ትንቢተ ኢሳይያስ 22

AMHNIVአማርኛ25 ጥቅሶች4:40 አዳምጥ
አዳምጥ 4:40 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ንግር፤ እስቲ ምን ቢጨንቃችሁ ነው፤ ሁላችሁም ሰገነት ላይ የወጣችሁት?

2አንቺ ጫጫታ የሞላብሽ ከተማ፤ የውካታና የፈንጠዝያ ከተማ ሆይ፤ የተገደሉብሽ በሰይፍ የተሠዉ አይደሉም፤ በጦርነትም አልሞቱም።

3መሪዎችሽ በሙሉ በአንድ ላይ ሸሽተዋል፤ ቀስት እንኳ ሳያነሡ ተማርከዋል፤ ጠላት ገና በሩቅ ሳለ የሸሻችሁ ሁሉ፣ ተይዛችሁ በአንድነት ታስራችኋል።

4ስለዚህ፣ “ከእኔ ራቁ፤ አምርሬ ላልቅስበት፣ ስለ ሕዝቤ ጥፋት፣ ልታጽናኑኝ አትሞክሩ” አልሁ።

5እግዚአብሔር የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በራእይ ሸለቆ፣ የመጯጯኺያ የመረገጥና የሽብር፣ ቅጥሮችን የማፈራረስ፣ ወደ ተራሮችም የሚጮኽበት ቀን አለው።

6ኤላም የፍላጻ ሰገባ፣ ፈረሷንና ሠረገላዋን አዘጋጀች፤ ቂርም ጋሻዋን አነገበች

7መልካሞቹ ሸለቆዎችሽ በሠረገሎች ተሞልተዋል፤ ፈረሰኞችም በከተማዪቱ በሮች ላይ ቆመዋል፤

8የይሁዳን መከላከያዎች ገልጧል። በዚያን ቀን በዱር ግምጃ ቤት የነበረውን፣ የጦር መሣሪያ ተመለከትህ፤

9የዳዊት ከተማ፣ ብዙ ፍርስራሾች እንዳሉበት አያችሁ፤ በታችኛውም ኵሬ፣ ውሃ አጠራቀማችሁ።

10በኢየሩሳሌም ያሉትን ቤቶች ቈጠራችሁ፤ ቅጥሩን ለመጠገንም ቤቶቹን አፈረሳችሁ።

11ለጥንቱ ኵሬ ውሃ የሚሆን፣ በሁለቱ ቅጥሮች መካከል ውሃ ማጠራቀሚያ ሠራችሁ፤ ነገር ግን ይህን ያደረገውን አልተመለከታችሁም፤ ቀድሞ ዐቅዶ የሠራውንም አላስታወሳችሁም።

12በዚያን ቀን ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንድታለቅሱና በዋይታ እንድትጮኹ፣ ጠጒራችሁን እንድትነጩ ማቅም እንድትለብሱ ጠራችሁ።

13ነገር ግን እነሆ፤ ተድላና ደስታ፣ ፍሪዳ መጣልና ሙክት ማረድ፣ ሥጋ መብላትና የወይን ጠጅ መጠጣት አለ፤ “እንብላ እንጠጣ ነገ እንሞታለንና” አላችሁ።

14የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን ገለጠልኝ፤ እንዲህም ሲል በጆሮዬ ሰማሁ፤ “ይህ ኀጢአት እስከምትሞቱበት ቀን ድረስ አይሰረይላችሁም” ይላል ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

15ጌታ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሂድና ይህን መጋቢ፣ የቤቱንም ኀላፊ ሳምናስን እንዲህ በለው፤

16‘እዚህ ምን ታደርጋለህ? በዚህ ስፍራ ለራስህ መቃብርን እንድታዘጋጅ፣ በከፍታውም ላይ መቀበሪያህን እንድትወቅር፣ ሬሳህ የሚያርፍበትንም ዐለት እንድትጠርብ ማን ፈቀደልህ?’

17አንተ ኀያል ሰው ሆይ፤ ተጠንቀቅ፤ እግዚአብሔር አጥብቆ ሊይዝህ፣ በእጆቹም ጨብጦ ሊወረውርህ ነው።

18አዙሮ አዙሮ እንደ ሩር አጡዞ፣ ወደ ሰፊ አገር ይወነጭፍሃል፤ አንተ የጌታህ ቤት ዕፍረ በዚያ ትሞታለህ፤ የክብር ሠረገሎችህም እዚያ ይቀራሉ።

19ከማዕረግህ አወርድሃለሁ፤ ከኀላፊነትህም ትባረራለህ።

20“በዚያን ቀን አገልጋዬን፣ የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፤

21መጐናጸፊያህን አለብሰዋለሁ፤ መታጠቂያህን አስታጥቀዋለሁ፤ ሥልጣንህንም አስረክበዋለሁ። እርሱም በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ፣ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል።

22የዳዊትን ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አደርጋለሁ፤ እርሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋም፤ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍትም።

23በአስተማማኝ ስፍራ እንደ ካስማ እተክለዋለሁ፤ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል።

24የቤተ ሰቡ ክብር፣ ልጅና የልጅ ልጅ፣ እንዲሁም ከማሰሮ ጀምሮ እስከ ጋን ድረስ ያለ የቤት ዕቃ ሁሉ በርሱ ላይ ይንጠለጠላል።

25“በዚያ ቀን” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ “በአስተማማኝ ስፍራ የተተከለ ካስማ ይነቀላል፤ ተሰብሮም ይወድቃል፤ በእርሱም ላይ የተንጠለጠለው ሸክም ወድቆ ይከሰከሳል፤” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአልና።

ማብራሪያ

22:1-7 ኢየሩሳሌም እንዲህ ባለ ፍርሃት ውስጥ የምትገኘው ለምንድን ነው? የተገደሉት ሰዎች በሰይፍ ሳይሆን በራብ የሞቱ ናቸው፤ ወይም፣ በፍርሃት የተገደሉ፣ ተስፋ የቆረጡ ናቸው። መሪዎቻቸው ሸሽተው ነበር፣ ነገር ግን ተይዘዋል። የእግዚአብሔር አገልጋዮች፣ ለኃጢአተኞች ስለሚመጡት መከራዎች አስቀድመው የሚያዩና የሚያስጠነቅቁ፣ በዚህ እይታ ተነክተዋል። ነገር ግን በኃይል የተያዘች ከተማ አስፈሪ ሁኔታዎች ሁሉ የቁጣው ቀን አስፈሪነትን በደካማ መንገድ ያመለክታሉ።

22:8-14 የይሁዳ ድካም አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ገሃድ ሆነ። አሁን ደግሞ ሥጋዊ መታመናቸውና ሥጋዊ ደኅንነታቸው ተገለጠ። ወደ ግንብ ምሽጎቻቸው ተመለከቱ። ለከተማይቱ ውሃ መኖሩንም አረጋገጡ። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች እግዚአብሔርን አልተመለከቱትም። ባደረጉትም ነገር ለክብሩ ግድ አላደረጉም። በጥረታቸውም ላይ ለበረከት በእርሱ አልተመኩም። ምክንያቱም ማንኛውም ፍጥረት እግዚአብሔር እንደሚያደርገው ለእኛ ይሆናል፤ ስለ እርሱም ልናመሰግነውና ለእርሱ ልንጠቀምበት ይገባል። እነርሱም እግዚአብሔርን በመቃወማቸው ለቁጣውና ለፍርዱ ታላቅ ንቀት አሳዩ። የእግዚአብሔር ዓላማ እነርሱን ማዋረድና ወደ ንስሐ መመለስ ነበር። እነርሱ ግን ከዚህ በተቃራኒ ተራመዱ። ከዚህ በኋላ ስላለው ሌላ ሕይወት ተግባራዊ አለማመን የብዙ የሰው ዘር ክፍል ኃጢአት፣ ውርደትና ጥፋት በሆኑት በሥጋዊ ደኅንነትና በአውሬያዊ የስሜት ምኞት ስር የሚገኝ ነው። እግዚአብሔርም በዚህ ተቈጣ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6