1በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ምድሪቱን ወረረ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ገበረለት፤ ከዚያ በኋላ ግን ሐሳቡን ለውጦ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ።
2እግዚአብሔርም በኢዮአቄም ላይ ባቢሎናውያን፣ ሶርያውያን፣ ሞዓባውያንና አሞናውያን አደጋ ጣዮችን ላከበት፤ በአገልጋዮቹ በነቢያቱ አማካይነት በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ይሁዳን ያጠፉ ዘንድ እነዚህን ላከ።
3ከፊቱ ያርቃቸው ዘንድ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በይሁዳ ላይ በትክክል ሊፈጸሙ ችለዋል፤ ይህም ምናሴ ስለ ሠራው ኀጢአትና ስለ ፈጸመውም ሁሉ፣
4እንዲሁም ንጹሕ ደም ስላፈሰሰ ነው። ኢየሩሳሌምም በንጹሕ ደም እንድትጥለቀለቅ በማድረጉ፤ እግዚአብሔር ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።
5በኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
6ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ዮአኪንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።
7የባቢሎንም ንጉሥ ከግብፅ ደረቅ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ የነበረውን ግዛቱን ሁሉ ወስዶበት ስለ ነበር፣ የግብፅ ንጉሥ ከአገሩ ዳግም ለዘመቻ አልወጣም።
8ዮአኪን ሲነግሥ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሦስት ወር ገዛ። እናቱ ኔስታ ትባላለች፤ እርሷም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች።
9አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10በዚያን ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ጦር አለቆች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቧት፤
11የጦር አለቆቹ ከበባ በሚያደርጉበትም ሰዓት ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ከተማዪቱ መጣ።
12የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን፣ እናቱ፣ የክብር አጃቢዎቹ፣ መሳፍንቱና ሹማምቱ ሁሉ እጃቸውን ለባቢሎን ንጉሥ ሰጡ። የባቢሎን ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው።
13እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ አጋዘ፤ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያሠራቸውንም የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ።
14ደግሞም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ እንዳለ የጦር አለቆቹንና ተዋጊዎቹን በሙሉ፣ የእጅ ባለሙያዎችንና ቀጥቃጮችን ሁሉ ጨምሮ ባጠቃላይ ዐሥር ሺህ ሰው በምርኮ ወደ አገሩ ወሰደ። በዚያ የቀሩት የመጨረሻዎቹ ያገሪቱ ድኾች ብቻ ነበሩ።
15ናቡከደነፆር ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው እንዲሁም የንጉሡን እናት፣ ሚስቶቹን፣ ሹማምቱና በአገር የታወቁትን ታላላቅ ሰዎችም ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ወሰደ።
16ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ በአጠቃላይ ብርቱ የሆኑትንና ለጦርነት ብቃት ያላቸውን ሰባት ሺህ ተዋጊዎች አንድ ሺህ የእጅ ባለሙያዎችንና ቀጥቃጮችን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ።
17ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያን በምትኩ አነገሠው፤ ስሙንም ሴዴቅያስ አለው።
18ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱ አሚጣል ትባላለች፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።
19ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
20እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቊጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አራቃቸው። በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።