ትንቢተ ኢሳይያስ 40

AMHNIVአማርኛ31 ጥቅሶች5:53 አዳምጥ
አዳምጥ 5:53 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ።

2ለኢየሩሳሌም አለዝባችሁ ንገሯት፤ ዐውጁላትም፤ በባርነት ያገለገለችበት ዘመን አብቅቶአል፤ የኀጢአቷም ዋጋ ተከፍሎአል፤ ስለ ኀጢአቷ ሁሉ ከእግዚአብሔር እጅ ሁለት ዕጥፍ ተቀብላለች።

3የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፤ “የእግዚአብሔርን መንገድ፣ በምድረ በዳ አዘጋጁ፤ ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣ በበረሓ አስተካክሉ።

4ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ወጣ ገባው ምድር ይስተካከላል፤ ሰርጓጒጡም ሜዳ ይሆናል።

5የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፤ ሰው ሁሉ በአንድነት ያየዋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።”

6ድምፅም፣ “ጩኽ” አለኝ፤ እኔም፣ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልሁ። “ሰው ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።

7ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነፍሶበታልና፤ ሕዝቡ በርግጥ ሣር ነው።

8ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

9አንተ ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር፤ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትነግር፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጩኽ። ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፣ “እነሆ፤ አምላካችሁ!” በል።

10እነሆ፤ ልዑል እግዚአብሔር በኀይል ይመጣል፤ ክንዱ ስለ እርሱ ይገዛል። እነሆ፤ ዋጋው ከእርሱ ጋር ነው፤ የሚከፍለውም ብድራት አብሮት አለ።

11መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤ የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።

12ውሆችን በዕፍኙ የሰፈረ፣ ሰማያትን በስንዝሩ የለካ፣ የምድርን ዐፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን፣ ኰረብቶችንም በመድሎት የመዘነ ማነው?

13የእግዚአብሔርን መንፈስ የተረዳ፣ አማካሪውስ ሆኖ ያስተማረው ማነው?

14ዕውቀት ለማግኘት እግዚአብሔር ማንን አማከረ? ትክክለኛውንስ መንገድ ማን አስተማረው? ዕውቀትን ያስተማረው፣ የማስተዋልንም መንገድ ያሳየው ማን ነበር?

15እነሆ፤ አሕዛብ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤ በሚዛን ላይ እንዳለ ትቢያ ይቈጠራሉ፤ ደሴቶችንም እንደ ደቃቅ ዐፈር ይመዝናቸዋል።

16ሊባኖስ ለመሠዊያ እሳት አትበቃም፤ የእንስሶቿም ቍጥር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያንሳል።

17አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንደ ኢምንት ናቸው፤ ከምንም የማይቈጠሩ መና ናቸው።

18እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋር ታነጻጽሩታላችሁ?

19የተቀረጸውንማ ምስል ባለጅ ይቀርጸዋል፤ ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤ የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል።

20እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣ የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤ የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣ ታዋቂ ባለሙያ ይፈልጋል።

21አላወቃችሁምን? አልሰማችሁምን? ከጥንት አልተነገራችሁምን? ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?

22እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው። ሰማያትን እንደ ድባብ ይዘረጋቸዋል፤ እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።

23አለቆችን ኢምንት፣ የዚህን ዓለም ገዦች እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል።

24ተተክለው ምንም ያህል ሳይቈዩ፣ ተዘርተው ምንም ያህል ሳይሰነብቱ፣ ገና ሥር መስደድ ሳይጀምሩ አነፈሰባቸው፤ እነርሱም ደረቁ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ወሰዳቸው።

25ቅዱሱ፣ “ከማን ጋር ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።

26ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።

27ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ?

28አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።

29ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጒልበት ይጨምራል።

30ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ።

31እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።

ማብራሪያ

ኢሳይያስ 40:1-11

የሰው ሕይወት ሁሉ ውጊያ ነው፤ የክርስትና ሕይወት ደግሞ ከሁሉም በላይ ነው። ነገር ግን ትግሉ ለዘላለም አይቆይም። ኃጢአት ሲሰረይ ችግሮች በፍቅር ይወገዳሉ። በክርስቶስ ሞት በታላቁ የእርቅ ሥራ፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ለጽድቁ ክብር ይገለጣል። በክርስቶስና በመከራው፣ እውነተኛ ንስሐ የገቡ ሁሉ ከጌታ እጅ ለኃጢአታቸው ሁሉ እጥፍ ይቅርታን/ጸጋን ይቀበላሉ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ በሞቱ የፈጸመው ካሣ ወሰን የሌለው ዋጋ አለውና።

ነቢዩ አይሁድ ከባቢሎን መመለሳቸውን በተወሰነ ደረጃ ጠቅሶ ነበር። ነገር ግን ይህ፣ ዮሐንስ መጥምቁ የክርስቶስን መምጣት ሲያበስር መንፈስ ቅዱስ በሐዲስ ኪዳን ካመለከተው ክስተት ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነገር ነው። የምስራቅ ነገሥታት በምድረ በዳ ሲጓዙ መንገዶች ይዘጋጁላቸው ነበር፣ እንቅፋቶችም ይወገዱ ነበር። ጌታም በቃሉ ትምህርትና በመንፈሱ ተጽዕኖ ልባችንን ያዘጋጅልን፣ ከፍ ከፍ ያሉና ትዕቢተኛ አሳቦች እንዲወርዱ፣ መልካም ምኞቶች እንዲተከሉ፣ ጠማማና የጠጠሩ ባሕርያት እንዲቃኑና እንዲለዝቡ፣ እያንዳንዱም እንቅፋት እንዲወገድ፤ በምድር ላይ ፈቃዱን ለመፈጸም ዝግጁ እንድንሆንና ለሰማያዊ መንግሥቱ እንድንዘጋጅ።

የወደቀው ሰው የያዘው ሁሉ ወይም የሚያደርገው ሁሉ እንደ ሳርና አበባው ብቻ ነው! የሚሞት ኃጢአተኛን በማውገዝ ሥር ጥለውት ሲሄዱት ማዕረጎቹና ንብረቶቹ ሁሉ ምን ይጠቅሙታል? ሥጋ ሁሉ ሊያደርገው የማይችለውን የጌታ ቃል ለእኛ ሊያደርግ ይችላል። የክርስቶስ የመምጣት ምሥራች እስከ ምድር ዳርቻ እንዲላክ ታስቦ ነበር። ሰይጣን የታጠቀው ኃያል ሰው ነው፤ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ይበልጥ ኃያል ነው፤ እርሱም ይገሰግሳል፣ የፈለገውንም ሁሉ ያደርጋል። ክርስቶስ መልካም እረኛ ነው፤ ለአዲስ ምዕመናን፣ ለደካማ አማኞችና ለሚያዝኑ ነፍሳት ርኅራኄ የተሞላበት እንክብካቤ ያሳያል። በቃሉ ከሚሰጣቸው ጥንካሬ በላይ አገልግሎትን አይጠይቅም፤ በመግቦቱም ከሚያበረታታቸው በላይ መከራን አያመጣም። የእረኛችንን ድምፅ እንወቅ፣ እንከተለውም፣ እኛም በጎቹ መሆናችንን እናሳይ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6