ትንቢተ ሕዝቅኤል 20

AMHEVGአማርኛ49 ጥቅሶች9:13 አዳምጥ
አዳምጥ 9:13 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እንዲህም ሆነ፤ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ።

2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

3የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ሽማግሌዎች ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔን ትጠይቁ ዘንድ መጥታችኋልን? እኔ ሕያው ነኝና በእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

4ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ በውኑ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኵሰት አስታውቃቸው።

5እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ለያዕቆብም ቤት ዘር በማልሁበት ቀን በግብፅም ምድር በተገለጥሁላቸውና፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፡ ብዬ በማልሁላቸው ጊዜ፥

6በዚያ ቀን ከግብፅ ምድር ወዳዘጋጀሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው፤

7እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት ይጣል፥ በግብፅም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፡ አልኋቸው።

8እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኵሰት አልጣለም የግብፅንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ፦ በግብፅ ምድር መካከል ቍጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፡ አልሁ።

9ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብፅም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።

10ከግብፅም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው።

11ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው።

12የምቀድሳቸውም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው።

13ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ፦ አጠፋቸው ዘንድ ቍጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ፡ አልሁ።

14ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።

15ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው።

16ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፤ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና።

17ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም።

18ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ፥ ወጋቸውንም አትጠብቁ፥ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ።

19እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም።

20ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ።

21ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቍጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ፡ አልሁ።

22ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።

23ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤

24ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና።

25ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው።

26እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው።

27ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመፅ አስቈጡኝ።

28እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቈጣኝን ቍርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቍርባናቸውን አፈሰሱ።

29እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድር ነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ተጠርቶአል።

30ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኵሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን?

31ቍርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤

32ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን፡ የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም።

33እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

34ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ።

35ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ።

36በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

37ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤

38ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ፤ ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

39ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሂዱ፥ ከዚህም በኋላ ትሰሙኝ ዘንድ ባትወድዱ ሁላችሁ ጣዖቶቻችሁን አምልኩ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን አታረክሱም።

40በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው በምድሩ ላይ ያመልኩኛል፤ በዚያም እቀበላቸዋለሁ፥ በዚያም ቍርባናችሁን በኵራታችሁንም የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እፈልጋለሁ።

41ከአሕዛብም ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፥ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ።

42ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

43በዚያም የረከሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ ስለ ሠራችሁትም ክፋታችሁ ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።

44የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

45የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦

46የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ደቡብ አቅና ወደ ደቡብም ተናገር በደቡብም ባለው ዱር ላይ ትንቢት ተናገር፤

47ለደቡብም ዱር፦ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በአንተ ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፤ በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ የሚቃጠል ነበልባል አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ፊት ሁሉ ይቃጠልበታል።

48እኔም እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያያል፥ እርሱም አይጠፋም፡ በለው።

49እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፦ ይህ ምሳሌን የሚመስል አይደለምን? ብለዋል፡ አልሁ።

ማብራሪያ

20:1-9. በኃጢአት ለመቀጠል የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚለምኑት፣ ያውም ስለእርሱ መከራ እየደረሰባቸው ሳለ እንኳን፣ እነዚያ ልቦች እጅግ የደነደጉ ናቸው፤ ቁጥርን ተመልከት።

20:10-26. የእስራኤል በምድረበዳ የነበረው ታሪክ በአዲስ ኪዳንም ሆነ በብሉይ ኪዳን ለማስጠንቀቂያነት ተጠቅሷል። እግዚአብሔር ለእነርሱ ታላላቅ ነገሮችን አደረገ። ሕግን ሰጣቸው፣ የጥንቱን የሰንበትን ቀን የመጠበቅ ሥርዓትም አሳደሰ። ሰንበታት መብቶች ናቸው፤ የእርሱ ሕዝብ መሆናችንንም የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። የዕለቱን ግዴታችንን ብንፈጽም፣ ለመጽናናታችን ሲሆን፣ እኛን ቅዱስ የሚያደርገን፣ ይኸውም በዚህ ምድር እውነተኛ ብፁዕ የሚያደርገን፣ እንዲሁም ወደፊት ብፁዕ፣ ማለትም ፍጹም ቅዱስ ለመሆን የሚያዘጋጀን ጌታ እንደሆነ እንረዳለን። እስራኤላውያን አመፁ፣ በራሳቸው ላይ ባመጡትም ፍርድ ውስጥ ተተዉ። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የራሱ ቅጣት እንዲሆን ያደርጋል፤ ሆኖም እርሱ የኃጢአት ፈጣሪ አይደለም። ሰዎችን ለመከራ ለማዳረግ የራሳቸውን ክፉ ምኞትና ስሜት እንዲከተሉ ከመተው በቀር ከዚህ በላይ አያስፈልግም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

ENGNIV In the seventh year, in the fifth month on the tenth day, some of the elders of Israel came to inquire of the Lord, and… English BCV ኮነ ኸዓ፥ ኣብታ ሻውዐይቲ ዓመት፥ ኣብቲ ሓምሻይ ወርሒ፥ ኣብ ዓስረይቲ መዓልቲ፥ ብዙሓት ሰባት ካብ ዓበይቲ እስራኤል፥ ንእግዚኣብሄር ክጥይቑ መፂኦም ኣብ ቅድመይ ተቐመጡ። ትግርኛ GAZBIB Kana booddees waggaa torbaffaatti, ji'a shanaffaatti, ji'icha keessaa guyyaa kurnaffaatti, jaarsolii Israa'el keessaa j… Afaan Oromoo BCV GIZ ወእምዝ አመ ሳብዕ ዓመት በኃምስ ወርዓኅ አመ ዓሡር ሠርቅ መጽኡ ኀቤየ እደው እምረበናተ ቤተ እስራኤል ይስአልዎ ለእግዚአብሔር ወነበሩ ቅድመ ገጽየ። giz GAZGAZ Kana booddees waggaa torbaffaatti, ji'a shanaffaatti, ji'icha keessaa guyyaa kurnaffaatti, jaarsolii Israa'el keessaa j… Afaan Oromoo BCV aksum ኮነ ኸዓ፥ ኣብታ ሻውዐይቲ ዓመት፥ ኣብቲ ሓምሻይ ወርሒ፥ ኣብ ዓስረይቲ መዓልቲ፥ ብዙሓት ሰባት ካብ ዓበይቲ እስራኤል፥ ንእግዚኣብሄር ክጥይቑ መፂኦም ኣብ ቅድመይ ተቐመጡ። ትግርኛ AMHNIV በሰባተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ። አማርኛ SWAHSUV Ikawa katika mwaka wa saba, mwezi wa tano, siku ya kumi ya mwezi, baadhi ya wazee wa Israeli walikuja ili kuuliza kwa B… Kiswahili