የሐዋርያት ሥራ 4

AMHNIVአማርኛ37 ጥቅሶች6:29 አዳምጥ
አዳምጥ 6:29 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ እየተናገሩ ሳሉ፣ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ኀላፊ እንዲሁም ሰዱቃውያን ድንገት ወደ እነርሱ መጡ።

2እነርሱም ሐዋርያት ሕዝቡን በማስተማራቸውና በኢየሱስ ስለተገኘው ትንሣኤ ሙታን በመስበካቸው እጅግ ተቈጡ።

3ጴጥሮስና ዮሐንስን ያዟቸው፤ ጊዜውም ምሽት ስለ ነበረ እስኪነጋ ድረስ ወህኒ ቤት አሳደሯቸው።

4ይሁን እንጂ ቃሉን ከሰሙት መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቊጥር ወደ አምስት ሺህ ከፍ አለ።

5በማግስቱም አለቆቻቸውና፣ ሽማግሌዎቻቸው እንዲሁም ጸሓፍት በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።

6ሊቀ ካህናቱ ሐና፣ ቀያፋ፣ ዮሐንስ፣ እስክንድሮስና የሊቀ ካህናቱ ቤተ ዘመዶች ሁሉ በዚያ ተገኝተው ነበር።

7እነርሱም ጴጥሮስንና ዮሐንስን በመካከል አቁመው፣ “ይህን ያደረጋችሁት በምን ኀይል ወይም በማን ስም ነው?” ብለው ጠየቋቸው።

8በዚህ ጊዜ፣ ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ የሕዝብ አለቆችና ሽማግሌዎች ሆይ፤

9ዛሬ ለዚህ ሽባ ሰው ስለ ተደረገው በጎ ሥራ፣ እንዴት እንደ ዳነ የምትጠይቁን ከሆነ፣

10እናንተ በሰቀላችሁት፣ እግዚአብሔር ግን ከሙታን ባስነሣው በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መዳኑንና ፊታችሁ መቆሙን እናንተም ሆናችሁ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይህን ይወቅ።

11እርሱም፣ “ ‘እናንተ ግንበኞች የናቃችሁት፣ የማእዘን ራስ የሆነው ድንጋይ’ ነው።

12ድነት በሌላ በማንም አይገኝም፤ እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከዚህ ስም በስተቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና።”

13ሰዎቹም፣ ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ፤ ከኢየሱስ ጋር እንደ ነበሩም ተገነዘቡ።

14የተፈወሰውን ሰው እዚያው ከእነርሱ ጋር ቆሞ ስላዩት የሚናገሩበትን ሰበብ አጡ።

15ስለዚህ ከሸንጎው እንዲያወጧቸው አዘዙ፤ ከዚያም በአንድነት ተሰብስበው ተመካከሩ፤

16እንዲህም ተባባሉ፤ “እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ምን እናድርጋቸው? በኢየሩሳሌም የሚኖር ሁሉ በእነርሱ እጅ የተደረገውን ድንቅ ታምር ዐውቆአል፣ ስለዚህ ይህንን ማስተባበል አንችልም፤

17ይሁን እንጂ፣ ይህ ነገር ከእንግዲህ በሕዝቡ መካከል ይበልጥ እንዳይስፋፋ፣ እነዚህም ሰዎች ዳግመኛ በዚህ ስም ለማንም እንዳይናገሩ እናስጠንቅቃቸው።”

18ከጠሯቸውም በኋላ፣ በኢየሱስ ስም ፈጽሞ እንዳይናገሩና እንዳያስተምሩ አዘዟቸው።

19ጴጥሮስና ዮሐንስ ግን መልሰው እንዲህ አሏቸው፤ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ለእናንተ መታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ይገባ እንደሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ፤

20እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።”

21እንደ ገና ከዛቱባቸው በኋላም ለቀቋቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ ስለ ሆነው ነገር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ስለ ነበር ሊቀጧቸው አልቻሉም፤

22በዚህ ታምር የተፈወሰውም ሰው ዕድሜው ከአርባ ዓመት በላይ ነበርና።

23ጴጥሮስና ዮሐንስም ከተፈቱ በኋላ ወደ ወገኖቻቸው ተመልሰው የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ያሏቸውን ሁሉ ነገሯቸው።

24እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ ድምፃቸውን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “ልዑል ጌታ ሆይ፤ አንተ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥረሃል፤

25በመንፈስ ቅዱስም አማካይነት በአገልጋይህ በአባታችን በዳዊት አፍ እንዲህ ብለህ ተናግረሃል፤ “ ‘አሕዛብ ለምን በቍጣ ተነሣሡ? ሕዝቡስ ለምን በከንቱ አሤሩ?

26የምድር ነገሥታት ተሰለፉ፤ ገዦችም በአንድነት ተሰበሰቡ፤ በጌታ ላይ፣ በተቀባውም ላይ ተከማቹ።’

27በርግጥም ሄሮድስና ጳንጥዮስ ጲላጦስ ከአሕዛብና ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በዚህች ከተማ አንተ በቀባኸው በቅዱሱ ብላቴናህ በኢየሱስ ላይ ለማሤር ተሰበሰቡ፤

28ይህም የሆነው የአንተ ክንድና ፈቃድ ጥንት የወሰኑት እንዲፈጸም ነው።

29አሁንም ጌታ ሆይ፤ ዛቻቸውን ተመልከት፤ ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገር እንዲችሉ አድርጋቸው።

30ለመፈወስ እጅህን ዘርጋ፤ በቅዱሱ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ድንቅና ታምራት አድርግ።”

31ከጸለዩም በኋላ የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በድፍረት ተናገሩ።

32ያመኑትም ሁሉ በአንድ ልብና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ነበር፤ ያላቸውም ሁሉ የጋራ ነበር እንጂ የራሱ የሆነውን ሀብት እንኳ እንደ ግሉ የሚቈጥር ማንም አልነበረም።

33ሐዋርያትም ስለ ጌታ ኢየሱስ ትንሣኤ በታላቅ ኀይል መመስከራቸውን ቀጠሉ፤ በሁላቸውም ላይ ታላቅ ጸጋ ነበር።

34ከመካከላቸውም አንድ ችግረኛ አልነበረም፤ ምክንያቱም መሬትም ሆነ ቤት የነበራቸውን ሁሉ እየሸጡ ዋጋውን አምጥተው፣

35በሐዋርያት እግር ሥር በማስቀመጥ ለእያንዳንዱ በሚያስፈልገው መጠን ያካፍሉት ነበር።

36በቆጵሮስ የሚኖር ዮሴፍ የሚባል አንድ ሌዋዊ ነበረ፤ ሐዋርያትም ‘በርናባስ’ ብለው ጠሩት፤ ትርጒሙም ‘የመጽናናት ልጅ’ ማለት ነው፤

37እርሱም መሬቱን ሸጦ፣ ገንዘቡን አምጥቶ በሐዋርያት እግር ሥር አስቀመጠ።

ማብራሪያ

4:1-4 ሐዋርያት የሙታንን ትንሣኤ በኢየሱስ አማካኝነት ሰበኩ። ይህ ደግሞ የወደፊቱን የደስታ ሕይወት ሁሉ ያካተተ ነበር፤ ይህንንም በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ማግኘት እንደሚቻል አስተማሩ። የክርስቶስ መንግሥት ክብር የሚያሳዝናቸው ሰዎች ሁኔታቸው የከፋ ነው፤ ምክንያቱም የዚያ መንግሥት ክብር የዘላለም እንደሆነ ሁሉ፣ ሐዘናቸውም የዘላለም ይሆናል።

ንጹሃንና ጠቃሚ የሆኑት የክርስቶስ አገልጋዮች፣ እንደ ሐዋርያት ያሉ፣ ክፉ ሰዎች ቅጣትን ሲያመልጡባቸው፣ በእምነት ስራቸውና በፍቅር ጉልበታቸው የተነሳ ብዙውን ጊዜ ችግር ደርሶባቸዋል። እስከ ዛሬም ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ የጋራ ጸሎትና መንፈሳዊ ውይይት በቁጣና በተቃውሞ የሚገጥሙበት አጋጣሚዎች አይጠፉም። ነገር ግን የክርስቶስን ትእዛዛት ብንታዘዝ እርሱ ይደግፈናል።

4:5-14 ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሳለ፣ ሁሉም ተአምራቱ የተደረገው እነርሱ በሰቀሉት በናዝሬቱ በኢየሱስ መሲሑ ስም ወይም ኃይል እንደሆነ እንዲረዱ አስፈለገው፤ ይህ ደግሞ እርሱ ከሙታን መነሳቱን የሰጡትን ምስክርነት አጸናው፣ እርሱም መሲሕ መሆኑን አረጋገጠ። እነዚህ ገዥዎች የሰቀሉት በዚያው በኢየሱስ መዳን አለባቸው፣ አለበለዚያም ለዘላለም ይጠፋሉ። የኢየሱስ ስም ለእያንዳንዱ ዘመንና ሕዝብ ለሆኑ ሰዎች ተሰጥቷል፤ በዚያም ብቻ አማኞች ከሚመጣው ቁጣ የሚድኑበት ነው። ነገር ግን ስግብግብነት፣ ትዕቢት ወይም ማንኛውም የተበላሸ ምኞት በውስጥ ሲገዛ፣ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ይጨፍራሉ፣ ልባቸውንም በብርሃኑ ላይ በጠላትነት ይዘጋሉ፤ የተሰቀለውን ክርስቶስን ከማወቅ ጋር ሲወዳደር ምንም ማወቅ የማይፈልጉትን ሁሉ የማያውቁና እውቀት የሌላቸው አድርገው ይቆጥራሉ። የክርስቶስ ተከታዮች ደግሞ ከእነርሱ ጋር የሚነጋገሩ ሁሉ ከኢየሱስ ጋር እንደነበሩ እንዲያውቁ በሚያስችል መንገድ መመላለስ ይኖርባቸዋል። ይህም ቅዱስ፣ ሰማያዊ፣ መንፈሳዊና ደስተኛ የሚያደርጋቸው፣ እንዲሁም ከዚህ ዓለም ከፍ የሚያደርጋቸው ነገር ነው።

4:15-22

የገዢዎቹ ትልቁ ስጋት የክርስቶስ ትምህርት በሕዝቡ ዘንድ እንዳይሰራጭ ነበር፤ ሆኖም ግን ሐሰት እንደሆነ ወይም አደገኛ እንደሆነ፣ ወይም ክፉ ዝንባሌ እንዳለው ሊናገሩ አልቻሉም ነበር፤ እውነተኛውንም ምክንያት ለመግለጥ አፈሩ፤ ይህም ምክንያት ግብዝነታቸውን፣ ክፋታቸውንና አምባገነንነታቸውን የሚመሰክር መሆኑ ነበር። የክርስቶስን ተስፋዎች በአግባቡ መመዘን የሚያውቁ ሰዎች፣ የዓለምን ማስፈራሪያዎች በአግባቡ መናቅም ያውቃሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6