ትንቢተ ኢሳይያስ 28

AMHNIVአማርኛ29 ጥቅሶች6:07 አዳምጥ
አዳምጥ 6:07 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ለኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል ለሆነች፣ በለመለመ ሸለቆ ዐናት ላይ ጒብ ብላ፣ የክብሩ ውበት ለሆነች ጠውላጋ አበባ፣ የወይን ጠጅ ለዘራቸው መኵራሪያ ለሆነች፣ ለዚያች ከተማ ወዮላት!

2እነሆ፤ ጌታ ኀያልና ብርቱ የሆነ ነገር አለው፤ ይህም እንደ በረዶ ወጀብ፣ እንደሚያጠፋ ዐውሎ ነፋስ፣ እንደ ኀይለኛ ማዕበል፣ እንደ ከባድ ዝናብ፣ በኀይል ወደ ምድር ይጥላታል።

3የኤፍሬም ሰካራሞች የመታበያ አክሊል፣ በእግር ይረገጣል።

4በለምለሙ ሸለቆ ዐናት ላይ ጒብ ብላ፣ የክብሩ ውበት የሆነች ጠውላጋ አበባ፣ ከመከር በፊት እንደ ደረሰች፣ ሰውም ድንገት አይቶ እንደሚቀጥፋት ወዲያውኑም እንደሚውጣት በለስ ትሆናለች።

5በዚያን ቀን የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ ለተረፈው ሕዝቡ፣ የክብር ዘውድ፣ የውበትም አክሊል ይሆናል።

6እርሱም በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጠው፣ የፍትሕ መንፈስ፣ ጦርን ከከተማዪቱ በር ላይ ለሚመልሱም፣ የኀይል ምንጭ ይሆናል።

7እነዚህም በወይን ጠጅ ይንገዳገዳሉ፤ በሚያሰክርም መጠጥ ይወላገዳሉ፤ ካህናቱና ነቢያቱ በሚያሰክር መጠጥ ተንገደገዱ፤ በወይን ጠጅ ነገር ተምታታባቸው፤ በሚያሰክር መጠጥ ተወላገዱ፤ ራእይ ሲያዩ ይስታሉ፤ ፍርድ ሲሰጡም ይሰናከላሉ።

8የማእድ ገበታቸው ሁሉ በትፋት ተሞልቶአል፤ ከትውኪያም የጸዳ ቦታ የለም።

9እነርሱም እንዲህ ይላሉ፤ “የሚያስተምረው ማንን ነው? መልእክቱን የሚያብራራውስ ለማን ነው? ወተት ለተዉት ሕፃናት? ወይስጡት ለጣሉት?

10በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፤ በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤ እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት ነውና።

11እንግዲያማ እግዚአብሔር፣ በባዕድ ልሳን በእንግዳ ቋንቋ ለዚህ ሕዝብ ይናገራል።

12እርሱ፣ “ይህቺ የዕረፍት ቦታ ናት፤ የደከመው ይረፍ፤ ይህቺ የእፎይታ ቦታ ናት” ያለው ለማን ነበር? እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም።

13ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፤ በደንብ ላይ ደንብ፣ በደንብ ላይ ደንብ፤ እዚህ ጥቂት እዚያ ጥቂት ይሆንባቸዋል። ይህ የሚሆንባቸው ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ፣ እንዲቈስሉና በወጥመድ እንዲያዙ፣ እንዲማረኩም ነው።

14ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ፣ እናንት ፌዘኞች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

15እናንት፣ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤ ከሲኦልም ጋር ስምምነት አድርገናል፤ ውሸትን መጠጊያችን፣ ሐሰትን መደበቂያችን አድርገናል፤ ታላቅ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ ሊነካን አይችልም” በማለት ታብያችኋል።

16ስለዚህ ልዑል እግዚእብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ የተፈተነ ድንጋይ፣ የመሠረት ድንጋይ፣ ለጽኑ መሠረት የሚሆን የከበረ የማእዘን ድንጋይ፣ በጽዮን አስቀምጣለሁ፤ በእርሱም የሚያምን አያፍርም።

17ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣ ጽድቅንም ቱንቢ አደርጋለሁ፤ ውሸት መጠጊያችሁን የበረዶ ዝናብ ይጠራርገዋል መደበቂያችሁንም ውሃ ያጥለቀልቀዋል።

18ከሞት ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይሻራል፤ ከሲኦልም ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት ይፈርሳል፤ ታላቁ መቅሠፍት እየጠራረገ ሲያልፍ፣ እናንተም ትጠራረጋላችሁ።

19በመጣ ቍጥር ይዞአችሁ ይሄዳል፤ ማለዳ ማለዳ፣ በቀንና በሌሊትም ይጠራርጋል።” ይህን ቃል ብታስተውሉ፣ ሽብር በሽብር በሆነ ነበር።

20እግር ዘርግቶ እንዳይተኛ ዐልጋው አጭር ነው፤ ሰውነትንም ለመሸፋፈን ብርድ ልብሱ ጠባብ ነው።

21እግዚአብሔር ሥራውን፣ አዎን ድንቅ ሥራውን ሊሠራ፣ ተግባሩን፣ እንግዳ የሆነ ተግባሩን ሊያከናውን፣ በፐራሲም ተራራ እንዳደረገው ይነሣል፣ በገባዖን ሸለቆ እንዳደረገው ይነሣሣል።

22እንግዲህ ፌዛችሁን አቁሙ፤ አለዚያ እስራታችሁ ይጸናባችኋል፤ ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ መላውን ምድር ለማጥፋት ያወጀውን ዐዋጅ ሰምቻለሁ።

23አድምጡ ድምፄን ስሙ፤ አስተውሉ ቃሌንም ስሙ።

24ገበሬ ሊዘራ መሬቱን ሲያዘጋጅ ያለ ማቋረጥ ያርሳልን? ጓሉን ሲከሰክስ፣ ዐፈሩን ሲያለሰልስ ይከርማልን?

25ዕርሻውን አስተካክሎ፣ ጥቍር አዝሙድና ከሙን አይዘራምን? ስንዴውንስ በትልሙ፣ ገብሱን በተገቢ ቦታው፣ አጃውንም በተመደበው ስፍራ አይዘራምን?

26አምላኩ ያስተምረዋል፤ ትክክለኛውንም መንገድ ያሳየዋል።

27ጥቍር አዝሙድ በመውቂያ መሣሪያ አይወቃም፤ ከሙን የሠረገላ መንኰራኵር አይሄድበትም፤ ጥቍር አዝሙድ በበትር፣ ከሙንም በዘንግ ይወቃል።

28እንጀራን ለመጋገር እህል ይፈጫል፤ ስለዚህ አንድ ሰው ለዘላለም እህል ሲወቃ አይኖርም። የመውቂያውን መንኰራኵር ቢያኼድበትም፣ ፈረሶቹ አይደፈጥጡትም።

29ይህ ሁሉ የሚሆነው በምክሩ ድንቅ በጥበቡ ታላቅ ከሆነው፣ ከሰራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

ማብራሪያ

28:1-4 ሰዎች የሚመኩበት፣ ምንም ያህል ቀላል ወይም ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ለእነርሱ እንደ ዘውድ ነው። ኩራት ግን የጥፋት መንደርደሪያ ነው። ሰካራሞች ምንኛ በሞኝነት ይሠራሉ! በወይን የተሸነፉት በሰይጣን ተሸንፈዋል፤ በዓለም ላይ ከመጠን በላይ መጠጣት የበለጠ ከባድ ባርነት የለም። ጤናቸው ይበላሻል፤ ሰዎች በሙያቸውና በንብረታቸው ይከስራሉ፤ ቤተሰቦቻቸውም በእርሱ ይጠፋሉ። ነፍሳቸውም ለዘላለም የመጥፋት አደጋ ላይ ናት፤ ይህ ሁሉ ደግሞ ዝቅተኛ ፍትወትን ለማርካት ሲባል ነው። በእግዚአብሔር ስም በሚጠሩ ሕዝብ ዘንድ፣ እንደ እስራኤል ባሉ፣ ከሌሎች ሁሉ የከፋ ነው። እርሱም እንደዚህ አላግባብ የሚጠቀሙበትን የተትረፈረፈ ነገር ሲወስድባቸው ጻድቅ ነው። የሚመኩበት የተትረፈረፈ ነገር ግን እንደሚደርቅ አበባ ነው። ልክ እንደ መጀመሪያው ፍሬ፣ እንደታየች እንደምትቀጠፍና እንደምትበላ።

28:5-15

ነቢዩ ቀጥሎ ወደ ይሁዳ ይመለሳል፣ እርሱም የሕዝቡ ቅሬታ ብሎ ይጠራቸዋል። በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ብቻ የሚመኩ ብቻ ደስተኞች ናቸው። ከዚህ የተነሳ ሕዝቡ ለእያንዳንዱ አገልግሎትና ለእያንዳንዱ ውጊያ ጥበብንና ኃይልን ያገኛሉ። ነገር ግን ቅዱስ እግዚአብሔር ከኃጢአተኛው ሰው ጋር የሚገናኘው በክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው። የሚያስተምሩት በወይን ጠጅ ሰክረውም ይሁን፣ ስለ መሲሑ መንግሥትና ድነት በሐሰት ትምህርቶችና ሐሳቦች ሰክረው ይሁን፣ እነርሱ ራሳቸው ብቻ አይስቱም፣ ነገር ግን ብዙዎችንም ያሳስታሉ። እነዚህ ሰዎች ባስተማሩባቸው ቦታዎች ሁሉ በስህተቶች ተሞልተዋል። በእግዚአብሔር ነገሮች ለመገንዘብ፣ በተሻለ ሁኔታ እንድንረዳቸው፣ ተመሳሳይ ትእዛዝ እና ተመሳሳይ መስመር ብዙ ጊዜ ሊደገምልን ያስፈልጋል። እግዚአብሔር በቃሉ፣ በእውነት ለጥቅማችን ወደሆነው ይጠራናል። የእግዚአብሔር አገልግሎት ከኃጢአት አገልግሎት ለደከሙት ብቸኛው እውነተኛ ዕረፍት ነው፣ እናም ከጌታ ኢየሱስ ቀላል ቀንበር በታች ካልሆነ በስተቀር ምንም የሚያድስ ነገር የለም። ይህ ሁሉ በሕዝቡ ላይ ብዙም ውጤት አልነበረውም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG ለኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል፥ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ በወፍራም ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮ! አማርኛ ENGNIV Woe to that wreath, the pride of Ephraim's drunkards, to the fading flower, his glorious beauty, set on the head of a f… English BCV ንሰካራማት ኤፍሬም ናይ ትዕቢት ኣኽሊል ንዝኾነት፥ ኣብ ልዕሊ ዝለምለመ ለሰ ጉብ ኢላ፥ ናይ ክብሩ መልክዕ ዝኾነት ፅምልውቲ ዕምበባ፥ ብመስተ ወይኒ ዝተሰነፉ መመክሒት ንዝኾነት ወይለኣ! ትግርኛ GAZBIB Gonfoo isa namoota Efreem warra machooftuudhaa fi of jajuu ta'eef, isa daraaraan isaa inni miidhagaan irraa coollageef,… Afaan Oromoo BCV GIZ አሌ ሎ ለአክሊለ ኀሳር ዐሳቢሁ ለኤፍሬም ጽጌ ዘይወድቅ እምትርሲቱ ውስተ ርእሰ ደብር ግዙፍ እለ ይሰክሩ ዘእንበለ ወይን። giz GAZGAZ Gonfoo isa namoota Efreem warra machooftuudhaa fi of jajuu ta'eef, isa daraaraan isaa inni miidhagaan irraa coollageef,… Afaan Oromoo BCV aksum ንሰካራማት ኤፍሬም ናይ ትዕቢት ኣኽሊል ንዝኾነት፥ ኣብ ልዕሊ ዝለምለመ ለሰ ጉብ ኢላ፥ ናይ ክብሩ መልክዕ ዝኾነት ፅምልውቲ ዕምበባ፥ ብመስተ ወይኒ ዝተሰነፉ መመክሒት ንዝኾነት ወይለኣ! ትግርኛ SWAHSUV Ole wa taji ya kiburi ya walevi wa Efraimu, na ua la uzuri wa fahari yake linalonyauka, lililo kichwani mwa bonde linal… Kiswahili