2ኛ ቆሮንቶስ 8

AMHNIVአማርኛ24 ጥቅሶች4:33 አዳምጥ
አዳምጥ 4:33 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር በመቄዶንያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት የሰጠውን ጸጋ እንድታውቁ እንፈልጋለን።

2የደረሰባቸው መከራ ጽኑ ቢሆንም ደስታቸው ግን የላቀ ነበር፤ ድኽነታቸው ብርቱ ቢሆንም ልግስናቸው ግን የበዛ ነበር።

3እንደ ዐቅማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከዐቅማቸው በላይ በፈቃዳቸው እንደ ሰጡ እመሰክርላቸዋለሁ።

4እነርሱም ቅዱሳንን ለመርዳት በሚደረገው አገልግሎት ለመሳተፍ ዕድል ያገኙ ዘንድ አጥብቀው ይለምኑን ነበር።

5እኛ ከጠበቅነው በላይ፣ በመጀመሪያ ራሳቸውን ለጌታ ሰጡ፤ ቀጥለውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳቸውን ለእኛ ሰጡ።

6ስለዚህ ቲቶ፣ በእናንተ መካከል ቀደም ሲል የጀመረውን የልግስና ሥራ ከፍጻሜ እንዲያደርስ ለምነነው ነበር።

7እናንተም በሁሉ ነገር ይኸውም በእምነት፣ በቃል፣ በዕውቀት፣ በፍጹም ትጋትና ለእኛም ባላችሁ ፍቅር ልቃችሁ እንደ ተገኛችሁ፣ በዚህም የቸርነት ሥራ ልቃችሁ እንድትገኙ ዐደራ እንላችኋለን።

8ይህን የምለው ትእዛዝ ለመስጠት ብዬ አይደለም፤ ነገር ግን ሌሎች ከሚያሳዩት ትጋት አንጻር የፍቅራችሁን እውነተኛነት ለማረጋገጥ ነው።

9የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ ታውቃላችሁና፤ በእርሱ ድኽነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ እርሱ ሀብታም ሆኖ ሳለ ለእናንተ ሲል ድኻ ሆነ።

10ስለዚህ ጒዳይ የምሰጣችሁ ጠቃሚ ምክር ይህ ነው፤ ባለፈው ዓመት በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤

11አሁንም የጀመራችሁትን ተግባር በዐቅማችሁ መጠን ከፍጻሜ አድርሱት፤ ይህም ለመስጠት የነበራችሁ በጎ ፈቃድ እውን እንዲሆን ነው።

12ለመስጠት በጎ ፈቃድ ካለን ስጦታው ተቀባይነት የሚያገኘው ባለን መጠን ስንሰጥ እንጂ፣ በሌለን መጠን ለመስጠት ስንሞክር አይደለም።

13ይህንን የምንለው እናንተ ተቸግራችሁ ሌሎች ይድላቸው ለማለት ሳይሆን፣ ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው።

14በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጒድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጒድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ።

15ይህም፣ “ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂት የሰበሰበም አልጐደለበትም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

16እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤

17ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የመጣው ልመናችንን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ጒጒትና በራሱ ፈቃድ በመነሣሣት ነበር።

18ከእርሱም ጋር በወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ልከነዋል።

19ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ አብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጦአል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው።

20በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን።

21ምክንያቱም ዐላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን፣ በሰውም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው።

22ደግሞም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ ተፈትኖ ትጉ ሆኖ የተገኘውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር ልከነዋል፤ አሁንም በእናንተ እጅግ ከመታመኑ የተነሣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየተጋ ነው።

23ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፣ እርሱ እናንተን ለማገልገል አብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችንም የሚጠይቅ ቢኖር እነርሱ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችና የክርስቶስ ክብር ናቸው።

24ስለዚህ የፍቅራችሁን እውነተኛነትና በእናንተም የምንታመነው የቱን ያህል እንደሆነ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ግለጡላቸው።

ማብራሪያ

8:1-6 የእግዚአብሔር ጸጋ በማንኛውም ጊዜ በእኛ ውስጥ ያለውን ወይም በእኛ የሚደረገውን መልካም ነገር ሁሉ መሠረትና ምንጭ መሆኑ ሊታመንበት ይገባል። ለሌሎች ጠቃሚዎች እንድንሆንና ለማንኛውም መልካም ሥራ ቀናተኞች እንድንሆን ከተደረግን፣ ይህ ታላቅ የእግዚአብሔር ጸጋና ሞገስ ነው። ጳውሎስ የማቄዶንያውያንን በጎ አድራጎት አወድሷል። ጳውሎስ እንዲያሳስባቸው ከሚያስፈልግ ይልቅ፣ ስጦታውን እንዲቀበልላቸው ለመኑት። ለእግዚአብሔር የምንጠቀምበት ወይም የምናወጣው ማንኛውም ነገር፣ የራሱን ለራሱ መስጠት ብቻ ነው። ለበጎ ተግባር የምንሰጠው ሁሉ፣ ራሳችንን ለጌታ አስቀድመን ካልሰጠን በቀር፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም፣ ለኛም ጥቅም አይሆንም። በእውነት መልካም የሆኑትን ሥራዎች ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸጋ በመስጠት፣ የሚገባውን ክብር ለእርሱ ብቻ ከመስጠት ባሻገር፣ የሰዎችን ጥንካሬ ምንጭም እናሳያለን። የበዛ መንፈሳዊ ደስታ ሰዎችን በፍቅር ሥራና ድካም ውስጥ ልባቸውን ያሰፋል። ይህ ደግሞ፣ እስካልተገፋፉ ድረስ ማንኛውንም መልካም ሥራ የማይቀላቀሉ ሰዎች ባሕሪ ምንኛ ይለያል!

፰፥፯-፱ እምነት ሥር ነው፤ ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማይቻል (ዕብ ፲፩፥፮)፣ እንዲሁ በእምነት የሞሉ በሌሎች ጸጋዎችና በመልካም ሥራዎችም ይሞላሉ፤ ይህም በፍቅር ሆኖ የሚገለጥ ነው። ብዙ የሚያወሩ ሁልጊዜ ምርጥ ሰራተኞች አይደሉም፤ ነገር ግን እነዚህ ቆሮንቶሳውያን መልካም አውቀውና ተናግረው እንደነበር ሁሉ፣ በሥራም ታታሪዎች ነበሩ። ለእነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች ሐዋርያው ይህንን ጸጋም እንዲጨምሩላቸው ይመኛል፣ ይኸውም ለድሆች በቸርነት እንዲበዙ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6