ሐቀኛ መጋቢ
26 ቁጥሮች2አማርኛሉቃ 16:1-13
1ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ “መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ በእርሱ ዘንድ፦ ‘ይህ ሰው ያለህን ይበትናል፡’ ብለው ከሰሱት።
2ጠርቶም፦ ‘ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ’ አለው።
3“መጋቢውም በልቡ፦ ‘ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፥ መለመንም አፍራለሁ።
4ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ፡’ አለ።
5“የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የፊተኛውን፦ ‘ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ?’ አለው።
6እርሱም፦ ‘መቶ ማድጋ ዘይት’ አለ። ‘ደብዳቤህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ አምሳ ብለህ ጻፍ’ አለው።
7በኋላም ሌላውን፦ ‘አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ?’ አለው። እርሱም፦ ‘መቶ ጫን ስንዴ’ አለ። ‘ደብዳቤህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ’ አለው።
8“ጌታውም ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና።
9እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ።
10ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው።
11“እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል?
12በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል?
13“ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።”
ሉቃ 16:19-31
19“ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር።
20አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥
21ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር።
22ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ።
23“በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ፡ አልዓዛርንም በእቅፉ።
24እርሱም እየጮኸ፦ ‘አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ፡’ አለ።
25አብርሃም ግን፦ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ።
26ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል፡’ አለ።
27“እርሱም፦ ‘እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤
28እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው፡’ አለ።
29አብርሃም ግን፦ ‘ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ’ አለው።
30“እርሱም፦ ‘አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ’ አለ።
31‘ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም፡’ አለው።”