ትንቢተ ኢሳይያስ 38

AMHNIVአማርኛ22 ጥቅሶች3:49 አዳምጥ
አዳምጥ 3:49 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ ታመመ፤ ሞት አፋፍ ደረሰ፤ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ ትሞታለህና ቤትህን አሰናዳ’ ” አለው።

2ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ፣ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

3“እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በታማኝነትና በፍጹም ልብ ደስ የሚያሰኝህንም በማድረግ እንዴት እንደኖርሁ አቤቱ አስብ።” ሕዝቅያስም አምርሮ አለቀሰ።

4የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

5“ሂድና ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ በዕድሜህም ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ።

6አንተንና ይህቺን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ለከተማዋም እከላከልላታለሁ።

7“ ‘እግዚአብሔር የገባልህን ቃል እንደሚፈጽምልህ፣ የእግዚአብሔር ምልክት ይህ ነው፤

8በአካዝ የሰዓት መቍጠሪያ ደረጃ ላይ፣ የወረደውን የፀሓይ ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።’ ” ስለዚህ ወርዶ የነበረው የፀሓይ ጥላ ያንኑ ያህል ወደ ኋላ ተመለሰ።

9የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከተፈወሰ በኋላ የጻፈው ጽሕፈት፤

10እኔ፣ “በዕድሜዬ እኩሌታ፣ በሲኦል ደጆች ማለፍ አለብኝን? የቀረውንስ ዘመኔን ልነጠቅ ይገባልን?” አልሁ።

11እንዲህም አልሁ፤ “ዳግም እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔርን በሕያዋን ምድር አላይም፤ ከእንግዲህም የሰውን ዘር አላይም፤ በዚህ ዓለም ከሚኖሩትም ጋር አልሆንም።

12ቤቴ እንደ እረኛ ድንኳን ተነቀለ፤ ከእኔም ተወሰደ፤ ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤ ከመጠቅለያ ቈርጦኛል፤ ከጠዋት እስከ ማታ ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

13እስከ ማለዳ በትዕግሥት ጠበቅሁ፤ እርሱ ግን እንደ አንበሳ ዐጥንቶቼን ሁሉ ሰባበረ፤ ከጠዋት እስከ ማታም ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

14እንደ ጨረባ፣ እንደ ሽመላም ተንጫጫሁ፤ እንደ ርግብ አልጐመጐምሁ፤ ዐይኖቼ ወደ ሰማይ በመመልከት ደከሙ፤ ጌታ ሆይ፤ ተጨንቄአለሁና ታደገኝ።”

15እንግዲህ ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፤ ራሱ ደግሞ ይህን አድርጓል፤ ስለ ነፍሴ ጭንቀት፣ ዕድሜዬን ሁሉ በትሕትና እሄዳለሁ።

16ጌታ ሆይ፤ ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ይኖራሉ፤ መንፈሴም እንዲሁ በእነዚህ ሕይወትን ያገኛል፤ ፈወስኸኝ፤ በሕይወትም አኖርኸኝ።

17እነሆ፤ በሥቃይ የተጨነቅሁት፣ ለጥቅሜ ሆነ፤ ከጥፋት ጒድጓድ፣ በፍቅርህ ጠበቅኸኝ፤ ኀጢአቴንም ሁሉ፣ ወደ ኋላህ ጣልኽ።

18ሲኦል አያመሰግንህም፤ ሞት አያወድስህም፤ ወደ ጒድጓድ የሚወርዱ፣ የአንተን ታማኝነት ተስፋ አያደርጉም።

19እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል። ስለ አንተ ታማኝነትም፣ አባቶች ለልጆቻቸው ይነግራሉ።

20እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜ ዘመናችን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።

21ኢሳይያስም፣ “የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳችሁ በዕባጩ ላይ አድርጉለት እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር።

22ሕዝቅያስም፣ “ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።

ማብራሪያ

38:1-8 በበሽታችን ሳለን ስንጸልይ፣ እግዚአብሔር እዚህ ለሕዝቅያስ የላከውን ዓይነት መልስ ባይልክልንም እንኳን፣ ቢሆንም ግን፣ በመንፈሱ አማካኝነት ደስ ይበላችሁ ብሎ ቢያዘን፣ ኃጢአታችን ይቅር እንደተባለልን ቢያረጋግጥልን፣ እንዲሁም እንኖርም እንሞትም የእርሱ እንደምንሆን ቢያረጋግጥልን፣ በከንቱ አንጸልይም። 2ነገሥት 20:1-11 ተመልከት።

38:9-22. እዚህ ላይ የሕዝቅያስን ምስጋና እናገኛለን። በበሽታችን ወቅት የምንቀበላቸውን ምሕረቶች ማስታወስ ለእኛ መልካም ነገር ነው። ሕዝቅያስ የነበረበትን ሁኔታ በዝርዝር አስቀምጧል። በዚህ ላይ አጽንዖት ሰጥቷል፤ 'እግዚአብሔርን ከእንግዲህ ወዲህ አላይም' በማለት። ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርን ከማገልገልና ከእርሱ ጋር ህብረት ከማድረግ ውጭ ለሌላ ዓላማ መኖር አይሻም። የአሁን መኖሪያችን እረኛ በጎጆው ውስጥ እንዳለ ነው፤ ደካማ፣ ትሑትና ቀዝቃዛ ማደሪያ ነው። እረኛም እንዳለው ሁሉ፣ በእኛም እንክብካቤ ሥር አደራ የተሰጠው ነገር አለ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል፡ አለው። አማርኛ ENGNIV In those days Hezekiah became ill and was at the point of death. The prophet Isaiah son of Amoz went to him and said, “… English BCV በቲ ዘመን እቱይ ሕዝቅያስ ንሞት ክሳዕ ዝበፅሕ ሓመመ። ነቢይ ኢሳይያስ ወዲ ኣሞፅ ከዓ ናብኡ መፂኡ፥ “እግዚኣብሄር ‘ክትመውት ኢኻ እምበር ብህይወት ኣይትነብርን ኢኻሞ፥ ቤትካ ኣመዓራሪ’ ይ… ትግርኛ GAZBIB Baras Hisqiyaas dhukkubsatee du'uu ga'ee ture; Isaayaas ilmi Amoz inni raajichi gara isaa dhaqee,“Ati in duuta malee hi… Afaan Oromoo BCV GIZ ወበውእት መዋዕል ደወየ ሕዝቂያስ ወበጽሐ ለሞት፤ ወመጽአ ኀቤሁ ኢሳይያስ ወልደ አሞጽ ነቢይ፤ ወይቤሎ፦ ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር፦ ሥራዕ ቤተከ እስመ ትመውት ወኢተሐዩ። giz GAZGAZ Baras Hisqiyaas dhukkubsatee du'uu ga'ee ture; Isaayaas ilmi Amoz inni raajichi gara isaa dhaqee,“Ati in duuta malee hi… Afaan Oromoo BCV aksum በቲ ዘመን እቱይ ሕዝቅያስ ንሞት ክሳዕ ዝበፅሕ ሓመመ። ነቢይ ኢሳይያስ ወዲ ኣሞፅ ከዓ ናብኡ መፂኡ፥ “እግዚኣብሄር ‘ክትመውት ኢኻ እምበር ብህይወት ኣይትነብርን ኢኻሞ፥ ቤትካ ኣመዓራሪ’ ይ… ትግርኛ SWAHSUV Siku hizo Hezekia aliugua, akawa katika hatari ya kufa; na Isaya nabii, mwana wa Amozi, akaenda kwa mfalme, akamwambia,… Kiswahili