የሐዋርያት ሥራ 10

AMHNIVአማርኛ48 ጥቅሶች7:53 አዳምጥ
አዳምጥ 7:53 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በቂሳርያ፣ ‘የኢጣሊያ ክፍለ ጦር’ በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ።

2እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር።

3አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ።

4ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው። መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት አርጎልሃል።

5አሁንም ሰዎች ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤

6እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፎአል።”

7ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለእርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤

8የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።

9የተላኩትም ሰዎች በማግስቱ ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ።

10በዚያን ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤

11ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ።

12በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበሩ አዕዋፍ ነበሩበት።

13በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።

14ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኵስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ።

15ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኵስ አትቍጠረው” አለው።

16ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨርቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ።

17ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጒም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤

18ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ።

19ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤

20ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለ ሆንሁ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ።”

21ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጒዳይ ምንድን ነው?” አላቸው።

22ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት።

23ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው። ጴጥሮስም በማግስቱ ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ፤

24በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር።

25ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት።

26ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንዳንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው።

27ጴጥሮስም እያነጋገረው አብሮት ሲገባ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤

28እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋር እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኵስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል፤

29ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።”

30ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና

31እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሶአል።

32ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ እርሱም በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፎአል።’

33እኔም ወዲያው ላኩብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ እኛ ሁላችን ጌታ ያዘዘህን ስትነግረን ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት አለን።

34ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በርግጥ ተረድቻለሁ፤

35ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል።

36እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው።

37ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በመላው ይሁዳ የሆነውን ታውቃላችሁ፤

38እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።

39“እርሱ በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ላደረገው ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ ደግሞም ሰዎች እርሱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።

40እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤

41የታየውም ለሁሉ ሰው ሳይሆን፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ አብረነው ለበላንና ለጠጣን፣ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለመረጠን ለእኛ ለምስክሮቹ ነው።

42ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን፤

43በእርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”

44ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው።

45ከጴጥሮስ ጋር የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ፤

46ይኸውም በልሳን ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው። በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፤

47“እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉ፣ እንግዲህ በውሃ እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ማን ነው?”

48ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ፣ ጴጥሮስ ጥቂት ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲቀመጥ ለመኑት።

ማብራሪያ

10:1-8 እስከዚያ ጊዜ ድረስ ወደ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን የተጠመቁት አይሁድ፣ ሳምራውያን እንዲሁም የተገረዙና የሥርዓቱን ሕግ ያከብሩ የነበሩ ተለዋጮች ብቻ ነበሩ፤ አሁን ግን አሕዛብ አስቀድሞ አይሁድ ሳይሆኑ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች መብቶች ሁሉ ለመካፈል ተጠርተዋል። ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት አንዳንድ ጊዜ እኛ ባልጠበቅነው ቦታ ይገኛል። የእግዚአብሔር ፍርሃት በልብ ውስጥ በነገሠበት ሁሉ፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎችም ሆነ በአምልኮተ እግዚአብሔር ሥራዎች ይታያል፤ አንዱ ከሌላው አያስቀርም። ቆርኔሌዎስ በእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ እምነት እንደነበረው ጥርጥር የለውም፤ ምንም እንኳ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በክርስቶስ ግልጽ የሆነ እምነት ባይኖረውም። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ነበር፤ በኢየሱስ አማላጅነት፣ ቆርኔሌዎስ እርሱን ከማወቁ በፊትም እንኳ። እኛም ሁላችንም እንደዚሁ፣ ቀድሞ በኃጢአት ሙታን የነበርን ሕያው እንደተደረግን። በክርስቶስም ደግሞ ጸሎቶቹና ምጽዋቶቹ ተቀባይነት አግኝተዋል፤ አለበለዚያ ግን ውድቅ ይሆኑ ነበር። ቆርኔሌዎስ ያለ ክርክር ወይም መዘግየት ሰማያዊውን ራእይ ታዘዘ። የነፍሳችንን ጉዳይ በሚመለከት ጊዜ አንጥፋ።

10:9-18 በአሕዛብ ላይ የጴጥሮስ የነበረው ቅድመ ግምት ጌታ ለዚህ አገልግሎት ባያዘጋጀው ኖሮ ወደ ቆርኔሌዎስ እንዳይሄድ ይከለክለው ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንደ ርኩስ ይቆጠሩ የነበሩትን እንስሳት እግዚአብሔር ንጹህ እንደሆኑ እንዲቆጠሩ እንዳዘዘ ለአንድ አይሁዳዊ መንገር፣ የሙሴ ሕግ ሙሉ በሙሉ እንደ ተሻረ ማለት ነበር። ጴጥሮስ የዚህን ትርጉም ብዙም ሳይቆይ እንዲያውቅ ተደረገ። እግዚአብሔር ከፊታችን ያሉትን አገልግሎቶችና እንዴት እኛን እንደሚያዘጋጀን ያውቃል። እኛም እርሱ ያስተማረንን ትርጉም የምንጠቀምበትን አጋጣሚ ስናገኝ እናውቃለን።

10:19-33 ለማንኛውም አገልግሎት ጥሪያችን ግልጽ ሆኖልን ስናይ፣ ከቀደሙ አድሎአዊ አመለካከቶች ወይም ከድሮ አስተሳሰቦች በሚመጡ ጥርጣሬዎችና ሥነ ምግባራዊ ስጋቶች ግራ መጋባት የለብንም። ቆርኔሌዎስ ከጴጥሮስ ሊያገኘው ከጠበቀው ሰማያዊ ጥበብ አብረውት እንዲካፈሉ ጓደኞቹን ሰብስቦ ነበር። መንፈሳዊ ምግቦቻችንን ብቻችንን ለመብላት ልንመኝ አይገባም። በሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ከእኛ ጋር እንዲቀላቀሉ መጋበዝ ለዘመዶቻችንና ለጓደኞቻችን ደግነትና ክብር እንደሆነ ተቆጥሮ ሊሰጥና ሊወሰድ ይገባዋል። ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስን እንዲያስመጣ እግዚአብሔር የሰጠውን መመሪያ ገለጸ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6