ትንቢተ ኢሳይያስ 8

AMHNIVአማርኛ22 ጥቅሶች4:05 አዳምጥ
አዳምጥ 4:05 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ትልቅ ሰሌዳ ወስደህ፣ ‘ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ’ ብለህ በተለመደው በሰው ፊደል ጻፍበት።

2እኔም፣ ካህኑን ኡሪያንንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ታማኝ ምስክሮቼ እንዲሆኑ እጠራቸዋለሁ።”

3እኔም ወደ ነቢዪቱ ሄድሁ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እግዚአብሔርም፣ እንዲህ አለኝ፤ “ስሙን ማኸር-ሻላል-ሃሽ-ባዝ ብለህ ጥራው።

4ሕፃኑም፣ ‘አባባ’ ወይም ‘እማማ’ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት፣ የደማስቆ ሀብትና የሰማርያ ምርኮ በአሦር ንጉሥ ይወሰዳል።”

5እግዚአብሔርም እንደ ገና እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤

6“ይህ ሕዝብ በጸጥታ የሚፈሰውን የሰሊሆምን ውሆች ትቶ፣ በረአሶንና በሮሜልዩ ልጅ ተደስቶአልና።

7ስለዚህ ጌታ ታላቁንና ብርቱውን የጐርፍ ውሃ፣ የአሦርን ንጉሥ ከነግርማ ሞገሱ ሁሉ ያመጣባቸዋል። ውሃውም ከቦዩ ዐልፎ ተርፎ በወንዙ ዳር ያለውን ምድር ሁሉ ያጥለቀልቃል፤

8እየጠራረገ ወደ ይሁዳ ይወርዳል፤ እያጥለቀለቀ ያልፋል፤ እስከ ዐንገትም ይደርሳል፤ አማኑኤል ሆይ፤ የተዘረጉ ክንፎቹ ምድርህን ከዳር እስከ ዳር ይሸፍናሉ።”

9እናንተ አሕዛብ፣ ፎክሩ፤ ግን ደንግጡ። በሩቅ አገር ያላችሁ አድምጡ፤ ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤ ለጦርነትም ተዘጋጁ፤ ነገር ግን ደንግጡ፤

10ተመካከሩ፤ ግን አይሳካም፤ ዕቅድ አውጡ፤ ሆኖም አይጸናም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።

11እግዚአብሔር ብርቱ እጁን በላዬ አድርጎ የእነዚህን ሰዎች መንገድ እንዳልከተል አስጠነቀቀኝ፤ እንዲህም አለኝ፤

12“እነዚህ ሰዎች፣ ‘አድማ’ ብለው የሚጠሩትን፣ ማንኛውንም ነገር፣ ‘አድማ’ አትበሉ፤ እነርሱ የሚፈሩትን አትፍሩ፤ አትሸበሩለትም።

13ልትቀድሱ የሚገባው የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ብቻ ነው፤ ልትፈሩት የሚገባው እርሱን ነው፤ ልትንቀጠቀጡለት የሚገባውም እርሱ ነው።

14እርሱም መቅደስ ይሆናል፤ ለሁለቱ የእስራኤል ቤት ግን የሚያደናቅፍ ድንጋይ የሚያሰናክልም ዐለት ይሆንባቸዋል፤ ለኢየሩሳሌም ሕዝብም ወጥመድና አሽክላ ይሆናል።

15ከእነርሱ ብዙዎች ይሰናከላሉ፤ ይወድቃሉ፤ ይሰበራሉ፤ ወጥመድ ይገባሉ፤ ይያዛሉም።”

16ምስክርነቱን አሽገው፤ ሕጉንም በደቀ መዛሙርቴ መካከል አትመው።

17ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሸሸገውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፤ እርሱንም ተስፋ አደርጋለሁ።

18እነሆ፤ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሰራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ለእስራኤል ምልክትና ድንቅ ነን።

19ሰዎች፣ “የሚያነበንቡትንና የሚያሾካሹኩትን ሟርተኞችንና መናፍስት ጠሪዎችን ጠይቁ ቢሏችሁ፣ ሕዝቡ አምላኩን መጠየቅ አይገባውምን? በሕያዋን ምትክ ሙታንን መጠየቅ ለምን አስፈለገ?

20ወደ ሕጉና ወደ ምስክር ቃሉ ሂዱ! እነርሱም እንዲህ ያለውን ቃል ባይናገሩ የንጋት ብርሃን አይበራላቸውም።

21ተጨንቀውና ተርበው በምድሪቱ ላይ ይንከራተታሉ፤ ክፉኛ ሲራቡም ይቈጣሉ፤ ወደ ላይ እየተመለከቱ ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይራገማሉ።

22ከዚያም ወደ ምድር ይመለከታሉ፣ የሚያዩትም ጭንቀት፣ ጨለማና የሚያስፈራም ጭጋግ ብቻ ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ።

ማብራሪያ

፰፡፩-፰ ነቢዩ በትልቅ ጥቅልል ወይም በብረት ሰሌዳ ላይ፣ ትርጉማቸውም "ለመበዝበዝ ፍጠኑ፣ ምርኮን ለማግኘትም ተጣደፉ" የሚሉ ቃላትን እንዲጽፍ ታዘዘ፤ ይህ የሚያመለክተውም የአሦር ሠራዊት በፍጥነት እንደሚመጣና ታላቅ ምርኮ እንደሚወስድ ነበር። በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የደማስቆና የሰማርያ ሀብት፣ በዚያን ጊዜ አስተማማኝና የሚያስፈሩ የነበሩ ከተሞችም፣ በአሦር ንጉሥ ይወሰዳሉ። ነቢዩ የተስፋውን መሲሕ ይማልዳል፤ እርሱም በዘመኑ ፍጻሜ በዚያች ምድር የሚገለጥና፣ ስለዚህም እንደ እግዚአብሔር፣ በዚያን ጊዜ ይጠብቃት ነበርና። ልዝብ ጅረት የገር አስተዳደር ተገቢ ምሳሌ እንደሆነ ሁሉ፣ የተትረፈረፈ ጎርፍም አሸናፊና ጨካኝ ገዥን ያመለክታል። ወራሪው ያገኘው ድልም ክንፎቿን በመላው ምድር ላይ ዘርግታ የምትበር አዳኝ ወፍ ተብሎ ተገልጿል። ክርስቶስን የሚጥሉ ሰዎች፣ ነጻነት ብለው የሚጠሩት ነገር እጅግ አሳፋሪ ባርነት እንደሆነ ያገኛሉ። ነገር ግን አንድም ጠላት አማኙን ከእማኑኤል እጅ ሊነጥቀው ወይም ከሰማያዊ ርስቱ ሊያሳጣው አይችልም።

፰፡፱-፲፮ ነቢዩ የአይሁድን ጠላቶች ይሞግታል። ጥረታቸው ከንቱ ይሆናል፤ እነርሱም ይደቃሉ። በመከራ ጊዜ፣ ለራሳችን ደኅንነት ብለን ወደ ተጣመመ መንገድ ከሚመሩን ፍርሃቶች ሁሉ መጠንቀቅ ያስፈልገናል። እግዚአብሔርን በአምልኮ መፍራት ሰውን ከመፍራት ከሚመጣ ጭንቀት ይከላከላል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6