1የኖኅ ልጆች የሴም፣ የካምና የያፌት ትውልድ ይህ ነው፤ እነርሱም ራሳቸው ከጥፋት ውሃ በኋላ ወንዶች ልጆችን ወለዱ።
2የያፌት ልጆች፦ ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ቶቤል፣ ሞሳሕ፣ ቴራስ ናቸው።
3የጋሜር ልጆች፦ አስከናዝ፣ ራፋት፣ ቴርጋማ ናቸው።
4የያዋን ልጆች፦ ኤሊሳ፣ ተርሴስ፣ ኪቲም፣ ሮዲኢ ናቸው።
5ከእነዚህም በየነገዳቸው፣ በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው ተከፋፍለው በባሕር ዳርና በደሴቶች፣ በየምድራቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ወጡ።
6የካም ልጆች፦ ኩሽ፣ ምጽራይም፣ ፉጥ፣ ከነዓን ናቸው።
7የኩሽ ልጆች፦ ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራዕማ፣ ሰበቅታ ናቸው። የራዕማ ልጆች፦ ሳባ፣ ድዳን ናቸው።
8ኩሽ የናምሩድ አባት ነበረ፤ ናምሩድም በምድር ላይ ኀያል ሰው እየሆነ ሄደ።
9በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ብርቱ አዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንደ ናምሩድ ብርቱ አዳኝ” ይባል ነበር።
10የግዛቱም የመጀመሪያ ከተሞች፦ ባቢሎን፣ ኦሬክ፣ አርካድና ካልኔ ናቸው፤ እነዚህ በሰናዖር ምድር ነበሩ።
11ከዚያም ምድር ወደ አሦር ወጥቶ ነነዌን፣ ረሆቦትን፣ ካለህን
12እንዲሁም በነነዌና በካለህ መካከል ሬስን ቈረቈረ፤ ታላቁንም ከተማ መሠረተ።
13ምጽራይም፦ የሉዳማውያን፣ የዕሚማውያን፣ ላህቢያውያን፣ የነፍታሌማውያን፣
14የፈትሩሲማውያን፣ ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው የኮስሉሂማውያን፣ የቀፍቶሪማውያን አባት ነበረ።
15ከነዓንም፦ የበኵር ልጁ የሲዶን፣ የኬጢያውያን፣
16የኢያቡሳውያን፣ የአሞራውያን፣ የጌርሳውያን አባት ነበረ፤
17እንዲሁም የኤዊያውያን፣ የዑርኬዋናውያን፣ የሲኒያውያን፣
18የአራዴዎናውያን፣ የሰማሪናውያን፣ የአማቲያውያን አባት ነበረ። ከጊዜ በኋላ የከነዓን ጐሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ፤
19የከነዓን ወሰን ከሲዶና አንሥቶ በጌራራ በኩል እስከ ጋዛ ይደርሳል፤ ከዚያም በሰዶም በኩል ገሞራን፣ አዳማንና ሰቦይን ይዞ እስከ ላሣ ይዘልቃል።
20እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የካም ዝርያዎች ናቸው።
21ለያፌት ታላቅ ወንድም ለሴም ደግሞ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የዔ ቦር ልጆች ሁሉ ቅደመ አያት ነው።
22የሴም ልጆች፦ ኤላም፣ አሦር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ፣ አራም ናቸው።
23የአራም ልጆች፦ ዑፅ፣ ሁል፣ ጌቴር፣ ሞሶሕ ናቸው።
24አርፋክስድ ሳላን ወለደ፤ ሳላም ዔቦርን ወለደ።
25ለዔቦርም ሁለት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ አንደኛው ልጅ በዘመኑ ምድር ተከፍላ ስለ ነበር ፍሌቅ ተባለ፤ ወንድሙም ዮቅጣን ተባለ።
26ዮቅጣንም፦ የኤልሞሳድ፣ የሣሌፍ፣ የሐስረ ሞት፣ የያራሕ፣
27የሀደራም፣ የአውዛል፣ የደቅላ አባት ነበረ፤
28እንዲሁም የዖባል፣ የአቢማኤል፣ የሳባ፣
29የኦፊር፣ የኤውላጥ፣ የዮባል አባት ነበረ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ናቸው።
30መኖሪያ ስፍራቸውም እስከ ሶፋር ድረስ ይዘልቃል።
31እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የሴም ዝርያዎች ናቸው።
32የኖኅ ወንዶች ልጆች ጐሣዎች እንደ ትውልዳቸው በየነገዳቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውሃ በኋላ ሕዝቦች በምድር ላይ የተሠራጩት ከእነዚሁ ነው።