2ኛ ቆሮንቶስ 6

AMHNIVአማርኛ18 ጥቅሶች3:16 አዳምጥ
አዳምጥ 3:16 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ እንደ መሆናችን መጠን፣ የተቀበላችሁትን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከንቱ እንዳታደርጉት ዐደራ እንላችኋለን።

2እርሱ፣ “በትክክለኛው ሰዓት ሰማሁህ፤ በመዳንም ቀን ረዳሁህ” ይላልና። እነሆ፤ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤ የመዳንም ቀን አሁን ነው።

3አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ፣ ለማንም ዕንቅፋት መሆን አንፈልግም።

4ይሁን እንጂ በምናደርገው ነገር ሁሉ ራሳችንን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እናቀርባለን፦ በብዙ ትዕግሥት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣

5በመገረፍ፣ በመታሰር፣ በሁከት፣ በሥራ ብዛት፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመራብ፣

6በንጽሕና፣ በዕውቀት፣ በትዕግሥት፣ በቸርነት፣ በመንፈስ ቅዱስ፣ በእውነተኛ ፍቅር፣

7በእውነት ቃል፣ በእግዚአብሔር ኀይል፣ በቀኝና በግራ እጅ የጽድቅ የጦር ዕቃ በመያዝ፣

8በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ፣ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤

9የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤

10ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው።

11የቆሮንቶስ ሰዎች ሆይ፤ ሁሉን በግልጽ ነግረናችኋል፤ ልባችንንም ወለል አድርገን ከፍተንላችኋል።

12ፍቅራችሁን የነፈጋችሁን እናንተ ናችሁ እንጂ እኛስ ፍቅራችንን አልነፈግናችሁም።

13ልጆቼ እንደመሆናችሁ መጠን ይህን አሳስባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያው ልክ ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱልን።

14ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?

15ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን ስምምነት አለው? የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ኅብረት አለው?

16የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖታት ጋር ምን ስምምነት አለው? እኛኮ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነን፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ተናግሮአል፤ “ከእነርሱ ጋር እኖራለሁ፤ በመካከላቸውም እመላለሳለሁ፤ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ።”

17“ስለዚህ ከመካከላቸው ውጡ፤ ለእኔም የተለያችሁ ሁኑ፤ ይላል ጌታ። ርኩስ የሆነውን ነገር አትንኩ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ።”

18“እኔ አባት እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ወንዶችና ሴቶች ልጆቼ ትሆናላችሁ፤ ይላል ሁሉን የሚችል ጌታ።”

ማብራሪያ

6:1-10 ወንጌል በጆሮአችን ውስጥ የሚያስተጋባ የጸጋ ቃል ነው። የወንጌል ዘመን የመዳን ቀን ነው፤ የጸጋው መንገድ የመዳን መንገድ ነው፤ የወንጌል ጥሪዎች የመዳን ጥሪዎች ናቸው፤ የአሁኑም ጊዜ እነዚህን ጥሪዎች ለመቀበል የተገባው ጊዜ ነው። ነገ የእኛ አይደለምና፤ ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም፤ እኛም ወዴት እንደምንሆን አናውቅም። አሁን የጸጋ ቀን ተሰጥቶናልና፤ ማንም እንዳይዘነጋው ይጠንቀቅ። የወንጌል አገልጋዮች ራሳቸውን እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሊመለከቱ ይገባል፤ በሁሉም ነገር ደግሞ ለዚያው አገልጋይነት ተስማሚ በሆነ መንገድ ሊሠሩ ይገባል።

ሐዋርያውም እንዲሁ አድርጓል፤ በመከራ ብዙ ትዕግሥት በማሳየት፣ ከመልካም መርሆዎች በመነሳት በመሥራት፣ እንዲሁም በተገቢው ስነ-ምግባርና ጠባይ። ምእመናን በዚህ ዓለም ከፈተናዎች ለመጠበቅ፣ የሰዎችን መልካም ምስክርነት በትዕቢት ርቀው ለመቀበል፣ እንዲሁም ስድባቸውን በትዕግሥት ለመቋቋም የእግዚአብሔር ጸጋ ያስፈልጋቸዋል። በራሳቸው ምንም የላቸውም፤ ነገር ግን በክርስቶስ ሁሉን ነገር አላቸው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6