1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጒዳዬን በፊትህ ሳቀርብ፣ አንተ ጻድቅ መሆንህን እያወቅሁ ነው። የክፉዎች መንገድ ለምን ይሰምራል? የከዳተኞችስ ኑሮ ለምን ይሳካል?
2አንተ ተክለሃቸዋል፤ ሥርም ሰደዋል፤ አድገዋል፤ ፍሬም አፍርተዋል። ሁል ጊዜ አንተ በአፋቸው ላይ አለህ፤ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ።
3ነገር ግን እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ እኔን ታውቀኛለህ፤ ታየኛለህ፤ ስለ አንተም ያለኝን ሐሳብ ትመረምራለህ። እንደሚታረዱ በጎች ንዳቸው፤ ለዕርድም ቀን ለይተህ አቈያቸው፤
4ምድሪቱ በዝናብ እጦት የምትጐዳው፣ የሜዳውም ሣር ሁሉ በድርቅ የሚመታው እስከ መቼ ነው? ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ፣ እንስሳትና አዕዋፍ ጠፍተዋል፤ ደግሞም ሕዝቡ፣ “በእኛ ላይ የሚሆነውን አያይም” ብለዋል።
5“ከእግረኞች ጋር ሮጠህ፣ እነርሱ ካደከሙህ፣ ከፈረሰኞች ጋር እንዴት ልትወዳደር ትችላለህ? በሰላም አገር ከተሰናከልህ፣ በዮርዳኖስ ደን ውስጥ እንዴት ልትሆን ነው?
6ወንድሞችህና የገዛ ቤተ ሰብህ፣ እነርሱ እንኳ አሢረውብሃል፣ በአንተም ላይ ይጮኻሉ፤ በመልካም ቢናገሩህም እንኳ አትመናቸው።
7“ቤቴን እተዋለሁ፤ ርስቴን እጥላለሁ፤ የምወዳትን እርሷን፣ አሳልፌ በጠላቶቿ እጅ እሰጣታለሁ።
8ርስቴ፣ በዱር እንዳለ አንበሳ ተነሥታብኛለች በእኔም ላይ ጮኻብኛለች፤ ስለዚህ ጠላኋት።
9ርስቴ ሌሎች አሞሮች፣ ሊበሏት እንደ ከበቧት፣ እንደ ዝንጕርጕር አሞራ አልሆነችምን? ሂዱ፤ የዱር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፤ እንዲቀራመቷትም አምጧቸው።
10ብዙ እረኞች የወይን ቦታዬን ያጠፋሉ፤ ይዞታዬንም ይረግጣሉ፤ ደስ የምሰኝበትንም ማሳ፣ ጭር ያለ በረሓ ያደርጉታል።
11በፊቴ ባድማ፣ ደረቅና ወና ይሆናል፤ መላዪቱም ምድር ጠፍ ትሆናለች፤ ስለ እርሷ የሚገደው የለምና።
12በምድረ በዳ ባሉት ወና ኰረብቶች ላይ፣ አጥፊዎች ይሰማራሉ፤ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ጫፍ እስከ ምድር ጫፍ፣ አንዳች ሳያስቀር ይበላል፤ የሚተርፍም የለም።
13ስንዴን ይዘራሉ፤ እሾኽን ያጭዳሉ፤ ይደክማሉ፤ የሚያገኙት ግን የለም፤ ከእግዚአብሔርም ጽኑ ቍጣ የተነሣ፣ በመኸራችሁ ውጤት ታፍራላችሁ።”
14እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሕዝቤ ለእስራኤል የሰጠሁትን ርስት የሚይዙትን ክፉ ጎረቤቶቼን ሁሉ፣ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅላለሁ፤
15ከነቀልኋቸው በኋላ ግን መልሼ እምራቸዋለሁ፤ እያንዳንዳቸውንም ወደ ገዛ አገራቸውና ወደ ገዛ ርስታቸው መልሼ አመጣቸዋለሁ።
16የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩና ሕዝቤን በበኣል እንዲምል እንዳስተማሩት ሁሉ፣ ‘ሕያው እግዚአብሔርን’ ብለው በስሜ ቢምሉ፣ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ፤
17የማይሰማኝን ሕዝብ ግን ፈጽሜ እነቅለዋለሁ፤ አጠፋዋለሁም” ይላል እግዚአብሔር።