ትንቢተ ኢሳይያስ 65

AMHEVGአማርኛ25 ጥቅሶች4:45 አዳምጥ
አዳምጥ 4:45 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ፦ እነሆኝ፥ እነሆኝ፡ አልሁት።

2መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁ።

3ይህ ሕዝብ ዘወትር የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥

4በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ በስውርም ስፍራ የሚያድሩ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የረከሰው መረቅ በዕቃቸው ውስጥ አለ።

5እነርሱም፦ ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ፡ ይላሉ፤ እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት ናቸው።

6እነሆ፥ በፊቴ ተጽፎአል፦ ኃጢአታችሁና የአባቶቻችሁን ኃጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ አመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፥ ይላል እግዚአብሔር፤

7በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው እሰፍራለሁ።

8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ፦ በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት፡ እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፉ ስለባሪያዎቼ እንዲሁ አደርጋለሁ።

9ከያዕቆብ ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኋቸው ይወርሱአታል፥ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ።

10ሳሮንም የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮርም ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ለፈልጉኝ ሕዝቤ ይሆናል።

11እናንተን ግን እግዚአብሔርን የተዋችሁትን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ጉድ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ እድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን የቀዳችሁትን፥

12እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።

13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ባሪያዎቼ፡ ይበላሉ፥ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤

14እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ።

15ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል።

16እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአልና፥ ከዓይኔም ተሰውሮአልና።

17እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም።

18ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።

19እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።

20ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጕልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና።

21ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ።

22ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።

23እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።

24እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ እመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ።

25ተኵላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፥ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

፷፭:፩-፯ አሕዛብ እግዚአብሔርን ለመፈለግ መጡና አገኙት፤ ምክንያቱም እርሱ አስቀድሞ ስለፈለጋቸውና ስላገኛቸው ነው። ብዙ ጊዜ እርሱ አንዳች ግድ የለሽ ተጫዋችን ወይም በደለኛ ተቃዋሚን ያገኛል፤ እርሱንም፦ "እነሆኝ!" ይለዋል። ወዲያውም ፈጣን ለውጥ ይከናወናል። በወንጌል ዘመን ሁሉ ክርስቶስ በጸጋ ለመስጠት ሲጠባበቅ ነበር። አይሁድ ተጠርተው ነበር፣ ግን ሊመጡ አልወደዱም። በእግዚአብሔር ውድቅ የተደረጉት ያለ ምክንያት አይደለም። ለራሳቸው እጅግ ደስ የሚያሰኛቸውን ያደርጉ ነበር። መንፈስ ቅዱስን አስከፉት፣ አበሳጩትም። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ተዉ፣ በጫካዎችም ውስጥ ይሠዉ ነበር። በወንጌል ከመወገዱ በፊት በንጹሕና በረከሱ ምግቦች መካከል ያለውን ልዩነት ግድ አልሰጣቸውም ነበር። ምናልባት ይህ ለተከለከሉ ደስታዎች ሁሉ፣ ከኃጢአት የሚገኝ መስሎ ለሚታየው ነገር ሁሉ፣ ጌታ ለሚጠላውም ለዚያ አስጸያፊ ነገር ተብሎ የተገለጸ ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ በአይሁድ ትዕቢትና ግብዝነት ላይ ብዙ ወዮታዎችን ተናገረ። በእነርሱ ላይ ያለው ማስረጃ ግልጽ ነው። እኛም ከትዕቢትና ራስን ከማስቀደም እንጠንቀቅ፤ እያንዳንዱ ኃጢአትና የሰው ልብ እጅግ የተሰወሩ ሐሳቦችም ጭምር በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቁና የሚፈረድባቸው እንደሆኑ እናስታውስ።

፷፭፥፰-፲። ባልበሰለው የወይን ዘለላ ውስጥ፣ በአሁኑ ጊዜ ምንም ዋጋ ባይኖረውም፣ አዲሱ ወይን በውስጡ ይገኛል። አይሁድ የተለየ ሕዝብ ሆነው ተጠብቀዋል፣ ይህም ሁሉም የጥንት ትንቢቶችና የተስፋ ቃላት ፍጻሜ ምስክር እንዲሆኑ ነው። የእግዚአብሔር ምርጦች፣ የጸሎተኛው ያዕቆብ መንፈሳዊ ዘር፣ የደስታና የሐሴት ተራሮቹን ይወርሳሉ፣ እንዲሁም በእንባ ሸለቆ ውስጥ አልፈው በሰላም ወደ እነርሱ ይወሰዳሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6