1ዳዊት ከቂስ ልጅ ከሳኦል ፊት ሸሽቶ በጺቅላግ ሳለ ወደ እርሱ የመጡት ሰዎች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም በጦርነቱ ላይ ከረዱት ተዋጊዎች መካከል ነበሩ።
2ሰዎቹ ቀስተኞች ሲሆኑ፣ በቀኝም ሆነ በግራ እጃቸው ፍላጻ መወርወርና ድንጋይ መወንጨፍ የሚችሉ ነበሩ፤ እነርሱም ከብንያም ነገድ የሆነው የሳኦል ሥጋ ዘመዶች ነበሩ፤
3አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፤ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ ነበረ፤ ሁለቱም የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች ነበሩ፤ የዓዝሞት ልጆች ይዝኤልና ፋሌጥ፤ በራኪያ፣ ዓናቶታዊው ኢዩ፤
4ገባዖናዊው ሰማያስ ከሠላሳዎቹ መካከል ኀያልና የሠላሳዎቹም መሪ ነበረ፤ ኤርምያስ፣ የሕዚኤል፣ ዮሐናን፣ ገድሮታዊው ዮዛባት፣
5ኤሉዛይ፣ ኢያሪሙት፣ በዓልያ፣ ሰማራያ፣ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፣
6ቆሬያውያኑ ሕልቃና፣ ይሺያ፣ ዓዘርኤል፣ ዮዛር፣ ያሾብዓም፤
7የጌዶር ሰው ከሆነው ደግሞ የይሮሐም ልጆች ዮዔላና ዝባድያ።
8ዳዊት በምድረ በዳ በሚገኘው ምሽጉ ውስጥ ሳለ፣ ከጋድ ነገድ የሆኑ ሰዎች መጥተው የእርሱን ሰራዊት ተቀላቀሉ፤ እነርሱም ለውጊያ የተዘጋጁ ጋሻና ጦር ለመያዝ የሚችሉ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ፤ ፊታቸው እንደ አንበሳ ፊት የሚያስፈራና በየተራራውም ላይ እንደሚዘል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ።
9የእነዚህም አለቃ ዔጼር ነበረ፤ ሁለተኛው አዛዥ አብድዩ፣ ሦስተኛው ኤልያብ፣
10አራተኛው መስመና፣ አምስተኛው ኤርምያስ፣
11ስድስተኛው ዓታይ፣ ሰባተኛው ኢሊኤል፣
12ስምንተኛው ዮሐናን፣ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፣
13ዐሥረኛው ኤርምያስ፣ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ።
14እነዚህ ጋዳውያን የጦር አዛዦች ነበሩ፣ ከእነርሱ ታናሽ የሆነው እንደ መቶ፣ ታላቅ የሆነው ደግሞ እንደ ሺህ አለቃ ይቈጠር ነበር።
15በመጀመሪያው ወር የዮርዳኖስ ወንዝ ከአፍ እስከ ገደፍ ሞልቶ ሳለ፣ ወንዙን ተሻግረው በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ሸለቆዎች ይኖሩ የነበሩትን ሁሉ ከዚያ ያባረሩት እነዚህ ሰዎች ነበሩ።
16ሌሎች ከብንያምና ከይሁዳም ወገን የሆኑ ሰዎች ዳዊት ወደሚገኝበት ምሽግ መጡ።
17ዳዊትም እነዚህን ሰዎች ሊቀበል ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ የመጣችሁት ልትረዱኝና በሰላም ከሆነ፣ ከእኔ ጋር እንድትሰለፉ ልቀበላችሁ ዝግጁ ነኝ፤ ነገር ግን እጄ ከበደል ንጹሕ ሆኖ ሳለ፣ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ፣ የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፤ ይፍረደውም”።
18ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በሠላሳዎቹ አለቃ በዓማሣይ ላይ ወረደ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “ዳዊት ሆይ፤ እኛ የአንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ፤ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ ሰላም ፍጹም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አንተን ለሚረዱም ሁሉ ሰላም ይሁን፤ አምላክህ ይረዳሃልና”። ስለዚህ ዳዊት ተቀበላቸው፤ የሰራዊቱም አለቃ አደረጋቸው።
19ዳዊት ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተባብሮ ሳኦልን ለመውጋት በሄደ ጊዜ፣ ከምናሴ ነገድ የሆኑ ጥቂት ሰዎች ከድተው ከዳዊት ሰራዊት ጋር ተቀላቀሉ። እርሱ ግን ርዳታ አላደረገላቸውም፤ ምክንያቱም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምክር ካደረጉ በኋላ እንዲህ ሲሉ ልከውት ነበር፤ “ከድቶ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ቢሄድ እኛን ያስጨርሰናል”።
20ዳዊት ወደ ጺቅላግ በሄደ ጊዜ ከድተው ወደ እርሱ የተቀላቀሉ የምናሴ ነገድ ሰዎች እነዚህ ነበሩ፤ ዓድና፣ ዮዛባት፣ ይዲኤል፣ ሚካኤል፣ ዮዛባት፣ ኤሊሁ፣ ጺልታይ፤ እነዚህ በምናሴ ግዛት ሳሉ የሻለቆች ነበሩ።
21ሁሉም ብርቱ ተዋጊዎችና በዳዊትም ሰራዊት ውስጥ አዛዦች ስለ ነበሩ፣ አደጋ ጣዮችን በመውጋት ረዱት።
22ሰራዊቱም እንደ እግዚአብሔር ሰራዊት እስኪሆን ድረስ፣ ዳዊትን ለመርዳት በየዕለቱ ብዙ ሰዎች ይጎርፉ ነበር።
23እግዚአብሔር ለዳዊት በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት የሳኦልን መንግሥት አንሥተው ለእርሱ ለመስጠት ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ ኬብሮን የመጡት ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤
24ጋሻና ጦር አንግበው ለጦርነት የተዘጋጁት የይሁዳ ሰዎች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ፤
25ከስምዖን ነገድ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ሰባት ሺህ አንድ መቶ።
26ከሌዊ ነገድ አራት ሺህ ስድስት መቶ፤
27የአሮን ቤተ ሰብ መሪ የሆነውን ዮዳሄን ጨምሮ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፤
28ወጣቱ ብርቱ ተዋጊ ጻዶቅና ከቤተ ሰቡ ሃያ ሁለት የጦር አለቆች፤
29የሳኦል ሥጋ ዘመድ የሆኑ የብንያም ሰዎች ሦስት ሺህ፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለሳኦል ቤት ታማኝ ነበሩ፤
30ከኤፍሬም ሰዎች በጐሣዎቻቸው ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ብርቱ ተዋጊዎች ሃያ ሺህ ስምንት መቶ፤
31ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች፤ እነርሱም ዳዊትን ለማንገሥ በየስማቸው ተጽፈው የመጡ ነበሩ።
32ዘመኑን የተረዱና እስራኤላውያንም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የተገነዘቡ የይሳኮር ሰዎች ሁለት መቶ አለቆች፤ በእነርሱም ሥር ሆነው የሚታዘዙ ዘመዶቻቸው።
33ልምድ ያላቸው፣ በሁሉም ዐይነት መሣሪያ ለመዋጋት የተዘጋጁና ዳዊትን ለመርዳት የመጡት መንታ ልብ የሌላቸው የዛብሎን ሰዎች ሃምሳ ሺህ፤
34ከንፍታሌም ሰዎች አንድ ሺህ የጦር አለቆች፤ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የያዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ሰዎች፤
35ከዳን ሰዎች ለጦርነት የተዘጋጁ ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ፤
36ከአሴር ሰዎች ልምድ ያላቸውና ለጦርነት የተዘጋጁ ወታደሮች አርባ ሺህ፤
37ከምሥራቅ ዮርዳኖስ ከሮቤል፣ ከጋድና ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ልዩ ልዩ ዐይነት መሣሪያ የታጠቁ አንድ መቶ ሃያ ሺህ ሰዎች።
38እነዚህ ሁሉ በሰራዊቱ ውስጥ ለማገልገል ፈቃደኞች የሆኑ ተዋጊዎች ናቸው፤ ወደ ኬብሮን የመጡትም ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ለማንገሥ ወስነው ስለ ነበር ነው። የቀሩትም እስራኤላውያን ሁሉ ዳዊትን ለማንገሥ በአንድ ሐሳብ ጸኑ።
39የሚያስፈልጋቸውንም ቤተ ሰቦቻቸው አዘጋጅተውላቸው ስለ ነበር፣ ሰዎቹ እየበሉና እየጠጡ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ቈዩ።
40እንዲሁም ሩቅ ከሆነው ከይሳኮር፣ ከዛብሎንና ከንፍታሌም አገር ሳይቀር ጎረቤቶቻቸው በአህያ፣ በግመል፣ በበቅሎና በበሬ ጭነው ምግብ አመጡላቸው፤ በእስራኤል ታላቅ ደስታ ስለ ሆነ ዱቄት፣ የበለስና የዘቢብ ጥፍጥፍ፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የቀንድ ከብትና በጎች በገፍ ቀርበው ነበር።