ቃየንና አቤል

16 ቁጥሮችአማርኛ

ዘፍ 4:1-16

1አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም፦ “ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ፡” አለች።

2ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ።

3ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤

4አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኵራትና ከስቡ አቀረበ። እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤

5ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም። ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ።

6እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፦ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ?

7መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢአት በደጅ ታደባለች፤ ፈቃድዋም ወደ አንተ ነው፥ አንተ ግን በእርስዋ ንገሥባት።”

8ቃየንም ወንድሙን አቤልን፦ “ና ወደ ሜዳ እንሂድ፡” አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም።

9እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፦ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው?” እርሱም አለ፦ “አላውቅም፤ የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን?”

10አለውም፦ “ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል።

11አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።

12ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኃይልዋን አትሰጥህም፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።”

13ቃየንም እግዚአብሔርን አለው፦ “ኃጢአቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት።

14እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ፤ ከፊትህም እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኰብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።”

15እግዚአብሔርም እርሱን አለው፦ “እንግዲህ ቃየንን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል።” እግዚአብሔርም ቃየንን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት።

16ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።