መጽሐፈ ዮዲት 16

AMHSDVአማርኛ30 ጥቅሶች

1ዮዲትም ይህቺን የምስጋና መዝሙር በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ትዘምር ጀመረች፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህቺን የምስጋና መዝሙር ከእርስዋ ቀጥለው ዘመሩ።

2ዮዲትም አለች፥ “አምላኬን በከበሮ አመስግኑት፤ለጌታዬም በጸናጽል ዘምሩለት፤በገና እየደረደራችሁ አመስግኑት፤በምስጋና ከፍ ከፍ አድርጉት።ስሙንም ጥሩ፤

3እግዚአብሔር በጦርነት ጦርን ያሸንፋልና።

4ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ሠራዊቱም በሕዝቡ መካከል ነው፤ከሚያሳድዱኝም ሰዎች እጅ አዳነኝ።

5አሦራውያን በመስዕ በኩል ከተራራው ወጡ፤ከብዙ ሠራዊቶቻቸውም ጋር ወጡ፤በብዛታቸውም ፈሳሹን ዘጉ።ፈረሶቻቸውም ኰረብታውን ሸፈኑት።

6አውራጃችንን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ፥ጐልማሶቻችንንም በጦር ይገድሉ ዘንድ፥ሕፃኖቻችንንም በምድር ላይ ይፈጠፍጡ ዘንድ፥ወንዶች ልጆቻችንንና ቆነጃጅቶቻችንን ይማርኩ ዘንድ አዝዘው ነበር።

7ነገር ግን ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር በሴት እጅ አጠፋቸው።

8አርበኛቸው በጐልማሳ እጅ ድል አልተነሣምና፥የጤጣኖስ ልጆችም ያጠፉት አይደሉምና።ታላላቁ አርበኞችም ድል አልነሡትም፤ነገር ግን የሜራሪ ልጅ ዮዲት በደም ግባቷ አጠፋችው።

9የመበለትነቷንም ልብስ በእስራኤል ዘንድ ስለሚጨነቁት ሰዎች ስትል ተወች።

10ፊትዋንም ሽቱ ተቀባች፤ጠጕርዋንም ተሠርታ ሰርመዴ አደረገች፥እርሱንም ለማሳት የተልባ እግር ልብስን ለበሰች።

11ጫማዎችዋም ዐይኖቹን በዘበዙ፤ደም ግባትዋም ሰውነቱን ማረከች፤ሰይፍም በአንገቱ አለፈ።

12ከመደፋፈርዋም የተነሣ የፋርስ ሰዎች ደነገጡ፤ከመጨከንዋም የተነሣ የሜዶን ሰዎች ፈሩ።

13ያንጊዜ የተጨነቁ ወገኖች ደስ ብሏቸው ደነፉ፤የእኔ ደካሞች በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤እነዚያም ደንግጠው ነበር፤ እነዚህም ድምፃቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ፤እነዚያም ደንግጠው ሸሹ፤

14የሴቶች ልጆች ልጆችም አሳድደው ወጓቸው፤ጐልማሶቻችንም አቈሰሏቸው፤በጌታዬም ጦርነት ጠፉ።

15ለእግዚአብሔር መዝሙር እዘምራለሁ፤አዲስ መዝሙር እዘምራለሁ፤

16እግዚአብሔር ሆይ፥ ገናና ነህ፤እጅግም ክቡር ነህ፥በኀይልህም የተደነቅህ ነህ።

17ፍጥረትህ ሁሉ ለአንተ ይገዛሉ፤አንተ አዘዝህ፤ እነርሱም ተፈጥረዋልና፤መንፈስህን ላክህ፤ እነርሱም ታነጹ፥ለቃልህም የማይታዘዝ የለም።

18ተራሮች ከውኆች ጋር ከመሠረቶቻቸው ይነዋወጣሉና፤ዐለቱም ከገጸ መዓትህ የተነሣ እንደ አደሮ ማር ይቀልጣልና፥ዳግመኛም የሚፈሩህን ይቅር በላቸው።

19መሥዋዕቱ ሁሉ ለበጎ መዓዛ አይበቃምና፥ስቡም ሁሉ ከቍርባንህ ያንሣልና።እግዚአብሔርን የሚፈራው ሰው ግን ሁልጊዜ ገናና ነው።

20በወገኖች ላይ በጠላትነት ለሚነሡ ለአሕዛብ ወዮላቸው፤ሁሉን ቻይ እግዚአብሔርም በፍርድ ቀን ይበቀላቸዋል።

21በሥጋቸውም እሳትና ትልን ይልክባቸዋል፤በመከራውም ለዘለዓለሙ ያለቅሳሉ።”

22ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ባነጹ ጊዜ የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና የፈቃድ ቍርባናቸውን፥ ስጦታቸውንም አቀረቡ።

23ዮዲትም ሕዝቡ የሰጧትን የሆሎፎርኒስን ገንዘብ፥ ከመኝታ ቤቱም የወሰደችውን የራስጌውን ሰይፍ ለመታሰቢያ ለእግዚአብሔር ሰጠች።

24ሕዝቡም በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ፊት ሦስት ወር ደስታ አደረጉ፤ ዮዲትም ከእነርሱ ጋር ተቀመጠች።

25ከእነዚያም ወራት በኋላ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ተመለሰ፤ ዮዲትም ወደ ቤጤልዋ ተመልሳ በንብረቷ ኖረች፤ በዘመኗም በሀገሩ ሁሉ የከበረች ሆነች።

26የሚፈልጓትም ብዙዎች ነበሩ፤ ባሏ ምናሴ ሞቶ በወገኖቹ ዘንድ ከተቀበረ ጀምሮ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ በግብር ያወቃት ሰው የለም።

27ፈጽማም በክብር ገነነች።

28በባሏ በምናሴም ቤት እስክታረጅ ድረስ ኖረች፤ ዕድሜዋም መቶ ዐምስት ዐመት ነበር፤ ያችንም ብላቴናዋን ነጻ አወጣቻት፤ በቤጤልዋ ሞታ በባሏ በምናሴ ዋሻ ተቀበረች፤

29የእስራኤልም ወገኖች ሰባት ቀን አለቀሱላት፤ ከመሞትዋም በፊት ገንዘብዋን ለባልዋ ለምናሴ አቅራቢያና ለእርሷ አቅራቢያ ለሆኑ ዘመዶችዋ አካፈለች።

30የእስራኤልንም ልጆች በዮዲት ዘመን፥ ዳግመኛም እርስዋ ከሞተች በኋላ ለብዙ ዘመን ያስፈራቸው አልነበረም።

ትርጉሞች1 · 1