መጽሐፈ መክብብ 7

AMHNIVአማርኛ29 ጥቅሶች4:27 አዳምጥ
አዳምጥ 4:27 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል።

2ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤ ሞት የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤ ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።

3ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤ ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና።

4የጠቢባን ልብ በሐዘን ቤት ነው፤ የሞኞች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው።

5የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣ የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል።

6የሰነፎች ሣቅ፣ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

7ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል፤ ጒቦም ልብን ያበላሻል።

8የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል፤

9የሞኞች ቊጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣ በመንፈስህ ለቊጣ አትቸኵል።

10አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤ እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና።

11ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው።

12ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው።

13እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከት፤ እርሱ ያጣመመውን፣ ማን ሊያቃናው ይችላል?

14ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን አስብ፤ እግዚአብሔር አንዱን እንዳደረገ፣ ሌላውንም አድርጎአል፤ ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ ምንም ሊያውቅ አይችልም።

15በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም።

16እጅግ ጻድቅ፣ እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ ራስህን ለምን ታጠፋለህ?

17እጅግ ክፉ አትሁን፤ ሞኝም አትሁን፤ ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ?

18አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ጽንፈኝነትን ያስወግዳል።

19በአንድ ከተማ ካሉ ዐሥር ገዦች ይልቅ፣ ጥበብ ጠቢቡን ሰው ኀያል ታደርገዋለች።

20ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።

21የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤ አለበለዚያ አገልጋይህ ሲረግምህ ትሰማ ይሆናል፤

22ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ ሌሎችን እንደረገምህ ልብህ ያውቃልና።

23እኔም ይህን ሁሉ በጥበብ ፈትኜ፣ “ጠቢብ ለመሆን ቈርጫለሁ” አልሁ፤ ይህ ግን ከእኔ የራቀ ነበር።

24ጥበብ ምንም ይሁን ምን፣ እጅግ ጥልቅና ሩቅ ነው፤ ማንስ ሊደርስበት ይችላል?

25ስለዚህ ጥበብንና የነገሮችን አሠራር ለመመርመርና ለማጥናት፣ የክፋትን መጥፎነት፣ የሞኝነትንም እብደት ለማስተዋል፣ አእምሮዬን መለስሁ።

26ልቧ ወጥመድ፣ እጆቿም እግር ብረት የሆኑ፣ አሽክላ የሆነች፣ ከሞት የከፋችዋን ሴት አገኘሁ፤ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከእጇ ያመልጣል፤ ኀጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች።

27ሰባኪው እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው፤ “የነገሮችን ብልኀት መርምሮ ለማግኘት፣ አንዱን በአንዱ ላይ በመጨመር፣

28ገና በመመርመር ላይ ሳለሁ፣ ግን ያላገኘሁት፣ ከሺህ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣ በእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም።

29ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤ እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ።”

ማብራሪያ

7:1-6 የቅድስናና የታማኝነት ዝና በዚህ ዓለም ካለው ሀብት ሁሉና ከደስታ ሁሉ የበለጠ የተወደደ ነው። ወደ ለቅሶ ቤት መሄድ ወደ ድግስ ቤት ከመሄድ ይልቅ የተሻለ ነው። አጋጣሚው ሲፈጠር ወደ ሁለቱም መሄድ ተገቢ ነው፤ አዳኛችን በቃና በጓደኛው ሰርግ ድግስ ላይ ተገኝቶ እንደበላ፣ በቢታንያም በጓደኛው መቃብር ላይ አለቀሰ። ነገር ግን፣ እኛ ምን ያህል ለከንቱነትና ለሥጋዊ ፍላጎት ለማርካት እንደምንዘነበል ስናስብ፣ የሰውን የዚህ ዓለም ፍጻሜ ለመረዳት ወደ ለቅሶ ቤት መሄድ የተሻለ ነው። ቁም ነገር ከሳቅና ፌሽታ ይበልጣል። ምንም እንኳ ለስሜታችን የማያስደስት ቢሆንም፣ ለነፍሳችን የሚጠቅመው ለእኛም የተሻለ ነው። የሥጋ ምኞታችን በጠቢባን ተግሳጽ መገደሉ፣ በሰነፎች አጉል ዘፈን ከሚረካ ይበልጣል። የሰነፍ ሳቅ ቶሎ ያልፋል፤ የደስታውም መጨረሻ ሐዘን ነው።

7:7-10 የፈተናዎቻችንና የችግሮቻችን ክስተት መጀመሪያ ከገመትነው ይልቅ ብዙ ጊዜ የተሻለ ነው። ትዕቢተኛና ችኩል ከመሆን ይልቅ በመንፈስ ትዕግስተኛ መሆን በእርግጥም ይሻላል። ቶሎ አትቆጣ፤ ለደረሰብህ በደልም ቶሎ ምላሽ አትስጥ። ቁጣህን አታርዘም፤ ምንም እንኳን ቁጣ የጥበበኛ ሰው ልብ ውስጥ ሊገባ ቢችልም፣ እንደ መንገደኛ ሰው አላፊ እንጂ አይኖርበትም፤ በሞኞች ልብ ውስጥ ብቻ ነው የሚኖረው። የራሳችንን ልብ መጥፎነት ይልቅ ማማረር የሚገባን ሲሆን፣ የዘመናችንን መጥፎነት እያነሱ ማማረር ሞኝነት ነው። በነዚህ ዘመናትም ቢሆን ብዙ ምህረቶችን እንደሰታለን። የቀድሞ ዘመናትን መልካምነት እያነሱ ማሞገስ ሞኝነት ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6