ትንቢተ ሕዝቅኤል 1

AMHNIVአማርኛ28 ጥቅሶች7:04 አዳምጥ
አዳምጥ 7:04 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በሠላሳኛው ዓመት፣ በአራተኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ በኮቦር ወንዝ አጠገብ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ፣ ሰማያት ተከፈቱ፤ እኔም የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ።

2ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ቀን፣

3በባቢሎናውያን ምድር በኮቦር ወንዝ አጠገብ፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ቡዝ ልጅ፣ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ፤ በዚያ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረች።

4እኔም አየሁ፤ ስመለከትም፣ እነሆ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል መጣ፤ ይኸውም በታላቅ ብርሃን የተከበበ፣ መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበረ፤ የእሳቱም መኻል የጋለ ብረት ይመስል ነበር።

5በእሳቱም ውስጥ የአራት ሕያዋን ፍጡራን አምሳያ ነበረ፤ መልካቸውም የሰው ቅርጽ ይመስል ነበር።

6እያንዳንዳቸውም አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው።

7እግራቸው ቀጥ ያለ ነበር፤ ኮቴያቸውም እንደ ጥጃ ኮቴ ያለ ሲሆን፣ እንደ ተወለወለ ናስም ያበለጨልጭ ነበር።

8በአራቱ ጐኖቻቸው ባሉት ክንፎቻቸው ሥር የሰው እጅ ነበራቸው። አራቱም ፊቶችና ክንፎች ነበሯቸው፤

9ክንፎቻቸውም እርስ በርስ ይነካኩ ነበር። እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላቸውም ዞር ብለው አይመለከቱም ነበር።

10ፊታቸውም እንዲህ ነበር፤ አራቱም እያንዳንዳቸው የሰው ፊት ነበራቸው፤ በቀኝ በኩል የአንበሳ ፊት፣ በግራ በኩልም የበሬ ፊት ነበራቸው፤ እያንዳንዳቸውም ደግሞ የንስር ፊት ነበራቸው።

11እንግዲህ ፊታቸው ይህን ይመስል ነበር፤ ክንፋቸውም ወደ ላይ ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ክንፍ ነበራቸው፤ የእያንዳንዱም ክንፍ የሌላውን ክንፍ ይነካ ነበር፤ ሁለቱ ክንፎቻቸው ሰውነታቸውን ይሸፍኑ ነበር።

12እያንዳንዱ ቀጥ ብሎ ወደ ፊት ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላም ሳይዞር መንፈስ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄድ ነበር።

13የሕያዋን ፍጡራኑ መልክም እንደሚነድ የከሰል ፍምና የተቀጣጠለ ችቦ ይመስል ነበር፤ በፍጡራኑ መካከል እሳት ወዲያ ወዲህ ይንቀሳቀስ ነበር፤ ብርሃኑም ደማቅ ነበር፤ ከእሳቱም ውስጥ መብረቅ ይወጣ ነበር።

14ፍጡራኑም እንደ መብረቅ ብልጭታ ፍጥነት ወዲያ ወዲህ ይወረወሩ ነበር።

15ሕያዋን ፍጡራኑን ስመለከታቸው፣ አራት ፊቶች ባሉት በእያንዳንዱ ፍጡር አጠገብ አንዳንድ መንኰራኵር በምድር ላይ አየሁ።

16የመንኰራኵሮቹ መልክና አሠራር እንዲህ ነበር፤ እንደ ቢረሌ ያንጸባርቁ ነበር፤ የአራቱም ቅርጽ ተመሳሳይ ሆኖ፤ እያንዳንዱ መንኰራኵር በመንኰራኵር ውስጥ ተሰክቶ የተሠራ ይመስል ነበር።

17በሚሄዱበት ጊዜም፣ ፍጡራኑ ወደሚዞሩበት ወደ አራቱ አቅጣጫ ሁሉ መንቀሳቀስ ይችሉ ነበር፤ ፍጡራኑ በሚሄዱበትም ጊዜ መንኰራኵሮቹ ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር።

18የመንኰራኵሮቹ ክብ ጠርዝ ረጅምና አስፈሪ ነበር፤ የአራቱም መንኰራኵሮች ክብ ጠርዝ ዙሪያውን በዐይኖች የተሞላ ነበር።

19ሕያዋኑ ፍጡራን ሲንቀሳቀሱ፣ በአጠገባቸው ያሉ መንኰራኵሮችም ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ሕያዋኑ ፍጡራን ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ መንኰራኵሮቹም አብረዋቸው ከፍ ከፍ ይሉ ነበር።

20መንፈስ ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዳሉ፤ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ፤

21ፍጡራኑ ሲንቀሳቀሱ ይንቀሳቀሳሉ፤ ፍጡራኑ ቀጥ ብለው ሲቆሙ እነርሱም ይቆማሉ፤ ፍጡራኑ ከምድር ከፍ ከፍ ሲሉ፣ የሕያዋኑ ፍጡራን መንፈስ በውስጣቸው ስላለ መንኰራኵሮቹ አብረዋቸው ይነሣሉ።

22ከሕያዋኑ ፍጡራን ራስ በላይ የሚያስፈራና፤ እንደ በረዶ የሚያንጸባርቅ ጠፈር የሚመስል ነገር ነበር።

23ከጠፈሩም በታች የአንዱ ክንፍ ወደ ሌላው ተዘርግቶ ነበር፤ እያንዳንዱም ሰውነቱን የሚሸፍንበት ሁለት ክንፍ ነበረው።

24ፍጡራኑ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የክንፎቻቸውን ድምፅ ሰማሁ፤ ድምፁም እንደሚጐርፍ ውሃ ጩኸት፣ ሁሉን እንደሚችል አምላክ ድምፅና እንደ ሰራዊት ውካታ ነበር። መንቀሳቀሳቸውን ሲያቆሙም ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉ ነበር።

25መንቀሳቀሳቸውን አቁመው ክንፎቻቸውን ዝቅ እንዳደረጉ፣ ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ድምፅ ተሰማ።

26ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ከፍ ብሎ የሰንፔር ዙፋን የሚመስል ነገር ነበር፤ በዙፋኑም ላይ የሰው መልክ የሚመስል ነበር።

27ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ በእሳት መካከል እንዳለ የጋለ ብረት፣ ከወገቡም በታች እሳት ይመስል እንደነበር አየሁ፤ ደማቅ ብርሃንም በዙሪያው ነበር።

28በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደሚታየው ቀስተ ደመና በዙሪያው ያለው ጸዳል እንዲሁ ነበር። ይህም የእግዚአብሔር ክብር መልክ አምሳያ ነበረ። ባየሁትም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ፤ የአንድ ተናጋሪን ድምፅ ሰማሁ።

ማብራሪያ

1:1-14 የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኛ መድረሱ ምህረት ሲሆን፣ መከራ ውስጥ ስንሆንም በትጋት ልናዳምጠው የሚገባ ግዴታ ነው። የእግዚአብሔር ድምፅ በብርሃንና በኃይል ሙላት በመንፈስ ቅዱስ መጣ። እነዚህ ራእዮች የነቢዩን አእምሮ በእግዚአብሔር ታላላቅና ከፍ ባሉ ሀሳቦች ለመሙላት፣ በኃጢአተኞች ላይ ፍርሃት ለማሳደር፣ እንዲሁም እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ራሳቸውን ላዋረዱ ሰዎች መጽናናትን ለመናገር የተላኩ ይመስላሉ። ከቁ. 4-14 ባለው ክፍል፣ የራእዩ የመጀመሪያ ክፍል ሲሆን፣ እግዚአብሔር በብዙ መላእክት ታጅቦና ተገልጋይ ሆኖ እንደሚታይ ያሳያል፤ እነዚህም እርሱ የላካቸው መልእክተኞቹና ትእዛዙን የሚፈጽሙ አገልጋዮቹ ናቸው። ይህ ራእይ በአእምሮ ውስጥ ከባድ አክብሮታዊ ፍርሃትንና የመለኮታዊ ቁጣ ስጋትን የሚያሳድር ሆኖ ሳለ፣ የበረከቶችን ተስፋም ያሳድጋል።

እሳቱ በክብር ተከቧል። እግዚአብሔርን በመፈለግ ፍጹም አድርገን ማወቅ ባንችልም፣ በዙሪያው ያለውን ብርሃን ግን እናያለን። የሕያዋን ፍጥረታት ምሳሌ ከእሳቱ መካከል ወጣ፤ መላእክት ሕልውናቸውንና ኃይላቸውን ከእግዚአብሔር ያገኛሉ። የሰውን ግንዛቤ አላቸው፣ ከዚህም በላይ። አንበሳ በኃይልና በድፍረት ይበልጣል፤ በሬ በትጋትና በትዕግስት እንዲሁም የሚሠራውን ሥራ ሳይሰለች በመፈጸም ይበልጣል፤ ንስር በፍጥነትና በሹል እይታ፣ ከፍ ብሎም በመብረር ይበልጣል፤ መላእክትም በእነዚህ ሁሉ ረገድ ሰውን የሚበልጡ በመሆናቸው፣ በእነዚህ መልክ ታዩ። መላእክት ክንፎች አሏቸው፤ እግዚአብሔርም ወደ የትኛውም ሥራ ቢልካቸው፣ ጊዜ አያጠፉም። ቀጥ ብለው፣ ጽኑና የማይናወጡ ሆነው ቆሙ። ለመንቀሳቀስ ክንፎች ብቻ ሳይሆን፣ ለመሥራትም እጆች ነበሯቸው። ፈጣኖች የሆኑ ነገር ግን ንቁ ያልሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ። ይሯሯጣሉ እንጂ፣ ምንም የሚጠቅም ነገር አይሠሩም፤ ክንፎች አሏቸው እንጂ፣ እጆች የላቸውም። የመላእክቱ ክንፎች ወደ የትም ቦታ ቢወስዷቸው፣ ግዴታቸውን ለመወጣት እጆቻቸውንም ከእነርሱ ጋር ያዙ። የትኛውንም አገልግሎት ቢፈጽሙ፣ ሁሉም ቀጥ ብለው ወደፊት ይሄዱ ነበር። ቀጥ ብለን ስንሄድ፣ ወደፊት እንጓዛለን፤ እግዚአብሔርን በአንድ ልብ ስናገለግል፣ ሥራ እንፈጽማለን። ሲሄዱ አይዞሩም ነበር። ስህተት አይሠሩም ነበር፤ ሥራቸውም እንደገና መሠራትን አይሻም ነበር። በማናቸውም ነገር ለመዘናጋት ከሥራቸው አይዞሩም ነበር። የእግዚአብሔር መንፈስ በሚመራቸው ሁሉ ይሄዱ ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፥ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ። አማርኛ ENGNIV In the thirtieth year, in the fourth month on the fifth day, while I was among the exiles by the Kebar River, the heave… English BCV ኮነ ድማ፥ ኣብ መበል ሰላሳ ዓመት፥ ኣብታ ራብዐይቲ ወርሒ፥ ካብታ ወርሒ ድማ ኣብ ሓምሸይቲ መዓልቲ፥ ኣብ ሩባ ኮቦር ኣብ ማእኸል እቶም ምሩኻት እንተለኹ፥ ሰማያት ተኸፈቱ፤ ራእይ እግዚኣብሄ… ትግርኛ GAZBIB Waggaa soddommaffaatti, ji'a afuraffaatti, ji'icha keessaa guyyaa shanaffaatti, laga Kebaar bukkee warra booji'aman gid… Afaan Oromoo BCV GIZ ወኮነ አመ ሠላሳ ክረምት በራብዕ ወርኅ በኃምስ ሠርቀ ወሀሎኩ ማእከለ ፄዋ በፈለገ ኮቦር ተርኅዉ ሰማያት ወርኢኩ ራእየ እግዚአብሔር። giz GAZGAZ Waggaa soddommaffaatti, ji'a afuraffaatti, ji'icha keessaa guyyaa shanaffaatti, laga Kebaar bukkee warra booji'aman gid… Afaan Oromoo BCV aksum ኮነ ድማ፥ ኣብ መበል ሰላሳ ዓመት፥ ኣብታ ራብዐይቲ ወርሒ፥ ካብታ ወርሒ ድማ ኣብ ሓምሸይቲ መዓልቲ፥ ኣብ ሩባ ኮቦር ኣብ ማእኸል እቶም ምሩኻት እንተለኹ፥ ሰማያት ተኸፈቱ፤ ራእይ እግዚኣብሄ… ትግርኛ SWAHSUV Ikawa katika mwaka wa thelathini, mwezi wa nne, siku ya tano ya mwezi, nilipokuwa pamoja na watu waliohamishwa, karibu … Kiswahili