ትንቢተ ኢሳይያስ 59

AMHEVGአማርኛ21 ጥቅሶች4:02 አዳምጥ
አዳምጥ 4:02 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም፤

2ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።

3እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፥ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል።

4በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በምናምንቴ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጕዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል፤

5የእባብን እንቍላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቍላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቍላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል።

6ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ በሥራቸውም አይሸፈኑም፤ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው።

7እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ።

8የሰላምን መንገድ አያውቁም፥ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም፤ መንገዳቸውን አጣምመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም።

9ስለዚህ ፍርድ ከእኛ ዘንድ ርቆአል፥ ጽድቅም አላገኘንም፤ ብርሃንን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ እነሆም፥ ጨለማ ሆነ፤ ጸዳልን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ ነገር ግን በጨለማ ሄድን።

10እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዓይን እንደሌላቸው ተርመሰመስን፤ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን።

11ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፥ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን፤ ፍርድን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱም የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል።

12ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና።

13ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ አምላካችንንም ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል።

14ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና።

15እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ፥ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ።

16ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው።

17ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።

18እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቍጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፤ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል።

19እርሱ የእግዚአብሔር ነፋስ እንደሚነዳው እንደ ጐርፍ ፈሳሽ ይመጣልና በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ።

20ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

21ከእርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፥ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከአፍህ ከዘርህም አፍ ከዘር ዘርህም አፍ አያልፍም፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

59:1-8 ጸሎታችን ምላሽ ባያገኝ፣ እንዲሁም የምንጠብቀው ድነት ለእኛ ባይፈጸምልን፣ ይህ የሆነው እግዚአብሔር ጸሎት ከመስማት ስለሰለቸ አይደለም፤ ይልቁንም እኛ ጸሎት ከመጸለይ ስለሰለቸን ነውና። እዚህ ላይ ኃጢአትን በእውነተኛው ገጽታዋ፣ እጅግ በጣም ኃጢአተኛ ሆና ተመልከቱ፤ እንዲሁም ኃጢአትን በውጤቶቿ ውስጥ፣ እጅግ በጣም ጎጂ ሆና ተመልከቱ፤ ከእግዚአብሔር የምትለይ፣ በዚህም ምክንያት እኛን ከጥሩ ነገር ሁሉ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ክፉ ነገር ሁሉ የምትለየን ናት። ሆኖም በርካቶች ለራሳቸው ጥፋት በአምላክ የለሽና በክፉ ሥርዓቶች ይመገባሉ። ሸረሪት ድሯን እንደምትጎነጉነው ዕቅዶችን በማውጣት ረገድ ያላቸው ብልሃታቸውም ሆነ ተንኮላቸው ሊያድናቸው ወይም ሊያወጣቸው አይችልም። የቤዛውን የጽድቅ ልብስ ለሚንቁት በገዛ ራሳቸው የተሰሩ የመዳን ዕቅዶች አይጠቅሙም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው እያንዳንዱ ሰው ወደ አንድ ዓይነት ክፋት በፍጥነት ይሮጣል። ነገር ግን መለኮታዊ እውነትንና ፍትህን ግድ የማይሰጣቸው ለሰላም እንግዳ ናቸው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6