ትንቢተ ኤርምያስ 29

AMHNIVአማርኛ32 ጥቅሶች6:55 አዳምጥ
አዳምጥ 6:55 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ነቢዩ ኤርምያስ በምርኮ ተወስደው በሕይወት ለቀሩት ሽማግሌዎች፣ ለካህናቱ፣ ለነቢያቱና ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ለወሰዳቸው ሕዝብ ሁሉ የላከው የደብዳቤ ቃል ይህ ነው፤

2ይህም የሆነው ንጉሡ ኢኮንያን እቴጌዪቱ እናቱ፣ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎች፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም መሪዎች፣ አናጺዎችና ብረት ቀጥቃጮች ተማርከው ከኢየሩሳሌም ከተወሰዱ በኋላ ነበር።

3ደብዳቤውንም ከይሁዳ ንጉሥ ከሴዴቅያስ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር በተላኩት መልእክተኞች በሳፋን ልጅ በኤልዓሣና በኬልቅያስ ልጅ በገማርያ እጅ ላከው፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤

4የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ላስማረካቸው ሁሉ እንዲህ ይላል፤

5“ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልት ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ፤

6አግብታችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ውለዱ፤ ወንዶች ልጆቻችሁንና ሴቶች ልጆቻችሁን አጋቡ፤ እነርሱም ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ይውለዱ፤ ቍጥራችሁም በዚያ ምድር ይብዛ እንጂ አይነስ።

7ተማርካችሁ ለሄዳችሁባት ከተማ ሰላምና ብልጽግናን እሹ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸልዩላት፤ ምክንያቱም እርሷ ብትበለጽግ እናንተም ትበለጽጋላችሁ።”

8የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላልና፤ “በመካከላችሁ ያሉት ነቢያትና ጠንቋዮች አያታልሏችሁ፤ የሚያልሙላችሁንም ሕልም አትስሙ፤

9በስሜ ሐሰተኛ ትንቢት ይነግሯችኋል እንጂ እኔ አልላክኋቸውም” ይላል እግዚአብሔር።

10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።

11ለእናንተ ያለኝን ዕቅድ እኔ ዐውቃለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ዕቅዱም ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጐዳ አይደለም።

12እናንተም ትጠሩኛላችሁ፤ ቀርባችሁ ወደ እኔ ትጸልያላችሁ፤ እኔም እሰማችኋለሁ።

13እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ፤

14እኔም እገኝላችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከምርኮም እመልሳችኋለሁ፤ እናንተንም ከበተንሁበት አገርና ስፍራ ሁሉ እመልሳችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በምርኮ ምክንያት ወዳስለቀቅኋችሁም ምድር እመልሳችኋለሁ።”

15እናንተም፣ “እግዚአብሔር በባቢሎን ነቢያት አስነሥቶልናል” ትላላችሁ፤

16እግዚአብሔር ግን በዳዊት ዙፋን ላይ ስለሚቀመጠው ንጉሥና ከእናንተ ጋር ተማርኮ ስላልሄደው ወገንህ በዚህ ከተማ ስለ ቀረው ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ይላል፤

17የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥ እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን፣ ራብንና መቅሠፍትን እሰድባቸዋለሁ፤ ከመበላሸቱ የተነሣም ሊበላ እንደማይቻል እንደ መጥፎ የበለስ ፍሬ አደርጋቸዋለሁ።

18በሰይፍ፣ በራብና በመቅሠፍት አሳድዳቸዋለሁ፤ በምድር መንግሥታት ሁሉ ፊት የሚያስጸይፉ አደርጋቸዋለሁ፤ በማሳድድባቸውም ሕዝቦች ዘንድ የርግማንና የድንጋጤ፣ የመሣቂያና የመዘባበቻ ምልክት ይሆናሉ፤

19በአገልጋዮቼ በነቢያት በኩል ደጋግሜ የላክሁላቸውን ቃሌን አልሰሙምና” ይላል እግዚአብሔር፤ “እናንተ ምርኮኞችም አልሰማችሁም” ይላል እግዚአብሔር።

20“ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን የሰደድኋችሁ ምርኮኞች ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

21የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚነግሯችሁ ስለ ቆላያ ልጅ ስለ አክዓብና ስለ መዕሤያ ልጅ ስለ ሴዴቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘እነዚህን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደናፆር አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም ዐይናችሁ እያየ ይገድላቸዋል።

22በእነርሱ ላይ ከደረሰው የተነሣ በባቢሎን ያሉ የይሁዳ ምርኮኞች ሁሉ፣ “እግዚአብሔር፣ የባቢሎን ንጉሥ በእሳት እንደ ጠበሳቸው እንደ ሴዴቅያስና እንደ አክዓብ ያድርግብህ” ብለው ይራገማሉ፤

23ከባልንጀሮቻቸው ሚስቶች ጋር በማመንዘርና ያልነገርኋቸውን ቃል በስሜ በሐሰት በመናገር በእስራኤል ዘንድ በደል ፈጽመዋልና። ይህንም እኔ ዐውቃለሁ፤ ምስክር ነኝ’ ” ይላል እግዚአብሔር።

24“ለኔሔላማዊው ለሸማያ እንዲህ ብለህ ንገረው፤

25የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በኢየሩሳሌም ላለው ሕዝብ ሁሉ፣ ለካህኑ ለመዕሤያ ልጅ ለሶፎንያስና ለሌሎችም ካህናት ሁሉ በገዛ ስምህ ደብዳቤዎችን ልከሃል፤ ለሶፎንያስም እንዲህ ብለሃል፤

26“በእግዚአብሔር ቤት ኀላፊ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር በካህኑ በዮዳሄ ምትክ ካህን አድርጎ ሾሞሃል፤ ነቢይ ነኝ እያለ ትንቢት የሚናገር ማንኛውም ያበደ ሰው እግሩን በግንድ፣ ዐንገቱን በሰንሰለት መቀፍደድ ይገባሃል።

27ታዲያ፣ ነቢይ ነኝ ባዩን የዓናቶቱን ኤርምያስን ለምን አልገሠጽኸውም?

28ይህ ሰው፣ ‘የምርኮው ጊዜ ረዥም ስለ ሆነ፣ ቤት ሠርታችሁ ተቀመጡ፤ አትክልትም ተክላችሁ ፍሬውን ብሉ’ በማለት ወደ ባቢሎን መልእክት ልኮብናል።” ’ ”

29ካህኑ ሶፎንያስም ደብዳቤውን ለነቢዩ ኤርምያስ አነበበለት።

30የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

31“ይህን መልእክት በምርኮ ላሉት ሁሉ እንዲህ ብለህ ላክ፤ ‘ስለ ኔሔላማዊው ስለ ሸማያ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እኔ ሳልልከው ሸማያ ትንቢት ተናግሮላችሁ፣ በሐሰት እንድትታመኑ አድርጐአችኋልና፣

32እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ኔሔላማዊውን ሸማያንና ዘሩን እቀጣለሁ፤ በእኔ ላይ ዐመፅን ተናግሮአልና፣ በዚህ ሕዝብ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖረውም” ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ለሕዝቤ የማደርገውንም መልካም ነገር አያይም።’ ”

ማብራሪያ

29:1-7

የእግዚአብሔር የተጻፈው ቃል እንደ ተናገረው ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ የተነፈሰ እውነተኛ ቃል ነው። የጌታ ቀናተኛ አገልጋይ ሩቅ ላሉት ሰዎች እንደዚሁም ቅርብ ላሉት ሁሉ ጥቅም ለማምጣት ማንኛውንም መንገድ ይጠቀማል። የመጻፍ ጥበብ ለዚህ ዓላማ እጅግ ጠቃሚ ነው። በማተም ጥበብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እውቀት ለማሰራጨት እጅግ በጣም ጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። እግዚአብሔር በዚህ ደብዳቤ ለምርኮኞች መላኩ ምንም እንኳ ቅር ቢሰኘውና ቢቀጣቸውም እንኳ እንዳልተዋቸው ያሳያል። በእግዚአብሔር ፍርሃት ውስጥ ቢኖሩ፣ በባቢሎን በምቾት መኖር ይችላሉ። በየትኛውም የሕይወት ሁኔታ፣ የምንፈልገውን ሁሉ ስለሌለን ብቻ ያለንን ነገር ምቾት አለመጣል ጥበብና ግዴታችን ነው። ምርኮኞች ሆነው የነበሩበትን የአገሪቱን ደህንነት እንዲሹ ታዘዋል። የባቢሎን ንጉሥ ሲጠብቃቸው በነበረበት ጊዜ፣ በእርሱ ሥር በጸጥታና በሰላም፣ በሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራትና በቅንነት መኖር አለባቸው፤ ትዕግሥት አድርገውም፣ በተገቢው ጊዜ መዳናቸውን ለእግዚአብሔር አደራ እንዲሰጡ ተመክረዋል።

29:8-19 ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ የመረጧቸውን ነቢያት እንዴት እንደሚጠሩና የራሳቸውን ምኞቶችና ሕልሞች ከእግዚአብሔር የተሰጡ መገለጦች እንደሆኑ አድርገው እንዴት እንደሚቆጥሩ መጠንቀቅ ይገባቸዋል። ሐሰተኛ ነቢያት ሰዎችን በኃጢአታቸው ያሞግሳሉ፤ ምክንያቱም እነዚያ ሰዎች መወደድን ይወዳሉና። ሰዎቹም ለነቢያቶቻቸው በደግነት ይናገራሉ፣ ይህም ነቢያቶቻቸውም ለእነርሱ በደግነት እንዲናገሩላቸው ነው።

እግዚአብሔር ሰባ ዓመታት ከተፈጸሙ በኋላ እንደሚመለሱ ቃል ገብቷል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG ነቢዩ ኤርምያስ ወደ ተረፉት የምርኮ ሽማግሌዎች፥ ወደ ካህናቱም፥ ወደ ነቢያቱም፥ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማርኮ ወዳፈለሰውም ሕዝብ ሁሉ ከኢየሩሳሌም የላከው የደብዳቤው ቃል ይህ… አማርኛ ENGNIV This is the text of the letter that the prophet Jeremiah sent from Jerusalem to the surviving elders among the exiles a… English BCV ነቢይ ኤርሚያስ ነቶም ብህይወት ዝነብሩ ሽማግለታትን፥ ነቶም ካህናትን ነቢያትን፥ ንዅሎም ነቶም ናቡከደነፆር ካብ ኢየሩሳሌም ማሪኹ ናብ ባቢሎን ዝወሰዶም ህዝቢ፥ ዝለኣኸሎም ቃል መልእኽቲ እዙ… ትግርኛ GAZBIB Ani Ermiyaas raajichi jaarsolii warra hafanitti luboota, raajota, guutummaa namoota warra Nebukadnezaar Yerusaalemii bo… Afaan Oromoo BCV GIZ ወከመዝ ውእቱ ነገረ መጽሐፍ ዘፈነወ ኤርምያስ ነቢይ እምኢየሩሳሌም ኀበ እለ ተርፉ ረበናት እለ አፍለስዎሙ፤ ወኀበ ካህናት ወኅበ ሐሳውያነ ነቢያት ወኀበ ኵሉ ሕዝብ ዘአፍለሰ ናቡከደነፆር ንጉ… giz GAZGAZ Ani Ermiyaas raajichi jaarsolii warra hafanitti luboota, raajota, guutummaa namoota warra Nebukadnezaar Yerusaalemii bo… Afaan Oromoo BCV aksum ነቢይ ኤርሚያስ ነቶም ብህይወት ዝነብሩ ሽማግለታትን፥ ነቶም ካህናትን ነቢያትን፥ ንዅሎም ነቶም ናቡከደነፆር ካብ ኢየሩሳሌም ማሪኹ ናብ ባቢሎን ዝወሰዶም ህዝቢ፥ ዝለኣኸሎም ቃል መልእኽቲ እዙ… ትግርኛ SWAHSUV Maneno haya ndiyo maneno ya waraka, ambao nabii Yeremia aliupeleka toka Yerusalemu, kwa hao waliobaki wa wakuu waliochu… Kiswahili