ትንቢተ ኤርምያስ 23

AMHNIVአማርኛ40 ጥቅሶች8:16 አዳምጥ
አዳምጥ 8:16 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1“በማሰማሪያ ቦታዬ ያሉትን በጎቼን ለሚያጠፉና ለሚበትኑ እረኞች ወዮላቸው!” ይላል እግዚአብሔር።

2ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሕዝቤን ስለሚጠብቁ እረኞች እንዲህ ይላል፤ “መንጋዬን ስለ በተናችሁ፣ ስላባረራችሁና ተገቢውን ጥንቃቄ ስላላደረጋችሁላቸው፣ ለክፋታችሁ ተገቢውን ቅጣት አመጣባችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤

3“የመንጋዬንም ቅሬታ ካባረርሁባቸው አገሮች ሁሉ እኔ ራሴ ሰብስቤ፣ ወደ መሰማሪያቸው እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ይበዛሉም።

4የሚጠብቋቸውን እረኞች አስነሣላቸዋለሁ፤ ከእንግዲህም አይፈሩም፤ አይደነግጡም ከእነርሱም አንድ እንኳ አይጐድልም” ይላል እግዚአብሔር።

5“እነሆ፤ ለዳዊት፣ ጻድቅ ቅርንጫፍ የማስነሣበት ጊዜ ይመጣል፤ እርሱም ፍትሕንና ጽድቅን የሚያደርግ፣ በጥበብ የሚገዛ ንጉሥ ይሆናል” ይላል እግዚአብሔር።

6በእርሱም ዘመን ይሁዳ ይድናል፤ እስራኤልም በሰላም ይኖራል፤ የሚጠራበትም ስም፣ ‘እግዚአብሔር ጽድቃችን’ የሚል ነው።

7“ስለዚህ ሰዎች፣ ‘እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን!’ ብለው ከእንግዲህ የማይምሉበት ዘመን ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

8ነገር ግን፣ ‘እስራኤልን ከሰሜን ምድርና እነርሱን ከበተነባቸው ከሌሎች አገሮች ያወጣ ሕያው እግዚአብሔርን’ ይላሉ፤ ከዚያ በኋላ በገዛ ምድራቸው ይኖራሉ።

9ስለ ነቢያት፣ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል፤ ዐጥንቶቼም ተብረክርከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ፣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ፣ የወይን ጠጅ እንዳሸነፈው፣ እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ።

10ምድሪቱ በአመንዝሮች ተሞልታለች፤ ከርግማን የተነሣ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በምድረ በዳ ያሉት መሰማሪያዎች ደርቀዋል። ነቢያቱም ጠማማ መንገድ ተከትለዋል፤ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ ተጠቅመዋል።

11“ነቢዩም፣ ካህኑም በጽድቅ መንገድ የማይሄዱ ናቸው፤ በቤተ መቅደሴ እንኳ ሳይቀር ክፋታቸውን አይቻለሁ።” ይላል እግዚአብሔር።

12“ስለዚህ መንገዳቸው ድጥ ይሆናል፤ ወደ ጨለማ ይጣላሉ፤ ተፍገምግመውም ይወድቃሉ፤ በሚቀጡበትም ዓመት፣ መዓት አመጣባቸዋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።

13“በሰማርያ ባሉ ነቢያት ላይ፣ ደስ የማያሰኝ ነገር አይቻለሁ፤ በበኣል ስም ትንቢት ተናገሩ፤ ሕዝቤን እስራኤልን አሳቱ።

14በኢየሩሳሌም ባሉ ነቢያትም ላይ፣ የሚዘገንን ነገር አይቻለሁ፤ ያመነዝራሉ፤ በመዋሸትም ይኖራሉ፤ ማንም ከክፋቱ እንዳይመለስ፣ የክፉዎችን እጅ ያበረታሉ፤ በእኔ ዘንድ ሁሉም እንደ ሰዶም፣ ነዋሪዎቿም እንደ ገሞራ ናቸው።”

15ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ነቢያት እንዲህ ይላል፤ “ከኢየሩሳሌም ነቢያት፣ በምድሪቱ ሁሉ ርኵሰት ተሠራጭቶአልና፤ መራራ ምግብ አበላቸዋለሁ፤ የተመረዘም ውሃ አጠጣቸዋለሁ።”

16የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነዚህ ነቢያት የሚተነብዩላችሁን አትስሙ፤ በባዶ ተስፋ ይሞሏችኋል፤ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ሳይሆን፣ ከገዛ ልባቸው የሆነውን ራእይ ይናገራሉ።

17እኔን ለሚንቁኝ፣ ‘እግዚአብሔር ሰላም ይሆንላችኋል ብሏል’ ይላሉ፤ የልባቸውን እልኸኝነት ለሚከተሉም ሁሉ፣ ‘ክፉ ነገር አይነካችሁም’ ይሏቸዋል።

18ቃሉን ለማየትና ለመስማት፣ እነማን የእግዚአብሔር ምክር ባለበት ቆመዋል? ቃሉን ያደመጠ፣ የሰማስ ማን ነው?

19እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐውሎ ነፋስ፣ በቍጣ ይነሣል፤ ብርቱም ማዕበል፣ የክፉዎችን ራስ ይመታል።

20እግዚአብሔር የልቡን ሐሳብ፣ ሙሉ በሙሉ ሳይፈጽም፣ ቍጣው እንዲሁ አይመለስም፤ በኋለኛው ዘመን፣ ይህን በግልጽ ትረዳላችሁ።

21እኔ እነዚህን ነቢያት አልላክኋቸውም፤ እነርሱ ግን ለራሳቸው መልእክታቸውን ይዘው ሮጡ፣ ሳልናገራቸውም፣ ትንቢት ተናገሩ።

22ምክሬ ባለበት ቢቆሙ ኖሮ፣ ቃሌን ለሕዝቤ ባሰሙ ነበር፤ ከክፉ መንገዳቸው፣ ከክፉ ሥራቸውም በመለሷቸው ነበር።

23“እኔ የቅርብ አምላክ ብቻ ነኝን? ይላል እግዚአብሔር፤ “የሩቅስ አምላክ አይደለሁምን?

24እኔ እንዳላየው፣ በስውር ቦታ ሊሸሸግ የሚችል አለን?” ይላል እግዚአብሔር። “ሰማይንና ምድርንስ የሞላሁ እኔ አይደለሁምን” ይላል እግዚአብሔር።

25“ ‘ሕልም አለምሁ ሕልም አለምሁ’ እያሉ በስሜ የሐሰት ትንቢት የሚናገሩትን የነቢያትን ቃል ሰምቻለሁ፤

26ይህ ነገር፣ የገዛ ልባቸውን ሽንገላ በሚተነብዩ በሐሰተኞች ነቢያት ልብ ውስጥ የሚቈየው እስከ መቼ ነው?

27አባቶቻቸው በኣልን በማምለክ ስሜን እንደ ረሱ፣ እነርሱ በሚነጋገሩት ሕልም፣ ሕዝቤ ስሜን እንዲረሳ ያደረጉ ይመስላቸዋል።

28ሕልመኛ ነቢይ ሕልሙን ያውራ፤ ቃሌ ያለው ግን በታማኝነት ይናገር፤ ገለባና እህል ምን አንድ አድርጎአቸው!” ይላል እግዚአብሔር።

29“ቃሌ እንደ እሳት፣ ድንጋይንም እንደሚያደቅ መዶሻ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር።

30“ስለዚህ ቃሌን እርስ በእርስ በመሰራረቅ ከእኔ እንደ ተቀበሉ አድርገው የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

31“አፈጮሌነታቸውን በመጠቀም፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ የሚሉትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤

32“እነሆ፤ ሐሰተኛ ሕልም ተመርኵዘው ትንቢት የሚናገሩትን ነቢያት እቃወማለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ እኔ ሳልልካቸው ወይም ሳልሾማቸው ደፍረው ውሸት ይናገራሉ፤ ሕዝቤንም ያስታሉ፤ ለዚህም ሕዝብ አንዳች አይረቡትም” ይላል እግዚአብሔር።

33“ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም ምንድን ነው?’ ብለው ቢጠይቁ፣ ‘ሸክሙ እናንተ ናችሁ፤ እወረውራችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር’ ብለህ መልስላቸው።

34ነቢይ ወይም ካህን ወይም ማንኛውም ሰው፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ እያለ ቢናገር፣ ያን ሰውና ቤቱን እቀጣለሁ።

35እያንዳንዱ ለባልንጀራው ወይም ለዘመዱ፣ ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠ?’ ወይም፣ ‘እግዚአብሔር ምን ተናገረ?’ ማለት ይገባዋል።

36ከእንግዲህ ግን፣ ‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብላችሁ መናገር አይገባችሁም፤ ምክንያቱም ለሰው ሁሉ የገዛ ራሱ ቃል ሸክሙ ስለሚሆን፣ የአምላካችንን የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን፣ የሕያው አምላክን ቃል ታጣምማላችሁ።

37ስለዚህ ለነቢዩ፣ ‘እግዚአብሔር ምን መልስ ሰጠህ’ ወይም፣ ‘እግዚአብሔር ምን ተናገረህ?’ ትለዋለህ፤

38‘የእግዚአብሔር ሸክም’ ብትሉ እንኳ፣ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ፣ “የእግዚአብሔር ሸክም” አትበሉ ብዬ ብነግራችሁም፣ እናንተ፣ “የእግዚአብሔር ሸክም” ብላችኋል፤

39ስለዚህ እናንተን፣ እንዲሁም ለእናንተና ለአባቶቻችሁ የሰጠኋትን ከተማ ጭምር ፈጽሜ እተዋችኋለሁ፤ ከፊቴ እጥላችኋለሁ፤

40ለዘላለም የማይረሳ ዕፍረት፣ የዘላለምም ውርደት አመጣባችኋለሁ።

ማብራሪያ

23:1-8 የእግዚአብሔርን ሕዝብ እንዲመግቡ ለተሾሙት፥ ነገር ግን መልካም ለማድረግ ግድ የሌላቸው ወዮላቸው! እነሆ፥ ለተዘነጉት በጎች የመጽናናት ቃል ቀርቧል። የእግዚአብሔር መንጋ ቅሬታ ቢቀርም፥ እርሱ ይፈልጋቸዋል፤ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸውም ይመራቸዋል። ክርስቶስ ከዳዊት ቤተሰብ የወጣ ዘር ተብሎ ተጠቅሷል። እርሱ ራሱ ጻድቅ ነው፤ በእርሱም አማካኝነት ሕዝቡ ሁሉ ይጸድቃሉ። ክርስቶስ የሰይጣንን የተቀማውን ሥልጣን ይሰብራል። የአብርሃምና የያዕቆብ መንፈሳዊ ዘር ሁሉ ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ዕዳና ከሥልጣኑም ይድናል። በነፍስ ውስጥ በክርስቶስ ግዛት ዘመን ነፍስ በሰላም ትኖራለች። እርሱ እዚህ 'ጌታ ጽድቃችን' ተብሎ ተጠቅሷል። እርሱ የኛ ጽድቅ የሆነው ምንም ፍጡር ሊሆን እንደማይችል ልዩ በሆነ መንገድ ነው። እስከ ሞት ድረስ ያለው የእርሱ ታዛዥነት የምእመናን ማጽደቂያ ጽድቅና የሰማያዊ ደስታቸው መብታቸው ነው። የእነርሱም ቅድሳት፥ ለሁሉም የግል ታዛዥነታቸው ምንጭ እንደሆነ፥ ከእርሱ ጋር በመተባበራቸውና የመንፈሱም አቅርቦት ውጤት ነው። በዚህ ስም እያንዳንዱ እውነተኛ አማኝ ይጠራዋል እንዲሁም ይማጸነዋል። ከዚህ ውጭ የምንለምነው ነገር የለንም፤ ክርስቶስ ሞቷል፥ ይልቁንም ዳግመኛ ተነስቷል፤ እርሱንም ጌታችን አድርገን ተቀብለነዋል። እርሱ ያከናወነው ይህ ጽድቅ፥ ለሕግና ለፍትሕ እርካታ ሲባል፥ የኛ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መንፈስ አማካኝነት በነጻ የተሰጠን ስጦታ በመሆን እርሱም በላያችን ላይ ያኖረዋል፥ ይለብሰናል፥ እንድንይዘውም ኃይል ይሰጠናል፥ በውስጡም ድርሻ እንድንጠይቅ ያደርገናል። ጌታ ጽድቃችን የሚለው ስም ንስሐ ለገባ ኃጢአተኛ፥ በኅሊናው የኃጢአትን ዕዳ ለተሰማው፥ የዚያንም ጽድቅ አስፈላጊነትና ዋጋውን ላየ፥ ጣፋጭ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6