የሐዋርያት ሥራ 3

AMHNIVአማርኛ26 ጥቅሶች4:37 አዳምጥ
አዳምጥ 4:37 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1አንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ በጸሎት ጊዜ ይኸውም ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት፣ ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር።

2ወደ ቤተ መቅደስ ከሚገቡት ሰዎች ምጽዋት እንዲለምን፣ ሰዎች በየዕለቱ ተሸክመው ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ የሚያስቀምጡት አንድ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ የሆነ ሰው ነበረ፤

3እርሱም ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ለመናቸው።

4ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ወደ እርሱ ትኵር ብሎ አየውና፣ “እስቲ ወደ እኛ ተመልከት” አለው።

5ሰውየውም፣ ከእነርሱ አንድ ነገር ለማግኘት አስቦ በትኵረት ተመለከታቸው።

6ጴጥሮስ ግን፣ “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ነገር ግን ያለኝን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ በእግርህ ተመላለስ” አለው፤

7ቀኝ እጁንም ይዞ አስነሣው፤ ወዲያውም እግሩና ቊርጭምጭሚቱ በረታ፤

8ዘሎም ቀጥ ብሎ ቆመ፤ መራመድም ጀመረ፤ ወዲህ ወዲያ እየሄደና እየዘለለም እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገባ።

9ሕዝቡም ሁሉ እየተራመደና እግዚአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ ባዩት ጊዜ፣

10ይህ ሰው ቀደም ሲል ‘ውብ’ በተባለው የቤተ መቅደስ መግቢያ በር ላይ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እርሱ መሆኑን ዐወቁ፤ በእርሱ ላይ ከተፈጸመውም ነገር የተነሣ በመደነቅና በመገረም ተሞሉ።

11የተፈወሰውም ለማኝ ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋር ጥብቅ ብሎ አብሮአቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደነበሩበት ‘የሰሎሞን መመላለሻ’ ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ።

12ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቊጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ?

13የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በእርሱ ፊት ካዳችሁት፤

14ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤

15የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን።

16ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው የበረታው በኢየሱስ ስም በማመን ነው፤ ሁላችሁም እንደምታዩት ፍጹም ፈውስ እንዲያገኝ ያደረገው የኢየሱስ ስምና በእርሱ አማካይነት የሚገኘው እምነት ነው።

17“አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደሆነ ዐውቃለሁ።

18እግዚአብሔር ግን የእርሱ የሆነው ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል አስቀድሞ በነቢያቱ ሁሉ አፍ የተናገረውን ፈጽሞአል።

19እንግዲህ ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ፤ ከመንገዳችሁም ተመለሱ፤ ከጌታም ዘንድ የመታደስ ዘመን ይመጣላችኋል፤

20ደግሞም አስቀድሞ ለእናንተ የተመደበውን ክርስቶስን እርሱም ኢየሱስን ይልክላችኋል።

21እግዚአብሔር አስቀድሞ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ እንደ ተናገረ፣ ሁሉን ነገር እስከሚያድስበት ዘመን ድረስ እርሱ በሰማይ ይቈይ ዘንድ ይገባል።

22ሙሴም እንዲህ ብሎአል፤ ‘ጌታ አምላካችሁ ከእናንተው መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱ የሚነግራችሁን ሁሉ ስሙት፤

23ይህን ነቢይ የማትሰማ ነፍስ ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይታ ትጥፋ።’

24“በርግጥም ከሳሙኤል ጀምሮ የተነሱት ነቢያት ሁሉ ስለ እነዚህ ጊዜያት ተናግረዋል።

25እናንተም የነቢያት ልጆች ናችሁ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለአብርሃም፣ ‘በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ’ ብሎ የገባው ኪዳን ወራሾች ናችሁ።

26እግዚአብሔር ብላቴናውን ባስነሣ ጊዜ፣ እያንዳንዳችሁን ከክፋታችሁ መልሶ ይባርካችሁ ዘንድ አስቀድሞ ወደ እናንተ ላከው።”

ማብራሪያ

3:1-11 ሐዋርያትና የመጀመሪያዎቹ አማኞች በጸሎት ሰዓት በቤተ መቅደስ አምልኮ ይገኙ ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስ ከተወለደ ጀምሮ ሽባ በሆነውና ከአርባ ዓመት በላይ በሆነው ሰው ላይ ተአምር ሊሰሩ በመለኮታዊ መመሪያ የተመሩ ይመስላል። ጴጥሮስ በናዝሬቱ ኢየሱስ ስም እንዲነሳና እንዲራመድ አዘዘው። እንደዚሁም፣ የሰዎችን ነፍሳት ፈውስ በበጎ ዓላማ ልንሞክር ከሆነ፣ አቅመ ቢስ ኃጢአተኞችን እንዲነሱና በእርሱ ባለ እምነት በቅድስና መንገድ እንዲራመዱ እየጠራን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና ኃይል መውጣት አለብን። የወደቀው ተፈጥሮአችን ሽባ ያደረጋቸውን ችሎታዎች ሁሉ በተመለከተ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሙሉ በሙሉ ሊያድነን እንደሚችል ለነፍሳችን እንዴት ያለ ጣፋጭ ሃሳብ ነው! መንፈስ ቅዱስ በኃይሉ እዚያ እንድንገባ ሲያደርገን፣ በምን ያህል ቅዱስ ደስታና ፍንደቃ ቅዱስ አደባባዮችን እንረግጣለን!

3:12-18 በተአምራት አሰራር ውስጥ ያለውን ልዩነት አስተውሉ። ጌታችን ሁልጊዜ ሁሉን የሚችል ስልጣን እንዳለው አድርጎ ይናገር ነበር፤ በመለኮታዊ ተአምራቱ የተሰጠውን ታላቅ ክብር ለመቀበልም ፈጽሞ አላቅማማም። ነገር ግን ሐዋርያት ሁሉን ለጌታቸው አመለከቱ፤ እርሱን የማይገባቸው መሳሪያዎቹ ሆነው ከማገልገል በቀር ምንም ክብር ለመቀበል እንቢ አሉ። ይህ ደግሞ ኢየሱስ ከአብ ጋር አንድ እንደሆነና ከእርሱም ጋር እኩል መሆኑን ያሳያል። ሐዋርያት ግን እነርሱ ደካማ፣ ኃጢአተኛ ሰዎች እንደሆኑ፣ በሁሉ ነገርም የፈውሱን ስራ ሙሉ በሙሉ ባደረገው በኢየሱስ ላይ ጥገኛ እንደሆኑ ያውቁ ነበር። ጠቃሚ ሰዎች እጅግ ትሑቶች መሆን አለባቸው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6