ገብርኤል ዘካርያስን ጎበኘ
23 ቁጥሮች2አማርኛሉቃ 1:11-20
11የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው።
12ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት።
13መልአኩም እንዲህ አለው፦ “ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፡ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።
14ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።
15በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤
16“ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል።
17እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።”
18ዘካርያስም መልአኩን፦ “እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?” አለው።
19መልአኩም መልሶ፦ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤
20እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም፡” አለው።
ሉቃ 1:26-38
26በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ፥
27ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።
28መልአኩም ወደ እርስዋ ገብቶ፦ “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ” አላት።
29እርስዋም ባየችው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና፦ “ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው?” ብላ አሰበች።
30መልአኩም እንዲህ አላት፦ “ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።
31እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ።
32እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤
33በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”
34ማርያምም መልአኩን፦ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” አለችው።
35መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።
36እነሆም ዘመድሽ ኤልሳቤጥ፥ እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች፥ ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው፤
37ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና።”
38ማርያምም፦ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” አለች። መልአኩም ከእርስዋ ሄደ።