ትንቢተ ኢሳይያስ 65

AMHNIVአማርኛ25 ጥቅሶች5:28 አዳምጥ
አዳምጥ 5:28 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1“ላልለመኑኝ ራሴን ገለጥሁላቸው፤ ላልፈለጉኝ ተገኘሁላቸው። ስሜን ላልጠራ ሕዝብ፣ ‘አለሁልህ፤ አለሁልህ’ አልሁት።

2ለዐመፀኛ ሕዝብ፣ መልካም ባልሆኑ መንገዶች ለሚሄዱ፣ የልባቸውን ምኞት ለሚከተሉ፣ ቀኑን ሙሉ እጆቼን ዘረጋሁ። ዘወትር በፊቴ የሚያስቈጡኝ ሕዝቦች፣

3በአትክልት ቦታዎች መሥዋዕት የሚያቀርቡ፣ በሸክላ መሠዊያዎች ላይ ዕጣን የሚያጥኑ፣ ዘወትር በፊቴ የሚያስቈጡኝ ሕዝብ ናቸው፤

4በመቃብር መካከል የሚቀመጡ፣ በስውር ቦታዎች የሚያድሩ፣ የዕሪያ ሥጋ የሚበሉ፣ ማሰሮዎቻቸውን በረከሰ ሥጋ መረቅ የሚሞሉ ናቸው፤

5‘ዘወር በል፤ አትቅረበኝ፤ አትጠጋኝ፤ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝ’ የሚሉ ናቸው። እንዲህ ያለው ሕዝብ በአፍንጫዬ ዘንድ እንደ ጢስ፣ ቀኑን ሙሉ እንደሚነድድ እሳት ነው።

6“እነሆ፤ እንዲህ የሚል ተጽፎ በፊቴ ተቀምጦአል፤ ዝም አልልም፤ ነገር ግን እንደ ሥራው እሰጠዋለሁ፤ የእጃቸውንም እከፍላቸዋለሁ፤

7የእናንተን ኀጢአት የአባቶቻችሁንም ኀጢአት እበቀላለሁ” ይላል እግዚአብሔር። “በተራሮች ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት ስላቀረቡ፣ በኰረብቶች ላይ ስለ ሰደቡኝ፣ በሰፈሩት ቊና ይሰፈርባቸዋል፤ ስለ ቀደሙት ሥራዎቻቸውም የእጃቸውን ያገኛሉ።”

8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በወይኑ ዘለላ ውስጥ ጭማቂው ገና እንዳለ ሁሉ፣ ሰዎችም፣ ‘በውስጡ ጥሩ ነገር ስላለ አትቊረጡት’ እንደሚሉ፣ እኔም ስለ ባሮቼ ስል እንዲሁ አደርጋለሁ፤ ሙሉ በሙሉ አላጠፋቸውም።

9ከያዕቆብ ዘር የሆኑትን፣ ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሱትን አመጣለሁ። የተመረጠው ሕዝቤ ይወርሳቸዋል፤ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ።

10አጥብቀው ለሚፈልጉኝ ሕዝቤ፣ ሳሮን የበጎች መሰማሪያ፣ የአኮር ሸለቆም የከብቶች ማረፊያ ይሆናል።

11“ነገር ግን እግዚአብሔርን ለተዋችሁት ለእናንተ፣ የተቀደሰ ተራራዬን ለረሳችሁት፣ ‘ዕጣ ፈንታ’ ለተባለ ጣዖት ቦታ ላዘጋጃችሁት፣ ‘ዕድል’ ለተባለም ጣዖት ድብልቅ የወይን ጠጅ በዋንጫ ለሞላችሁት፣

12ተጣርቼ ስላልመለሳችሁ፣ ተናግሬ ስላልሰማችሁ፣ በፊቴ ክፉ ነገር ስላደረጋችሁ፣ የሚያስከፋኝን ነገር ስለ መረጣችሁ፣ ለሰይፍ እዳርጋችኋለሁ፤ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ።”

13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ባሮቼ ይበላሉ፤ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ ባሮቼ ይጠጣሉ፤ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ ባሮቼ ደስ ይላቸዋል፤ እናንተ ግን ታፍራላችሁ።

14ባሮቼ፣ ከልብ በመነጨ ደስታ ይዘምራሉ፤ እናንተ ግን፣ ልባችሁ በማዘኑ ትጮኻላችሁ፤ መንፈሳችሁ በመሰበሩም ወዮ ትላላችሁ።

15ስማችሁንም፣ የተመረጠው ሕዝቤ ርግማን እንዲያደርገው ትተዋላችሁ፤ ጌታ እግዚአብሔር ይገድላችኋል፤ ለአገልጋዮቹ ግን ሌላ ስም ይሰጣቸዋል።

16ስለዚህ በምድሪቱ ላይ በረከትን የሚጠራ፣ በእውነት አምላክ ስም ይባረካል፤ በምድሪቱ መሐላን የሚምል፣ በእውነት አምላክ ስም ይምላል፤ ያለፉት ችግሮች ተረስተዋል፤ ከዐይኖቼም ተሰውረዋል።

17“እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም።

18ነገር ግን በምፈጥረው፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለዘላለም ሐሤት አድርጉ። ኢየሩሳሌምን ለደስታ፣ ሕዝቧን ለሐሤት እፈጥራለሁና።

19በኢየሩሳሌም እደሰታለሁ፤ በሕዝቤ ሐሤት አደርጋለሁ፤ የልቅሶና የጩኸት ድምፅ፣ ከእንግዲህ በዚያ አይሰማም።

20“ከእንግዲህም በዚያ፣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ በሕይወት የሚኖር ሕፃን፣ ወይም ዕድሜ ያልጠገበ አረጋዊ አይኖርም፤ አንድ መቶ ዓመት የሞላው ሰው ቢሞት፣ በአጭር እንደ ተቀጨ ይቈጠራል፤ አንድ ሰው መቶ ዓመት ሳይሞላው ቢሞት፣ እንደ ተቀሠፈ ይገመታል።

21ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።

22ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ፣ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይረዝማል፤ እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።

23ድካማቸው በከንቱ አይቀርም፤ ዕድለ ቢስ ልጆችም አይወልዱም፤ እነርሱና ዘራቸው፣ እግዚአብሔር የባረከው ሕዝብ ይሆናሉ።

24ገና ሳይጣሩ እመልስላቸዋለሁ፤ ተናግረው ሳይጨርሱ እሰማለሁ።

25ተኵላና የበግ ጠቦት በአንድነት ይበላሉ፤ አንበሳ እንደ በሬ ሣር ይበላል፤ እባብ ትቢያ ይልሳል፤ በተቀደሰው ተራራዬም፣ ጒዳት አያደርሱም፤ ጥፋት አያመጡም፤” ይላል እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

፷፭:፩-፯ አሕዛብ እግዚአብሔርን ለመፈለግ መጡና አገኙት፤ ምክንያቱም እርሱ አስቀድሞ ስለፈለጋቸውና ስላገኛቸው ነው። ብዙ ጊዜ እርሱ አንዳች ግድ የለሽ ተጫዋችን ወይም በደለኛ ተቃዋሚን ያገኛል፤ እርሱንም፦ "እነሆኝ!" ይለዋል። ወዲያውም ፈጣን ለውጥ ይከናወናል። በወንጌል ዘመን ሁሉ ክርስቶስ በጸጋ ለመስጠት ሲጠባበቅ ነበር። አይሁድ ተጠርተው ነበር፣ ግን ሊመጡ አልወደዱም። በእግዚአብሔር ውድቅ የተደረጉት ያለ ምክንያት አይደለም። ለራሳቸው እጅግ ደስ የሚያሰኛቸውን ያደርጉ ነበር። መንፈስ ቅዱስን አስከፉት፣ አበሳጩትም። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ተዉ፣ በጫካዎችም ውስጥ ይሠዉ ነበር። በወንጌል ከመወገዱ በፊት በንጹሕና በረከሱ ምግቦች መካከል ያለውን ልዩነት ግድ አልሰጣቸውም ነበር። ምናልባት ይህ ለተከለከሉ ደስታዎች ሁሉ፣ ከኃጢአት የሚገኝ መስሎ ለሚታየው ነገር ሁሉ፣ ጌታ ለሚጠላውም ለዚያ አስጸያፊ ነገር ተብሎ የተገለጸ ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ በአይሁድ ትዕቢትና ግብዝነት ላይ ብዙ ወዮታዎችን ተናገረ። በእነርሱ ላይ ያለው ማስረጃ ግልጽ ነው። እኛም ከትዕቢትና ራስን ከማስቀደም እንጠንቀቅ፤ እያንዳንዱ ኃጢአትና የሰው ልብ እጅግ የተሰወሩ ሐሳቦችም ጭምር በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቁና የሚፈረድባቸው እንደሆኑ እናስታውስ።

፷፭፥፰-፲። ባልበሰለው የወይን ዘለላ ውስጥ፣ በአሁኑ ጊዜ ምንም ዋጋ ባይኖረውም፣ አዲሱ ወይን በውስጡ ይገኛል። አይሁድ የተለየ ሕዝብ ሆነው ተጠብቀዋል፣ ይህም ሁሉም የጥንት ትንቢቶችና የተስፋ ቃላት ፍጻሜ ምስክር እንዲሆኑ ነው። የእግዚአብሔር ምርጦች፣ የጸሎተኛው ያዕቆብ መንፈሳዊ ዘር፣ የደስታና የሐሴት ተራሮቹን ይወርሳሉ፣ እንዲሁም በእንባ ሸለቆ ውስጥ አልፈው በሰላም ወደ እነርሱ ይወሰዳሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6