1ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹን ሁሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባችሁ እነግራችሁ ዘንድ ተሰብሰቡ።
2“እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ ተሰብሰቡና ስሙ፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ፤
3“ሮቤል፣ አንተ የበኵር ልጄ ነህ፤ ኀይሌና የጒብዝናዬም መጀመሪያ፤ በክብር ትልቃለህ በኀይልም ትበልጣለህ።
4እንደ ውሃ የዋለልህ ነህና እልቅና አይኖርህም፤ የአባትህን መኝታ ደፍረሃል፤ ምንጣፌንም አርክሰሃል።
5ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች፣ ሰይፎቻቸው የዐመፅ መሣሪያዎች ናቸው።
6ወደ ሸንጎአቸው አልግባ፤ ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፤ በቍጣ ተነሣሥተው ሰዎችን ገድለዋል፤ የበሬዎችንም ቋንጃ እንዳሻቸው ቈራርጠዋል።
7እጅግ አስፈሪ የሆነ ቍጣቸው፣ ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤ በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፤ በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ።
8“ይሁዳ፣ ወንድሞችህ ይወድሱሃል፤ እጅህም የጠላቶችህን ዐንገት ዐንቆ ይይዛል፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይሰግዱልሃል።
9“አንተ የአንበሳ ደቦል ይሁዳ፤ ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣ እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ በምድርም ላይ ይተኛል፤ እንደ እንስት አንበሳም ያደባል፤ ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል?
10በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል። ገዥነት የሚገባው እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል።
11አህያውን በወይን ግንድ፣ ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጐናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል።
12ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።
13“ዛብሎን፣ በባሕር ዳር ይኖራል፤ የመርከቦች መጠጊያም ይሆናል፤ ወሰኑም እስከ ሲዶና ይደርሳል።
14“ይሳኮር፣ ዐጥንተ ብርቱ አህያ፣ በጭነት መካከል የሚተኛ፣
15ማረፊያ ቦታው መልካም፣ ምድሪቱም አስደሳች መሆኗን ሲያይ፣ ትከሻውን ለሸክም ያመቻቻል፤ ተገድዶም ያገለግላል።
16“ዳን፣ ከእስራኤል ነገዶች እንደ አንዱ ሆኖ፣ በራሱ ሕዝብ ላይ ይፈርዳል።
17ዳን የመንገድ ዳር እባብ፣ የመተላለፊያም መንገድ እፉኝት ነው፤ ጋላቢው የኋሊት እንዲወድቅ፣ የፈረሱን ሰኮና ይነክሳል።
18“እግዚአብሔር ሆይ (ያህዌ)፤ ማዳንህን እጠባበቃለሁ።
19“ጋድን ወራሪዎች አደጋ ይጥሉበታል፤ እርሱ ግን ዱካቸውን ተከታትሎ ብድሩን ይመልሳል።
20“አሴር ማእደ ሰፊ ይሆናል፤ ለነገሥታትም የሚስማማ ምግብ ያቀርባል።
21“ንፍታሌም ነጻ እንደ ተለቀቀች፣ የሚያማምሩም ግልገሎች እንደምትወልድ ሚዳቋ ነው።
22ዮሴፍ፤ ፍሬያማ የወይን ተክል፣ በምንጭ ዳር የተተከለ ወይን ነው። ሐረጎቹ ቅጥርን ያለብሳሉ።
23ቀስተኞች በጭካኔ አጠቁት፤ በጥላቻም ነደፉት።
24ነገር ግን በያዕቆብ ኀያል አምላክ ክንድ፣ እረኛው በሆነው በእስራኤል ዐለት፣ ቀስቱ ጸና፤ ጠንካራ ክንዱም ቀለጠፈ።
25አንተን በሚረዳህ በአባትህ አምላክ፣ በሚባርክህ፣ ሁሉን ማድረግ በሚችል አምላክ፣ ከላይ ከሰማይ በሚገኝ ረድኤት፣ ከምድር ጥልቅ በሚገኝ በረከት፣ ከማሕፀንና ከጡት በሚገኝ ምርቃት ይባርክሃል።
26ከጥንት ተራሮች በረከት፣ ከዘላለም ኰረብቶች ምርቃት ይልቅ፣ የአባትህ በረከት ይበልጣል፤ ይኸ ሁሉ በዮሴፍ ራስ ላይ ይውረድ፤ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነውም ግንባር ላይ ይረፍ።
27ብንያም፣ ነጣቂ ተኵላ ነው፤ ያደነውን ማለዳ ይበላል፤ የማረከውን ማታ ይከፋፈላል።
28እነዚህ ሁሉ ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው። ይህም እያንዳንዳቸውን ተገቢ በሆነው በረከት አባታቸው ሲባርካቸው የተናገረው ቃል ነው።
29ከዚህ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ወገኖቼ የምሰበሰብበት ጊዜ ደርሶአል፤ በኬጢያዊው በኤፍሮን ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ዘንድ ቅበሩኝ፤
30ይህ በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ በማክፌላ ዕርሻ ውስጥ ያለው ዋሻ፣ የመቃብር ቦታ እንዲሆን አብርሃም ከኬጢያዊው ኤፍሮን ላይ ከነዕርሻ ቦታው የገዛው ነው።
31በዚያ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ተቀብረዋል፤ በዚያ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ተቀብረዋል፤
32እኔም ልያን የቀበርኋት እዚያው ነው። ዕርሻውና ዋሻው የተገዙት ከኬጢያውያን ላይ ነው።”
33ያዕቆብ እነዚህን ቃላት ለልጆቹ ተናግሮ እንዳበቃ፣ እግሮቹን በዐልጋው ላይ ሰብስቦ፣ የመጨረሻ ትንፋሹን ተነፈሰ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ።