1ኛ ቆሮንቶስ 1

AMHNIVአማርኛ31 ጥቅሶች5:06 አዳምጥ
አዳምጥ 5:06 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራው ከጳውሎስ፣ ከወንድማችንም ከሶስቴንስ፤

2በቆሮንቶስ ላለችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ተቀድሰው፣ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ሆነው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት፤

3ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

4በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር ስለ እናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።

5ምክንያቱም በማናቸውም ነገር ይኸውም በንግግር ሁሉ፣ በዕውቀትም ሁሉ በእርሱ በልጽጋችኋል፤

6ስለ ክርስቶስ የመሰከርንላችሁም በእናንተ ዘንድ ጸንቶአል።

7ስለዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ በጒጒት በመጠባበቅ ላይ ሳላችሁ፣ ማንኛውም መንፈሳዊ ስጦታ አይጐድልባችሁም።

8በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትገኙ እርሱ እስከ መጨረሻው ድረስ አጽንቶ ይጠብቃችኋል።

9ወደ ልጁ፣ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው።

10ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር፣ አንድ ልብ፣ አንድ ሐሳብ እንዲኖራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም እንድትስማሙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።

11ወንድሞች ሆይ፤ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ከቀሎዔ ቤተ ሰብ ሰምቻለሁ፤

12ነገሩም እንዲህ ነው፤ ከእናንተ አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሲል፣ ሌላው፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ይላል፤ ደግሞም አንዱ፣ “እኔ የኬፋ ነኝ” ሲል፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔስ የክርስቶስ ነኝ” ይላል።

13ለመሆኑ ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ጳውሎስስ ለእናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠምቃችኋልን?

14ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በስተቀር ከእናንተ ማንንም ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤

15ስለዚህ በስሜ መጠመቁን የሚናገር ማንም የለም።

16በርግጥ የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰው አጥምቄአለሁ፤ ከእነዚህ ሌላ ግን ማጥመቄ ትዝ አይለኝም።

17ክርስቶስ የላከኝ ወንጌልን እንድሰብክ እንጂ እንዳጠምቅ አይደለም፤ የክርስቶስም መስቀል ከንቱ እንዳይሆን፣ በሰዎች የንግግር ጥበብ አልሰብክም።

18የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉ ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድ ነው ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤

19እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የዐዋቂዎችንም ዕውቀት ከንቱ አደርጋለሁ።”

20ጠቢብ የት አለ? ሊቅስ የት አለ? የዘመኑስ ፈላስፋ የት አለ? እግዚአብሔር የዓለምን ጥበብ ሞኝነት አላደረገምን?

21ከእግዚአብሔር ጥበብ የተነሣ ዓለም በገዛ ጥበቧ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ያድን ዘንድ የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአል።

22መቼም አይሁድ ታምራዊ ምልክትን ይፈልጋሉ፤ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፤

23እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው።

24እግዚአብሔር ለጠራቸው ግን፣ አይሁድም ሆኑ ግሪኮች፣ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል፣ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው።

25ምክንያቱም ከሰው ጥበብ ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል፤ ከሰውም ብርታት ይልቅ የእግዚአብሔር ድካም ይበረታል።

26ወንድሞች ሆይ፤ በተጠራችሁ ጊዜ ምን እንደ ነበራችሁ እስቲ አስቡ። በሰው መስፈርት ከእናንተ ብዙዎቻችሁ ዐዋቂዎች አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ኀያላን አልነበራችሁም፤ ብዙዎቻችሁም ከትልቅ ቤተ ሰብ አልተ ወለዳችሁም።

27ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔር ብርቱዎችን ያሳፍር ዘንድ የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ።

28እግዚአብሔር የተከበረውን እንደሌለ ለማድረግ፣ በዚህ ዓለም ዝቅ ያለውንና የተናቀውን ነገር፣ ቦታም ያልተሰጠውን ነገር መረጠ፤

29ይኸውም ማንም ሰው በእርሱ ፊት እንዳይመካ ነው።

30በክርስቶስ ኢየሱስ ለመሆን የበቃችሁት ከእርሱ የተነሣ ነው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበባችን፣ ጽድቃችንና ቅድስናችን፣ ቤዛችንም ሆኖአል።

31እንግዲህ፣ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ “የሚመካ በጌታ ይመካ።”

ማብራሪያ

1:1-9 ሁሉም ክርስቲያኖች በጥምቀት ለክርስቶስ የተወሰኑና የተሰጡ ናቸው፤ ቅዱሳን ለመሆንም የጸኑ ግዴታዎች አለባቸው። ነገር ግን በእግዚአብሔር እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት በክርስቶስ ኢየሱስ የተቀደሱ፣ ቅዱሳን ለመሆን የተጠሩ፣ ሁሉንም የድነት በረከቶች ለማግኘት በሥጋ እንደተገለጠ አምላክ አድርገው በእርሱ ላይ የሚጠሩ፣ ጌታቸውና የሁሉ ጌታ አድርገው የሚያውቁትና የሚታዘዙት ናቸው፤ ከዚህ ውጭ ሌላ ሰው አያካትትም።

ክርስቲያኖች ከዓለማውያንና ከአምላክ የለሾች የሚለዩት ያለ ጸሎት ለመኖር የማይደፍሩ በመሆናቸው ነው። ከአይሁድና ከአረማውያን ደግሞ የሚለዩት በክርስቶስ ስም የሚጠሩ በመሆናቸው ነው። በእነዚህ ክፍሎች ሐዋርያው “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” የሚለውን ቃል ስንት ጊዜ እንደደጋገመ ልብ በሉ። እርሱን ደጋግሞ ለመጥቀስ ወይም ከመጠን ያለፈ ክብር ለመስጠት አልፈራም ነበር። ክርስቶስን ለሚጠሩ ሁሉ ሐዋርያው የተለመደውን ሰላምታ ሰጠ፤ ስለእነርሱም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔርን ይቅር ባይ ምሕረት፣ ቅድሳት ጸጋና የሚያጽናና ሰላም ተመኘ። ኃጢአተኞች ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ሊኖራቸው አይችልም፤ ከእርሱም ምንም ሰላም ሊያገኙ አይችሉም፤ በክርስቶስ ካልሆነ በስተቀር።

ወደ ክርስቶስ እምነት ስለተመለሱ እንዲሁም ጸጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ስለተሰጣቸው አመሰገነ። በእርሱ በሁሉም መንፈሳዊ ስጦታዎች ከብረው ነበር። ስለ መናገር ችሎታና ስለ እውቀት ይናገራል። እግዚአብሔር እነዚህን ሁለቱን ስጦታዎች በሰጠበት ቦታ፣ ለጥቅም ታላቅ ኃይል ሰጥቷል። እነዚህ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለሐዋርያት የመሰከረባቸው። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት የሚጠባበቁ በእርሱ እስከ መጨረሻው ይጠበቃሉ። እንደዚህ የሆኑትም በክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ ይሆናሉ፤ ይህንን ያገኙትም በታላቅና በነጻ ጸጋ ነው። የእንደዚህ አይነቱ መብት ተስፋ ምንኛ የከበረ ነው! በክርስቶስ ኃይል ከኃጢአት ዝንባሌዎቻችን ኃይልና ከሰይጣን ፈተናዎች መጠበቅ!

1:10-16 በሃይማኖት ታላላቅ ጉዳዮች ላይ አንድ ልብ ሁኑ፤ የአሳብ አንድነት ባይኖርም እንኳን የፍቅር አንድነት ይኑር። በትልልቅ ጉዳዮች ላይ የሚኖረው ስምምነት ስለ ትናንሾቹ ያሉትን ልዩነቶች ሊያስወግድ ይገባል። በሰማይ ፍጹም አንድነት ይኖራል፤ በምድርም ወደዚያ በምንቀርብበት መጠን ወደ ፍጽምና እንቀርባለን። ጳውሎስና አጵሎስ ሁለቱም የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ አገልጋዮች፣ የእምነታቸውና የደስታቸውም ረዳቶች ነበሩ፤ ነገር ግን ክርክር የሚወዱት ወደ ቡድኖች ተከፋፈሉ። እጅግ መልካም የሆኑት ነገሮች እንኳ ለመበላሸት ምንኛ ተጋላጭ ናቸው፤ ወንጌልና ተቋማቱም የልዩነትና የክርክር መሳሪያ ሆኑ። ሰይጣን በክርስቲያኖች መካከል ጠብን ለማስነሳት ሁልጊዜም ይጥራል፤ ይህም ወንጌልን ከሚቃወምባቸው ዋና ዋና ዘዴዎቹ አንዱ ነው። ሐዋርያው ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ፣ ይህም ይበልጥ ጠቃሚ ሥራ ስለሆነ፣ ማጥመቅን ለሌሎች አገልጋዮች ትቶ ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6