ወደ ኤፌሶን 4

AMHNIVአማርኛ32 ጥቅሶች4:33 አዳምጥ
አዳምጥ 4:33 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ።

2ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ።

3በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።

4በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤

5አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤

6ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።

7ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል።

8ስለዚህም እንዲህ ይላል፤ “ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮ ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።”

9ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው?

10ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው።

11አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤

12ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣

13ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው።

14ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም።

15ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው፤

16ከእርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።

17ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም።

18እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቦናቸው ጨልሞአል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል።

19ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኵሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል።

20እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም፤

21በርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በእርሱ ተምራችኋል።

22ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጎደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤

23ደግሞም በአእምሮአችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣

24እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።

25ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና።

26ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤ በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤

27ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት።

28ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም።

29እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ።

30ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ።

31መራርነትን ሁሉ፣ ቍጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ።

32እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።

ማብራሪያ

4:1-6 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ክርስቶስ ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራቸው ሰዎች እንደሚገባ መመላለስ ከምንም ነገር በላይ በብርቱ የሚመከር ነው። በትሕትና፣ ለትዕቢት ተቃራኒ የሆነውን ትሑት መሆንን እንረዳለን። በየዋህነት ደግሞ፣ ሰውን ለማስቀየም ፈቃደኛ የማያደርግና በቀላሉ የማይናደድ ወይም የማይከፋ እጅግ ግሩም የሆነ የነፍስ ባሕርይ ነው። እኛ ራሳችን ይቅር ለማለት የሚያስቸግሩን ብዙ ነገሮች በውስጣችን እናገኛለንና፤ ስለዚህ በሌሎች ላይ ይቅር ለማለት ከባድ ነው የምንላቸውን ነገሮች ብናገኝ ልንደነቅ አይገባም። ሁሉም አማኞች ተስፋ የሚያደርጉበት አንድ ክርስቶስ አለ፤ ሁሉም የሚጠብቁትም አንድ ሰማይ አለ፤ ስለዚህ በአንድ ልብ ሊሆኑ ይገባል። ሁሉም ስለ ዓላማው፣ ስለ ፈጣሪው፣ ስለ ባሕርዩና ስለ ኃይሉ አንድ እምነት ነበራቸው። ሁሉም ስለ ሃይማኖት ታላላቅ እውነቶች አንድ ዓይነት ያምኑ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ጥምቀት፣ በውኃ ተጠምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን ተቀብለዋል፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም ነበር፤ ይህም የ'እንደገና መወለድ' ምልክት ነው። በሁሉም አማኞች ውስጥ እግዚአብሔር አብ በቅዱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እንደሚኖር ሁሉ፣ በመንፈሱና በልዩ ጸጋው አማካኝነት ይኖራል።

ኤፌሶን 4:7-16 ለእያንዳንዱ አማኝ እርስ በእርስ ለመተጋገዝ የጸጋ ስጦታ ተሰጥቶታል፡፡ የተሰጠውም ሁሉ ክርስቶስ እንደተመቸው ለእያንዳንዱ ሰው ሊሰጥ ነው፡፡ እርሱ ለእነርሱ ተቀበለ፣ እርሱም ለእነርሱ የተትረፈረፉ ስጦታዎችንና ጸጋዎችን እንዲሰጣቸው ነው፤ በተለይም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ፡፡ ይህ ስጦታ የቃል እውቀት ብቻ ወይም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ዝም ብሎ ማመን ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን እምነትንና መታዘዝን የሚያመጣ ነው፡፡ በክርስቶስ ሙላት አለ፣ ከዚያም ሙላት በእግዚአብሔር ምክር መሰረት ለእያንዳንዱ አማኝ አንድ መጠን ተሰጥቶታል፤ ነገር ግን ፍጹም ወደሆነው መጠን ወደ ሰማይ እስክንመጣ ድረስ አንደርስም፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ ዓለም እስከሆኑ ድረስ ያድጋሉ፤ የክርስቲያንም ዕድገት ወደ ክርስቶስ ክብር ያመራል፡፡ አንድ ሰው በቦታው ላይ ለመሻሻል፣ እንዲሁም እንደ መጠኑ የተቀበለውን ሁሉ ለሌሎች መንፈሳዊ ጥቅም ለማዋል በተነሳሳ ቁጥር፣ በልቡ ውስጥ የእውነተኛ ፍቅርና በጎ አድራጎት ጸጋ ሰርጾበታል ብሎ በበለጠ እርግጠኝነት ሊያምን ይችላል፡፡

4:17-24 ሐዋርያው ኤፌሶናውያንን በጌታ በኢየሱስ ስም እና ስልጣን እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፡ ወንጌልን ከተናዘዙ በኋላ፣ በከንቱ አስተሳሰቦችና ሥጋዊ ምኞቶች ይሄዱ እንደነበሩት ካልተለወጡት አሕዛብ መሆን የለባቸውም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6