ መተኛቱ የተናገረ መሰላቸው።

14ስለዚህም በግልጽ እንዲህ አላቸው፤ “አልዓዛር ሞቶአል፤

15ታምኑ ዘንድ፣ በዚያ ባለ መኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ አሁን ግን ወደ እርሱ እንሂድ።”

16ከዚያም ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ለተቀሩት ደቀ መዛሙርት፣ “እኛም ሄደን ከእርሱ ጋር እንሙት” አላቸው።

17ኢየሱስ ሲደርስ አልዓዛር ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት ነበር።

18ቢታንያ ከኢየሩሳሌም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ትርቅ ነበር።

19ብዙዎች አይሁድም ማርታንና ማርያምን ስለ ወንድማቸው ሞት ሊያጽናኗቸው መጥተው ነበር፤

20ማርታ የኢየሱስን መምጣት ሰምታ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ቀርታ ነበር።

21ማርታም ኢየሱስን እንዲህ አለችው፤ “ጌታ ሆይ፤ አንተ በዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር።

22አሁንም ቢሆን የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንደሚሰጥህ ዐውቃለሁ።”

23ኢየሱስም፣ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት።

24ማርታም፣ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው።

25ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤

26በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽን?”

27እርሷም፣ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው።

28ይህን ካለች በኋላ፣ ተመልሳ እኅቷን ማርያምን ለብቻዋ ጠርታ፣ “መምህሩ መጥቷል፤ ይፈልግሻልም” አለቻት።

29ማርያምም ይህን እንደ ሰማች፣ ፈጥና ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች።

30በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ቦታ ነበር እንጂ፣ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር።

31ማርያምን ሲያጽናኑ በቤት ውስጥ የነበሩ አይሁድም፣ ብድግ ብላ መውጣቷን ሲያዩ፣ ወደ መቃብሩ ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሏት።

32ማርያምም ኢየሱስ ወደነበረበት ቦታ ደርሳ እንዳየችው፣ እግሩ ላይ ተደፍታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ፣ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” አለችው።

33ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ፣ ተከትለዋትም የመጡት አይሁድም ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ መንፈሱ በኀዘን ታውኮ፣

34“የት ነው ያኖራችሁት?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ መጥተህ እይ” አሉት።

35ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።

36አይሁድም፣ “እንዴት ይወደው እንደ ነበር አያችሁ” አሉ።

37ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፣ “የዐይነ ስውሩን ዐይን የከፈተ፣ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበር?” አሉ።

38ኢየሱስ ልቡ ዳግመኛ በኀዘን ተነክቶ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም በድንጋይ የተገጠመ ዋሻ ነበር፤

39እርሱም፣ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹም እኅት ማርታ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለ ቈየ ይሸታል” አለችው።

40ኢየሱስም፣ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርሁሽም?” አላት።

41ስለዚህ ድንጋዩን አነሡ። ኢየሱስም ወደ ላይ ተመልክቶ አንዲህ አለ፤ “አባት ሆይ፤ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤

42ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ይህን መናገሬ ግን በዚህ የቆሙ ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ ነው።”

43ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ በታላቅ ድምፅ፣ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” ብሎ ተጣራ።

44የሞተውም ሰው እጅና እግሩ በቀጭን ስስ ጨርቅ እንደ ተጠቀለለ፣ ፊቱም በሻሽ እንደ ተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስም “መግነዙን ፍቱለትና ይሂድ” አላቸው።

45ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፣ ኢየሱስ ያደረገውን ካዩት አይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ።

46አንዳንዶቹ ግን ሄደው ኢየሱስ ያደረገውን ለፈሪሳውያን ተናገሩ፤

47ከዚያም የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን የአይሁድን ሸንጎ ስብሰባ ጠሩ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው ብዙ ታምራዊ ምልክቶችን እያደረገ ስለ ሆነ ምን ብናደርግ ይሻላል?

48እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ሥፍራችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል።”

49ከመካከላቸውም አንዱ፣ በዚያ ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እናንተ እኮ ምንም አታውቁም!

50ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት የሚሻል መሆኑን አታስተውሉም።”

51ይህን ያለው ከራሱ አልነበረም፤ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ፣ ኢየሱስ ለአይሁድ ሕዝብ እንደሚሞት ትንቢት መናገሩ ነበር፤

52ለዚያም ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች በአንድነት ለመሰብሰብ ነው።

53ከዚያን ቀን ጀምሮም፣ ሊገድሉት አሤሩ።

54ስለዚህ ኢየሱስ ከዚያ ወዲያ በአይሁድ መካከል በይፋ አልተመላለሰም፤ ነገር ግን በምድረ በዳ አጠገብ ወደምትገኝ ኤፍሬም ወደተባለች መንደር ገለል አለ፤ በዚያም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሰነበተ።

55የአይሁድ ፋሲካ እንደ ተቃረበም፣ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የመንጻት ሥርዐት ለማድረግ ብዙዎች ከአገር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።

56ኢየሱስንም ይፈልጉት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ቆመው፣ “ምን ይመስላችኋል? ለበዓሉ አይመጣ ይሆን?” ተባባሉ።

57የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን ይይዙት ዘንድ የት እንዳለ የሚያውቅ ሰው እንዲጠቊም ትእዛዝ ሰጥተው ነበር።

ማብራሪያ

11:1-6 ክርስቶስ ለሚወዳቸው ሰዎች መታመም አዲስ ነገር አይደለም፤ የሰውነት ደዌዎች የብልሹነት ዝንባሌያችንን ያስተካክላሉ፣ የእግዚአብሔርንም ሕዝቦች ጸጋዎች ይፈትናሉ። እርሱ ሕዝቡን ከእነዚህ መከራዎች ለመጠበቅ አልመጣም፤ ነገር ግን ከኃጢአታቸውና ከመምጣት ካለው ቁጣ ሊያድናቸው እንጂ። ሆኖም ግን፣ ሲታመሙና ሲቸገሩ ለሚገኙ ወዳጆቻችንና ዘመዶቻችን በእርሱ ፊት መማለድ ይገባናል። ይህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር የሚያመጣ በመሆኑ፣ የአምላክ አቅርቦት ከሚመስሉን ከጨለማ አያያዞች ጋር እንድንታረቅ ያድርገን። ሕመም፣ ኪሳራና ብስጭትም እንደዚሁ ናቸው፤ እግዚአብሔር ከተከበረ፣ እኛም ልንረካ ይገባናል። ኢየሱስ ማርታን፣ እኅቷንም፣ አልዓዛርንም ይወድ ነበር። ፍቅርና ሰላም የሚበዛባቸው ቤተሰቦች እጅግ የተባረኩ ናቸው፤ ነገር ግን ኢየሱስ የሚወዳቸውና በእነርሱም የሚወደድባቸው እጅግ ደስተኞች ናቸው። የሚያሳዝነው ግን፣ በትናንሽ ቤተሰቦች ውስጥ እንኳ ይህ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር እምብዛም አይከሰትም። እግዚአብሔር የዘገየ ሲመስል እንኳ፣ ጸጋ የተሞላባቸው ዓላማዎች አሉት። የመዳን ሥራ፣ ጊዜያዊም ይሁን መንፈሳዊ፣ የሕዝብም ይሁን የግል፣ ሲዘገይ፣ ለትክክለኛው ጊዜ ብቻ ይጠብቃል።

11:7-10 ክርስቶስ ሕዝቡን ወደ ምንም ዓይነት አደጋ ባመጣቸው ጊዜ ሁሉ፣ እርሱ ራሱም ከእነርሱ ጋር አብሮ ይሄዳል። ብዙውን ጊዜ ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደሆንን እንገምታለን፤ ነገር ግን በእርግጥ ለሀብታችን፣ ለክብራችን፣ ለምቾታችንና ለደህንነታችን ብቻ ቀናተኞች ስንሆን ነው። ስለዚህ፣ መርሆዎቻችንን መፈተሽ ያስፈልገናል። ነገር ግን ሥራችን እስኪፈጸም እና ምስክርነታችንም እስኪጠናቀቅ ድረስ ቀናችን ይራዘማል። አንድ ሰው በእግዚአብሔር ቃል እንደተገለጸውና በእግዚአብሔር አርአያነት እንደተወሰነው ግዴታውን በሚፈጽምበት ጊዜ መጽናናትንና እርካታን ያገኛል። ክርስቶስ በሄደበት ሁሉ በቀን (በብርሃን) ተመላለሰ፤ እኛም ፈለጉን ከተከተልን እንዲሁ እንመላለሳለን። አንድ ሰው በልቡ መንገድ ከሄደ፣ በዚህም ዓለም አካሄድ መሰረት ከእግዚብሔር ፈቃድና ክብር ይልቅ የራሱን ሥጋዊ አስተሳሰቦች ከመከረ፣ ወደ ፈተናዎችና ወጥመዶች ይወድቃል። ይሰናከላል፤ ምክንያቱም በውስጡ ብርሃን የለምና። በውስጣችን ያለው ብርሃን ለሥነ ምግባራዊ ድርጊቶቻችን ልክ በዙሪያችን እንዳለ ብርሃን ለተፈጥሮአዊ ድርጊቶቻችን እንደሚሆን ነው።

11:11-16 በመጨረሻው ትንሣኤ እንደምናገኝ እርግጠኞች ስለሆንን፣ የዘላለም ሕይወት የሆነው የዚያ ትንሣኤ የማመን ተስፋ ሥጋችንን አውልቀን መሞትን ልብሳችንን አውልቀን እንደምንተኛው ያህል ቀላል የሚያደርግልን ለምንድን ነው? እውነተኛ ክርስቲያን ሲሞት፣ የሚተኛ ብቻ ነው። ከቀደመው ቀን ድካሞች ያርፋል። ከዚህም በላይ፣ ሞት ከእንቅልፍ የተሻለ ነው፤ ምክንያቱም እንቅልፍ ለአጭር ጊዜ ማረፊያ ብቻ ሲሆን፣ ሞት ግን የምድራዊ ጭንቀቶችና ድካሞች መጨረሻ ነው። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ አሁን ወደ አልዓዛር መሄዱ አያስፈልግም፣ እርሱንና እነርሱንም ለአደጋ ያጋልጣል ብለው አሰቡ። እንዲሁ እኛ ብዙ ጊዜ፣ እንድንሠራ የተጠራንበትን መልካም ሥራ በመሥራት ላይ አደጋ ካለ፣ በሌላ እጅ ይሠራ ዘንድ ተስፋ እናደርጋለን። ነገር ግን ክርስቶስ አልዓዛርን ከሙታን ባስነሳው ጊዜ፣ ብዙዎች በእርሱ እንዲያምኑ ተደረጉ፤ ያመኑትንም እምነት ፍጹም ለማድረግ ብዙ ተሠራ። ወደ እርሱ እንሂድ፤ ሞት ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን አይችልም፣ ወይም ከጥሪው መድረስ ክልል ውጪ ሊያደርገንም አይችልም። እንደ ቶማስ፣ በአስቸጋሪ ጊዜያት ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸው መበረታታት አለባቸው። የጌታ የኢየሱስ ሞት፣ እግዚአብሔር በጠራን ጊዜ ሁሉ ለመሞት ፈቃደኛ ሊያደርገን ይገባል።

ዮሐንስ 11:17-32 ይህ እግዚአብሔርን መፍራት የነበረበትና በረከቱ ያረፈበት ቤት ነበር፤ ሆኖም የልቅሶ ቤት ሆነ። ጸጋ ሐዘንን ከልብ ያርቃል እንጂ ከቤት አያስወግደውም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6