ትንቢተ ኢሳይያስ 40

AMHEVGአማርኛ31 ጥቅሶች4:47 አዳምጥ
አዳምጥ 4:47 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ።

2ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ።

3የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።

4ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤

5የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።

6ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው።

7የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው።

8ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።

9የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ።

10እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው።

11መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።

12ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው?

13የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው?

14ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?

15እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፤ እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል።

16ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም።

17አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ ከምናምን እንደሚያንሱ፥ እንደ ከንቱ ነገርም ይቈጥራቸዋል።

18እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?

19የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት አፍስሶለታል።

20ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል።

21አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?

22እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥

23አለቆችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው።

24ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው።

25እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ።

26ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።

27ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፦ መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፥ ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች፡ ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ?

28አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።

29ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።

30ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤

31እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።

ማብራሪያ

ኢሳይያስ 40:1-11

የሰው ሕይወት ሁሉ ውጊያ ነው፤ የክርስትና ሕይወት ደግሞ ከሁሉም በላይ ነው። ነገር ግን ትግሉ ለዘላለም አይቆይም። ኃጢአት ሲሰረይ ችግሮች በፍቅር ይወገዳሉ። በክርስቶስ ሞት በታላቁ የእርቅ ሥራ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ለጽድቁ ክብር ይገለጣል። በክርስቶስና በመከራው፣ እውነተኛ ንስሐ የገቡ ሁሉ ከጌታ እጅ ለኃጢአታቸው ሁሉ እጥፍ ይቅርታን/ጸጋን ይቀበላሉ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ በሞቱ የፈጸመው ካሣ ወሰን የሌለው ዋጋ አለውና።

ነቢዩ አይሁድ ከባቢሎን መመለሳቸውን በተወሰነ ደረጃ ጠቅሶ ነበር። ነገር ግን ይህ፣ ዮሐንስ መጥምቁ የክርስቶስን መምጣት ሲያበስር መንፈስ ቅዱስ በሐዲስ ኪዳን ካመለከተው ክስተት ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነገር ነው። የምስራቅ ነገሥታት በምድረ በዳ ሲጓዙ መንገዶች ይዘጋጁላቸው ነበር፣ እንቅፋቶችም ይወገዱ ነበር። ጌታም በቃሉ ትምህርትና በመንፈሱ ተጽዕኖ ልባችንን ያዘጋጅልን፣ ከፍ ከፍ ያሉና ትዕቢተኛ አሳቦች እንዲወርዱ፣ መልካም ምኞቶች እንዲተከሉ፣ ጠማማና የጠጠሩ ባሕርያት እንዲቃኑና እንዲለዝቡ፣ እያንዳንዱም እንቅፋት እንዲወገድ፤ በምድር ላይ ፈቃዱን ለመፈጸም ዝግጁ እንድንሆንና ለሰማያዊ መንግሥቱ እንድንዘጋጅ።

የወደቀው ሰው የያዘው ሁሉ ወይም የሚያደርገው ሁሉ እንደ ሳርና አበባው ብቻ ነው! የሚሞት ኃጢአተኛን በማውገዝ ሥር ጥለውት ሲሄዱት ማዕረጎቹና ንብረቶቹ ሁሉ ምን ይጠቅሙታል? ሥጋ ሁሉ ሊያደርገው የማይችለውን የጌታ ቃል ለእኛ ሊያደርግ ይችላል። የክርስቶስ የመምጣት ምሥራች እስከ ምድር ዳርቻ እንዲላክ ታስቦ ነበር። ሰይጣን የታጠቀው ኃያል ሰው ነው፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ይበልጥ ኃያል ነው፤ እርሱም ይገሰግሳል፣ የፈለገውንም ሁሉ ያደርጋል። ክርስቶስ መልካም እረኛ ነው፤ ለአዲስ ምዕመናን፣ ለደካማ አማኞችና ለሚያዝኑ ነፍሳት ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ ያሳያል። በቃሉ ከሚሰጣቸው ጥንካሬ በላይ አገልግሎትን አይጠይቅም፤ በመግቦቱም ከሚያበረታታቸው በላይ መከራን አያመጣም። የእረኛችንን ድምፅ እንወቅ፣ እንከተለውም፣ እኛም በጎቹ መሆናችንን እናሳይ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6