መጽሐፈ ዮዲት 1

AMHSDVአማርኛ16 ጥቅሶች

1በታላቅዋ ከተማ በነነዌ ለአሦር በነገሠ በናቡከደነፆር በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ሜዶንንና ባጥናን ይገዛ የነበረው ንጉሥ አርፋክስድ፥

2የባጥናን ዙሪያ በለዘበ ድንጋይ ሠራ፤ በከተማዋ ወርድ በኩል የመሠረትዋ ስፋት ሠላሳ ክንድ ነው፤ በከተማዋ ፊት ለፊት ያለው ስፋት ስድሳ ክንድ ርዝመት ነው። የግንቡን ቁመት ሰባ ክንድ አድርጎ ሠራ፤ ማዕዘኑም አምሳ ክንድ ነው።

3በየበሩ መቶ መቶ ክንድ እያለፈ የጕበኛ ቤቱን አቆመ፤ መሠረቱም ከማዕዘን እስከ ማዕዘን ድረስ ስድሳ ክንድ ነው።

4ጽኑዓኑ፥ ኀያላኑና የጥበቃ ሠራዊቱ የሚገቡባቸው የሚከፈቱ የበሮችዋን ደጃፍ ቁመታቸውን ሰባ ክንድ፥ ስፋታቸውን አርባ ክንድ አድርጎ ሠራ።

5በዚያም ወራት ናቡከደነፆር ንጉሡ አርፋስክድን በሰፊ ሜዳ ተዋጋው፤ ያም ሜዳ በራግው አውራጃ ያለ ነው።

6በአምባ የሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ ወጥተው ተቀበሉት፤ በኤፍራጥስና በጤግሮስ፥ በሒደስጶንም፥ በኤሊሜዎን ንጉሥ በአርዮክ ግዛት አውራጃ ያሉ ሁሉ የካሉድን ልጆች ይዋጓቸው ዘንድ እጅግ ብዙ የሆኑ አሕዛብም ተሰበሰቡ።

7የፋርስ ንጉሥ ናቡከደነፆርም በፋርስ አውራጃ ለሚኖሩ ሁሉ፥ በቂልቅያ፥ በደማስቆና በሊባኖስ ምዕራብ ወደሚኖሩ ሁሉ በወንዝ ዳርም ወደሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላከ።

8በቀርሜሎስና በገለዓድ፥ በገሊላና ሰፊ በሆነ በአስዴራን ምድረ በዳ ለሚኖሩ አሕዛብ።

9በሰማርያና በአውራጃዋ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶ እስከ ኢየሩሳሌምና እስከ ቢላጢኒ፥ እስከ ኪሎስና እስከ ቃዴስ እስከ ግብፅ ወንዝ፥ ጣፍናስና ራሚስ እስከ ጌሴም ምድር ሁሉ።

10በጣኔዎስና በሜኒፌዎስ በላይ እስኪደርስ በግብፅ ለሚኖሩ ሁሉ እስከ ኢትዮጵያ ድንበር ድረስ ሁሉ ላከ።

11በምድር የሚኖሩ ሁሉ የፋርስ ንጉሥ የናቡከደነፆርን ትእዛዝ እንቢ አሉ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ጦር አልሄዱም። አልፈሩትምና በፊታቸው እንደ አንድ ሰው ሆኗልና። መልእክተኞቹም ባዶአቸውን በውርደት ከፊታቸው ተመለሱ።

12ናቡከደነፆርም በዚያች ምድር ላይ ፈጽሞ ተቈጣ፤ የቂልቅያንና የደማስቂኒስን፥ የሶርያንም አውራጃ ሁሉ ይበቀልና በሞዓብ ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ የአሞንንም ልጆች ይሁዳንም ሁሉ በግብፅ የሚኖሩትንም ከሁለቱ ባሕሮች ድረስ ተበቅሎ በሰይፍ ያጠፋቸው ዘንድ በዙፋኑና በመንግሥቱ ማለ።

13ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ንጉሡ አርፋክስድን በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት ተዋጋው፤ ድል ነሥቶም የአርፋክስድን ሠራዊቱን ሁሉ፥ ፈረሶቹንና ሰረገላዎቹን ሁሉ ወሰደ።

14ሀገሮቹንም ሁሉ ያዘ፤ እስከ ባጥናም ድረስ ሄዶ አምባቸውን ያዘ፤ ሀገሩንም ሁሉ በረበረ፤ አጠፋትም።

15አርፋክስድንም በራግው አውራጃ ይዞ በጦር ወጋው፤ ፈጽሞም አጠፋው።

16እርሱም ተመለሰ፤ ከእርሱ ጋር ያሉ እጅግ አርበኞች የሆኑ ብዙ ሰዎችም ሁሉ ተመለሱ፤ በዚያም ሲያስብና ሲመክር መቶ ሃያ ቀን ተቀመጠ።

ትርጉሞች1 · 1