ትንቢተ ዳንኤል 6

AMHEVGአማርኛ28 ጥቅሶች5:32 አዳምጥ
አዳምጥ 5:32 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ዳርዮስም በመንግሥቱ ሁሉ ዘንድ እንዲሆኑ መቶ ሀያ መሳፍንት በመንግሥቱ ላይ ይሾም ዘንድ ወደደ።

2መሳፍንቱም ሒሳቡን ያመጡላቸው ዘንድ፥ ንጉሡም እንዳይጐዳ ሦስት አለቆች በላያቸው አደረገ፤ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል ነበረ።

3ዳንኤልም መልካም መንፈስ ስላለው ከአለቆችና ከመሳፍንት በለጠ፤ ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ይሾመው ዘንድ አሰበ።

4የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም።

5እነዚያም ሰዎች፦ “ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም፡” አሉ።

6የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።

7የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች፦ ‘ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል’ የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ።

8አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ።”

9ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ።

10ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።

11እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት።

12ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ፦ “ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን?” አሉት። ንጉሡም መልሶ፦ “ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው፡” አላቸው።

13የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ “ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም፡” አሉት።

14ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፤ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ።

15የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን፦ “ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ፡” አሉት።

16የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ “ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ፡” አለው።

17ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው።

18ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ ሳይበላም አደረ፤ መብልም አላመጡለትም፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ።

19በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ።

20ወደ ጕድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ “የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን?” አለው።

21ዳንኤልም ንጉሡን፦ “ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።

22በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም፡” አለው።

23የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፤ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።

24ንጉሡም አዘዘ፥ ዳንኤልንም የከሰሱ እነዚያን ሰዎች አመጡአቸው፥ እነርሱንና ልጆቻቸውንም ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉአቸው፤ ወደ ጕድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።

25የዚያን ጊዜም ንጉሥ ዳርዮስ በምድር ሁሉ ላይ ወደሚኖሩ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ ወደሚናገሩ ሁሉ ጻፈ፥ እንዲህም አለ፦ “ሰላም ይብዛላችሁ።

26በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያው አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነውና፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፥ ግዛቱም እስከ መጨረሻ ድረስ ይኖራል።”

27ያድናል ይታደግማል፥ በሰማይና በምድርም ተአምራትንና ድንቅን ይሠራል፥ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል።

28ይህም ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ኑሮው ተቃናለት።

ማብራሪያ

6:1-5 ለእግዚአብሔር ክብር ስናስተውል፣ ዳንኤል አሁን እጅግ አንጋፋ ቢሆንም እንኳ፣ አሁንም ለሥራ ብቁ እንደነበርና ለሃይማኖቱም ታማኝ ሆኖ እንደቀጠለ እናያለን። ይህም የእግዚአብሔር ክብር ነው፤ ሃይማኖትን የሚመሰክሩ ሰዎች፣ እጅግ ንቁ የሆኑ ጠላቶቻቸው እንኳ ሊነቅፏቸው ምንም ምክንያት እንዳያገኙ በሚያስችል መንገድ ራሳቸውን ሲመሩ፤ ሊነቅፏቸው የሚችሉትም በአምላካቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ሲሆን ነው፤ እነርሱም በህሊናቸው መሠረት የሚመሩባቸው ጉዳዮች ናቸው።

6:6-10

ለሰላሳ ቀን ጸሎትን መከልከል፣ ለዚያ ያህል ጊዜ ማለት እግዚአብሔርን ከሰው የሚያገኘውን አምልኮ ሁሉ መዝረፍ፣ ሰውንም በእግዚአብሔር ካለው መጽናናት ሁሉ መዝረፍ ነው። በችግር ወይም በጭንቀት ጊዜ፣ የሰው ሁሉ ልብ እግዚአብሔርን እንዲጠራ አይመራውምን? ያለ እግዚአብሔር አንድ ቀን መኖር አንችልም ነበር፤ ሰዎችስ ያለ ጸሎት ሰላሳ ቀን መኖር ይችላሉን? ሆኖም ግን ሊሰጋ የሚገባው፣ ምንም ዓይነት መከልከያ ድንጋጌ ሳይኖርባቸው፣ ለሰላሳ ቀንና ከዚያ በላይ ተከታታይነት ባለው መልኩ ከልብ የመነጨ፣ ቁም ነገር የሆነ ልመናን ወደ እግዚአብሔር የማያቀርቡ ሰዎች፣ በትሕትናና በአመስጋኝ ልብ ዘወትር ከሚያገለግሉት እጅግ የሚበዙ መሆናቸው ነው። አሳዳጅ ሕጎች ሁልጊዜ የሚወጡት በሐሰት ሰበብ ነው፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች መራራ ቅሬታ ማሰማት ወይም ስድብ ውስጥ መዘፈቅ አይገባቸውም። ለጸሎት ሰዓት መመደብ መልካም ነው። ዳንኤል በግልጽና በድፍረት ጸለየ፤ ምንም እንኳ እጅግ ብዙ ሥራ የሚበዛበት ሰው ቢሆንም፣ ይህ ከዕለታዊ የአምልኮ ልምምዶቹ እንደሚያስቀረው አላሰበም። በዓለም ውስጥ ብዙም ሥራ የሌላቸው ሆነውም ለነፍሳቸው ይህን ያህል እንኳን የማያደርጉት እንዴት የማይሰበስባቸው ናቸው! በፈተና ጊዜ መጠንቀቅ አለብን፤ ጥንቃቄን እንደ ሽፋን አድርገን፣ በእግዚአብሔር ጉዳይ ፈሪነት እንዳይዝብን።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6