ትንቢተ ሕዝቅኤል 20

AMHNIVአማርኛ49 ጥቅሶች10:35 አዳምጥ
አዳምጥ 10:35 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በሰባተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ።

2የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

3“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሐሳቤን ልትጠይቁ መጣችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ ከእኔ ጠይቃችሁ እንድትረዱ አልፈቅድም’፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

4“የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጽላቸው፤

5እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፣ ለያዕቆብ ቤት ዘር እጄን አንሥቼ ማልሁላቸው፤ በግብፅም ራሴን ገለጥሁላቸው። እጄንም አንሥቼ፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።

6በዚያን ቀን፣ ከግብፅ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው።’

7እኔም፣ ‘እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብፅ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።

8“ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብፅንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብፅ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።

9ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብፅ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።

10ስለዚህ ከግብፅ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው።

11ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው።

12ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።

13“ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።

14ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።

15ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤

16ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋር ተጣብቆአልና።

17እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም።

18ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ።

19እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ።

20በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁም ታውቃላችሁ።

21“ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር።

22ነገር ግን ከግብፅ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ።

23ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤

24ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋር ተጣብቆአል።

25እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤

26እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’

27“ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እኔን በመተው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤

28ልሰጣቸው ወደማልሁላቸው ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉና የለመለመውን ዛፍ ሁሉ ተመለከቱ፤ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ ቍርባናቸውን በማቅረብ ቍጣዬን አነሣሡ፤ መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣናቸውን ዐጠኑ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውንም አፈሰሱ።”

29እኔም፣ ‘የምትሄዱበት ይህ ከፍታ ቦታ ምንድን ነው?” አልኋቸው።’ እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ ተብሎ ይጠራል።

30“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እንዳደረጉት ራሳችሁን ታረክሳላችሁን? በረከሱ ምስሎቻቸው ምኞት ትቃጠላላችሁን?

31ቍርባናችሁን በምታቀርቡበት ጊዜ ልጆቻችሁን ለእሳት በመዳረግ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ሁሉ እየረከሳችሁ ናችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ታዲያ የእኔን ሐሳብ እንድትጠይቁ ልፍቀድላች ሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

32“ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም።

33በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ።

34ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ።

35ወደ አሕዛብ ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ።

36በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋር እፋረዳለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

37ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋር አጣብቃችኋለሁ።

38በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

39“ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖታቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም።

40በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋር በዚያ እሻለሁ።

41ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።

42ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

43በዚያም መንገዳችሁንና ራሳችሁን ያረከሳችሁበትን ተግባር ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በፈጸማችሁትም ክፋት ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ።

44የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ብልሹ ተግባራችሁ ሳይሆን፣ ስለ ስሜ ስል በምጐበኛችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

45የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

46“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ደቡብ አዙር፤ በደቡብ ላይ ቃል ተናገር፤ በደቡብ አገር ደን ላይም ትንቢት ተንብይ።

47ለደቡቡ ደን እንዲህ በል፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በአንተ ላይ እሳት ልለኵስ ነው፤ እሳቱ የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍህን ሁሉ ይበላል፤ የሚንቦገቦገው ነበልባሉም አይጠፋም፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ያለውን ፊት ሁሉ ይለበልባል።

48ሰው ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ያያል፤ የሚያጠፋውም የለም።’ ”

49እኔም፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፣ ‘ተምሳሌት ብቻ ይመስላል’ ይሉኛል” አልሁ።

ማብራሪያ

20:1-9. በኃጢአት ለመቀጠል የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚለምኑት፣ ያውም ስለእርሱ መከራ እየደረሰባቸው ሳለ እንኳን፣ እነዚያ ልቦች እጅግ የደነደጉ ናቸው፤ ቁጥርን ተመልከት።

20:10-26. የእስራኤል በምድረበዳ የነበረው ታሪክ በአዲስ ኪዳንም ሆነ በብሉይ ኪዳን ለማስጠንቀቂያነት ተጠቅሷል። እግዚአብሔር ለእነርሱ ታላላቅ ነገሮችን አደረገ። ሕግን ሰጣቸው፣ የጥንቱን የሰንበትን ቀን የመጠበቅ ሥርዓትም አሳደሰ። ሰንበታት መብቶች ናቸው፤ የእርሱ ሕዝብ መሆናችንንም የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። የዕለቱን ግዴታችንን ብንፈጽም፣ ለመጽናናታችን ሲሆን፣ እኛን ቅዱስ የሚያደርገን፣ ይኸውም በዚህ ምድር እውነተኛ ብፁዕ የሚያደርገን፣ እንዲሁም ወደፊት ብፁዕ፣ ማለትም ፍጹም ቅዱስ ለመሆን የሚያዘጋጀን ጌታ እንደሆነ እንረዳለን። እስራኤላውያን አመፁ፣ በራሳቸው ላይ ባመጡትም ፍርድ ውስጥ ተተዉ። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የራሱ ቅጣት እንዲሆን ያደርጋል፤ ሆኖም እርሱ የኃጢአት ፈጣሪ አይደለም። ሰዎችን ለመከራ ለማዳረግ የራሳቸውን ክፉ ምኞትና ስሜት እንዲከተሉ ከመተው በቀር ከዚህ በላይ አያስፈልግም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG እንዲህም ሆነ፤ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔርን ይጠይቁ ዘንድ ከእስራኤል ሽማግሌዎች አያሌ ሰዎች መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። አማርኛ ENGNIV In the seventh year, in the fifth month on the tenth day, some of the elders of Israel came to inquire of the Lord, and… English BCV ኮነ ኸዓ፥ ኣብታ ሻውዐይቲ ዓመት፥ ኣብቲ ሓምሻይ ወርሒ፥ ኣብ ዓስረይቲ መዓልቲ፥ ብዙሓት ሰባት ካብ ዓበይቲ እስራኤል፥ ንእግዚኣብሄር ክጥይቑ መፂኦም ኣብ ቅድመይ ተቐመጡ። ትግርኛ GAZBIB Kana booddees waggaa torbaffaatti, ji'a shanaffaatti, ji'icha keessaa guyyaa kurnaffaatti, jaarsolii Israa'el keessaa j… Afaan Oromoo BCV GIZ ወእምዝ አመ ሳብዕ ዓመት በኃምስ ወርዓኅ አመ ዓሡር ሠርቅ መጽኡ ኀቤየ እደው እምረበናተ ቤተ እስራኤል ይስአልዎ ለእግዚአብሔር ወነበሩ ቅድመ ገጽየ። giz GAZGAZ Kana booddees waggaa torbaffaatti, ji'a shanaffaatti, ji'icha keessaa guyyaa kurnaffaatti, jaarsolii Israa'el keessaa j… Afaan Oromoo BCV aksum ኮነ ኸዓ፥ ኣብታ ሻውዐይቲ ዓመት፥ ኣብቲ ሓምሻይ ወርሒ፥ ኣብ ዓስረይቲ መዓልቲ፥ ብዙሓት ሰባት ካብ ዓበይቲ እስራኤል፥ ንእግዚኣብሄር ክጥይቑ መፂኦም ኣብ ቅድመይ ተቐመጡ። ትግርኛ SWAHSUV Ikawa katika mwaka wa saba, mwezi wa tano, siku ya kumi ya mwezi, baadhi ya wazee wa Israeli walikuja ili kuuliza kwa B… Kiswahili