መጽሐፈ መክብብ 10

AMHNIVአማርኛ20 ጥቅሶች2:45 አዳምጥ
አዳምጥ 2:45 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የሞቱ ዝንቦች ሽቶን እንደሚያገሙ፣ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ያቀላል።

2የጠቢብ ልብ ወደ ቀኝ፣ የሞኝ ልብ ግን ወደ ግራ ያዘነብላል።

3ሞኝ በጐዳና ሲሄድ ማስተዋል ይጐድለዋል፤ ጅል መሆኑንም ለማንም ይገልጻል።

4የገዥ ቊጣ በተነሣብህ ጊዜ፣ ስፍራህን አትልቀቅ፤ ትዕግሥት ታላቁን ጥፋት ጸጥ ያደርጋልና።

5ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤ ይህም ከገዥ የሚወጣ ስሕተት ነው፤

6ሞኞች በብዙ የክብር ስፍራዎች ሲቀመጡ፣ ሀብታሞች ግን በዝቅተኛ ስፍራ ሆነዋል።

7መሳፍንት እንደ ባሮች በእግራቸው ሲሄዱ፣ ባሮች ፈረስ ላይ ተቀምጠው አይቻለሁ።

8ጒድጓድን የሚምስ ራሱ ይገባበታል፤ ቅጥርንም የሚያፈርስ እባብ ይነድፈዋል።

9ድንጋይ የሚፈነቅል ይጐዳበታል፤ ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።

10መጥረቢያ ቢደንዝ፣ ጫፉም ባይሳል፣ ብዙ ጒልበት ይጨርሳል፤ ብልኀት ግን ለውጤት ያበቃል።

11እባብ በድግምት ከመፍዘዙ በፊት ቢነድፍ፣ ለደጋሚው ምንም አይጠቅመውም።

12ከጠቢብ አፍ የሚወጣ ቃል ባለ ሞገስ ነው፤ ሞኝ ግን በገዛ ከንፈሩ ይጠፋል፤

13ቃሉ በመጀመሪያ ሞኝነት ነው፤ በመጨረሻም ደግሞ ክፉ እብደት ነው፤

14ሞኙም ቃልን ያበዛል። የሚመጣውን የሚያውቅ የለም፤ ከእርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ማን ሊነግረው ይችላል?

15የሞኝ ሥራ ራሱን ያደክመዋል፤ ወደ ከተማ የሚወስደውንም መንገድ አያውቅም።

16አንቺ፣ ንጉሥሽ ልጅ የሆነ፣ መሳፍንትሽም በጠዋት ግብዣ የሚያደርጉ ምድር ሆይ፤ ወዮልሽ!

17አንቺ ንጉሥሽ ከተከበረው ዘር የሆነ፣ ለመስከር ሳይሆን ለብርታት፣ በተገቢው ጊዜ የሚበሉ መሳፍንት ያሉሽ ምድር ሆይ፤ የተባረክሽ ነሽ፤

18ሰው ሰነፍ ከሆነ ጣራው ይዘብጣል፤ እጆቹም ካልሠሩ ቤቱ ያፈሳል።

19ግብዣ ለሣቅ ያዘጋጃል፤ ወይንም ሕይወትን ያስደስታል፤ ገንዘብም ካለ ሁሉ ነገር አለ።

20በሐሳብህም እንኳ ንጉሥን አትንቀፍ፤ በመኝታ ክፍልህም ባለጠጋን አትርገም፤ የሰማይ ወፍ ቃልህን ልትወስድ፣ የምትበረዋም ወፍ የምትለውን ልታደርስ ትችላለችና።

ማብራሪያ

፲፥፩-፫ በተለይ ሃይማኖታቸውን የገለጹ ሰዎች ከክፋት መገለጫዎች ሁሉ መራቅ ይገባቸዋል። ጥበበኛ ሰው ከሞኝ ይልቅ ታላቅ ብልጫ አለው፤ ሞኝ ግን ምንም ነገር ለማድረግ ሲሞክር ሁልጊዜ ግራ ይገባዋል። ኃጢአት የኃጢአተኞች ነውር ነው፣ በሄዱበትም ሁሉ የሞኝነታቸውን ያሳያል።

10:4-10 ሰሎሞን ሰዎችን ፍትህን በችኮላ እንዳይፈልጉና ለኩራትና ለበቀልም እንዳይገዙ የሚያስጠነቅቅ ይመስላል። በስሜት የኃላፊነት ቦታህን አትተው፤ ለጥቂት ጊዜ ታገስ፣ እጅ መስጠት ታላላቅ በደሎችን እንደሚያረግብ ታገኛለህና። ሰዎች እንደ ብቃታቸው አይመረጡም። ብዙውን ጊዜም እርዳታ ለመስጠት በጣም የሚጓጉት የችግሮቹን ወይም የሚያስከትለውን ነገር ብዙም የማያውቁት ናቸው። ይኸው አስተያየት ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለክርስቶስም አካል ይሠራል። ሁሉም አባላት እርስ በእርሳቸው ተመሳሳይ እንክብካቤ ሊኖራቸው ይገባልና።

10:11-15 በምሥራቅ እባቦችን በሙዚቃ የማሠር ልማድ አለ። የለፈለፈው ሰው አንደበት የማይታዘዝ ክፉ ነገር ነው፤ ሞት የሚያስከትል መርዝም የተሞላበት ነው። ተቃውሞም ይበልጥ እንዲያገርሽ ያደርገዋል እንጂ አይመልሰውም። እርሱን ገር አድርጎ ለማቆየት መንገድ መፈለግ ይኖርብናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6