1ጽድቋ እንደ ማለዳ ወጋገን እስኪፈነጥቅ፣ ድነቷ እንደሚያንጸባርቅ ፋና እስኪታይ፣ ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም።
2መንግሥታት ጽድቅሽን፣ ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣ በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።
3በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።
4ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤ ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤ ነገር ግን፣ “ደስታዬ በእርሷ” ትባያለሽ፤ ምድርሽም፣ “ባለባል” ትባላለች፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ ምድርሽም ባለባል ትሆናለች።
5ጐልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣ ልጆችሽ እንዲሁ ያገቡሻል፤ ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣ አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።
6ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንም ሆነ ሌሊት ፈጽሞ አይታክቱም። እናንት ወደ እግዚአብሔር አቤት፣ አቤት የምትሉ፤ ፈጽሞ አትረፉ፤
7ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣ የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።
8እግዚአብሔር በቀኝ እጁ፣ በኀያል ክንዱም እንዲህ ሲል ምሎአል፤ “ከእንግዲህ እህልሽን፣ ለጠላቶችሽ መብል እንዲሆን አልሰጥም፤ ከእንግዲህ የደከምሽበትን፣ አዲስ የወይን ጠጅ ባዕዳን አይጠጡትም።
9ነገር ግን መከሩን የሰበሰቡ ይበሉታል፤ እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፤ የወይኑን ፍሬ የለቀሙም በመቅደሴ አደባባዮች ይጠጡታል።”
10ዕለፉ፤ በበሮቹ በኩል ዕለፉ፤ ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤ አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ፤ ድንጋዩን አስወግዱ፤ ለመንግሥታትም ምልክት አሳዩ።
11እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ፣ እንዲህ ሲል ዐውጆአል፤ “ለጽዮን ሴት ልጅ፣ ‘እነሆ፤ አዳኝሽ መጥቶአል፤ ዋጋሽ በእጁ አለ፤ ዕድል ፈንታሽም ከእርሱ ጋር ነው’ በሏት።”
12እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤ አንቺም የምትፈለግ፣ ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።