1ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ እንደ ቆየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት።
2አሮንም፣ “የሚስቶቻችሁን፣ የወንድና የሴት ልጆቻችሁን የጆሮ ወርቅ አውልቃችሁ ወደ እኔ አምጡ” ብሎ መለሰላቸው።
3ሕዝቡም ሁሉ የጆሮ ወርቃቸውን አውልቀው ወደ አሮን አመጡ።
4እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ።
5አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ።
6በማግሥቱ ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ።
7ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “ከግብፅ ያወጣኻቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ አለው፤
8ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለእርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ ” አሉ።
9እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ አንገተ ደንዳናዎችም ናቸው፤
10አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
11ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነዳል?
12ግብፃውያን፣ ‘በተራራዎቹ ላይ ሊገድላቸው ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ።
13ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።”
14ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም።
15ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላቶች በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጎኖች ተጽፎባቸው ነበር።
16ጽላቶቹ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሥራ ነበሩ፤ በጽላቶቹ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጽሕፈት ነበር።
17ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለቃ አለው።
18ሙሴም “የድል ድምፅ አይደለም፤ የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤ የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው” ብሎ መለሰለት።
19ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቶቹን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው።
20የሠሩትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ።
21አሮንንም፣ “ወደዚህ አስከፊ ኀጢአት ትመራቸው ዘንድ እነዚህ ሕዝብ ምን አደረጉህ?” አለው።
22አሮንም መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ አትቈጣ ብሎ መለሰለት፤ ይህ ሕዝብ ሁል ጊዜ ለክፋት ያዘነበለ መሆኑን አንተ ታውቃለህ፤
23እነርሱም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም’ አሉኝ።
24ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።”
25ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሳለቂያ እንደሆኑ ሙሴ አስተዋለ።
26ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር (ያህዌ) የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከእርሱ ጋር ሆኑ።
27ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው።
28ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያኑም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ያህል አለቁ።
29ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ።
30በማግሥቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው።
31ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ።
32አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ።”
33እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የበደለኝን ሁሉ ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ፤
34አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርኩት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።”
35አሮን በሠራው ጥጃ ባደረጉት ነገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕዝቡን በመቅሠፍት መታ።