ትንቢተ ኢሳይያስ 22

AMHEVGአማርኛ25 ጥቅሶች4:14 አዳምጥ
አዳምጥ 4:14 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ስለ ራእይ ሸለቆ የተነገረ ሸክም። እናንተ ሁላችሁ ወደ ሰገነት መውጣታቸሁ ምን ሆናችኋል?

2ጩኸትና ፍጅት የተሞላብሽ ከተማ፥ ደስታ ያለሽ ከተማ ሆይ፥ በአንቺ ውስጥ የተገደሉት በሰይፍ የተገደሉ አይደሉም፥ በሰልፍም የሞቱ አይደሉም።

3አለቆችሽ ሁሉ በአንድነት ሸሹ፥ ያለ ቀስትም ተማረኩ፤ ከሩቅ ሸሽተው ከአንቺ ዘንድ የተገኙት ሁሉ በአንድነት ታሰሩ።

4ስለዚህ፦ ፊታችሁን ከእኔ ዘንድ አርቁ፤ መራራ ልቅሶ አለቅሳለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ጥፋት ታጽናኑኝ ዘንድ አትድከሙ፡ አልሁ።

5ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የድንጋጤና የመረገጥ የድብልቅልቅም ቀን፥ የቅጥርም መፍረስ ወደ ተራራም መጮኽ በራእይ ሸለቆ ውስጥ ሆኖአል።

6ኤላምም ከሰረገለኞችና ከፈረሰኞች ጋር ሆኖ አፎቱን ተሸከመ፥ ቂርም ጋሻውን ገለጠ።

7መልካሞቹንም ሸለቆችሽን ሰረገሎች ሞሉባቸው፥ ፈረሰኞችም መቆሚያቸውን በበር ላይ አደረጉ።

8የይሁዳንም መጋረጃ ገለጠ፤ በዚያም ቀን በዱር ቤት የነበረውን የጦር ዕቃ ተመለከትህ፥

9የዳዊትም ከተማ ፍራሾች እንደ በዙ አይታችኋል፥ የታችኛውንም ኵሬ ውኃ አከማችታችኋል፥

10የኢየሩሳሌምን ቤቶች ቈጠራችሁ ቅጥሩንም ለማጥናት ቤቶችን አፈረሳችሁ።

11በአሮጌው ኵሬ ላለው ውኃ በሁለቱ ቅጥር መካከል መከማቻ ሠራችሁ፤ ይህን ያደረገውን ግን አልተመለከታችሁም፥ ቀድሞ የሠራውንም አላያችሁም።

12በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ።

13እነሆም፥ ሐሜትና ደስታ በሬውንና በጉንም ማረድ ሥጋንም መብላት የወይን ጠጅንም መጠጣት ሆነዋል፤ እናንተ፦ ነገ እንሞታለንና እንብላ እንጠጣ፡ ብላችኋል።

14ይህም ነገር በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ፦ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም፡ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

15የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በቤቱ ውስጥ ወደ ተሾመው ወደዚህ አዛዥ ወደ ሳምናስ ሂድ እንዲህም በለው፦

16መቃብር በዚህ ያስወቀርህ ከፍ ባለው ስፍራ መቃብር ያሰራህ በድንጋይም ውስጥ ለራስህ መኖርያ ያሳነጽህ በዚህ ምን አለህ? በዚህስ በአንተ ዘንድ ማን አለ?

17እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይል ወርውሮ ይጥልሃል፥ አጠንክሮም ይጨብጥሃል።

18ጠቅልሎም ያንከባልልሃል ወደ ሰፊይቱም ምድር እንደ ኳስ ይጥልሃል፤ አንተ የጌታህ ቤት እፍረት! በዚያ ትሞታለህ በዚያም የክብርህ ሰረገላዎች ይሆናሉ።

19ከአዛዥነት ሥራህ አሳድድሃለሁ፥ ከሹመትህም ትሻራለህ።

20በዚያም ቀን ባሪያዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን እጠራለሁ፥

21መጐናጸፊያህንም አለብሰዋለሁ፥ በመታጠቂያህም አስታጥቀዋለሁ፥ ሹመትህንም በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለይሁዳም ቤት አባት ይሆናል።

22የዳዊትንም ቤት መክፈቻ በጫንቃው ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ይከፍታል የሚዘጋም የለም እርሱም ይዘጋል የሚከፍትም የለም።

23በታመነም ስፍራ እንደ ችንካር እተክለዋለሁ፥ ለአባቱም ቤት የክብር ዙፋን ይሆናል።

24የአባቱንም ቤት ክብር ሁሉ ልጆቹንም የልጅ ልጆቹንም፥ ከጽዋ ዕቃ ጀምሮ እስከ ማድጋ ዕቃ ድረስ፥ ታናናሹን ዕቃ ሁሉ ይሰቅሉበታል።

25በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ በታመነው ስፍራ የተከለው ችንካር ይወልቃል ተሰብሮም ይወድቃል፥ በእርሱም ላይ የተሰቀለው ሸክም ይጠፋል እግዚአብሔር ተናግሮአልና።

ማብራሪያ

22:1-7 ኢየሩሳሌም እንዲህ ባለ ፍርሃት ውስጥ የምትገኘው ለምንድን ነው? የተገደሉት ሰዎች በሰይፍ ሳይሆን በራብ የሞቱ ናቸው፤ ወይም፣ በፍርሃት የተገደሉ፣ ተስፋ የቆረጡ ናቸው። መሪዎቻቸው ሸሽተው ነበር፣ ነገር ግን ተይዘዋል። የእግዚአብሔር አገልጋዮች፣ ለኃጢአተኞች ስለሚመጡት መከራዎች አስቀድመው የሚያዩና የሚያስጠነቅቁ፣ በዚህ እይታ ተነክተዋል። ነገር ግን በኃይል የተያዘች ከተማ አስፈሪ ሁኔታዎች ሁሉ የቁጣው ቀን አስፈሪነትን በደካማ መንገድ ያመለክታሉ።

22:8-14 የይሁዳ ድካም አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ገሃድ ሆነ። አሁን ደግሞ ሥጋዊ መታመናቸውና ሥጋዊ ደኅንነታቸው ተገለጠ። ወደ ግንብ ምሽጎቻቸው ተመለከቱ። ለከተማይቱ ውሃ መኖሩንም አረጋገጡ። ነገር ግን በእነዚህ ሁሉ ዝግጅቶች እግዚአብሔርን አልተመለከቱትም። ባደረጉትም ነገር ለክብሩ ግድ አላደረጉም። በጥረታቸውም ላይ ለበረከት በእርሱ አልተመኩም። ምክንያቱም ማንኛውም ፍጥረት እግዚአብሔር እንደሚያደርገው ለእኛ ይሆናል፤ ስለ እርሱም ልናመሰግነውና ለእርሱ ልንጠቀምበት ይገባል። እነርሱም እግዚአብሔርን በመቃወማቸው ለቁጣውና ለፍርዱ ታላቅ ንቀት አሳዩ። የእግዚአብሔር ዓላማ እነርሱን ማዋረድና ወደ ንስሐ መመለስ ነበር። እነርሱ ግን ከዚህ በተቃራኒ ተራመዱ። ከዚህ በኋላ ስላለው ሌላ ሕይወት ተግባራዊ አለማመን የብዙ የሰው ዘር ክፍል ኃጢአት፣ ውርደትና ጥፋት በሆኑት በሥጋዊ ደኅንነትና በአውሬያዊ የስሜት ምኞት ስር የሚገኝ ነው። እግዚአብሔርም በዚህ ተቈጣ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6