ሩትና ቦዔዝ
57 ቁጥሮች3አማርኛሩት 2:1-22
1ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ።
2ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን፦ “በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ፡” አለቻት። እርስዋም፦ “ልጄ ሆይ፥ ሂጂ፡” አለቻት።
3ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች።
4እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፡” አላቸው። እነርሱም፦ “እግዚአብሔር ይባርክህ፡” ብለው መለሱለት።
5ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን፦ “ይህች ቆንጆ የማን ናት?” አለው።
6የአጫጆቹም አዛዥ፦ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤
7እርስዋም፦ ‘ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ፡’ አለች፤ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም፡” አለው።
8ቦዔዝም ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ።
9ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ፡” አላት።
10በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት፦ “እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን?” አለችው።
11ቦዔዝም፦ “ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ።
12እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን፡” አላት።
13እርስዋም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ፡” አለችው።
14በምሳም ጊዜ ቦዔዝ፦ “ወደዚህ ቅረቢ፤ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ፡” አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ አተረፈችም።
15ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን፦ “በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አታሳፍሩአት፤
16ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፤ እርስዋም ትቃርም፥ አትውቀሱአትም፡” ብሎ አዘዛቸው።
17በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፤ የቃረመችውንም ወቃችው፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ።
18ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፤ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት።
19አማትዋም፦ “ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን፡” አለቻት። እርስዋም፦ “ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል፡” ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት።
20ኑኃሚንም ምራትዋን፦ “ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፡” አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ፦ “ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው፡” አለቻት።
21ሞዓባዊቱ ሩትም፦ “ደግሞ፦ ‘መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ፡’ አለኝ፡” አለቻት።
22ኑኃሚንም ምራትዋን ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ከገረዶቹ ጋር ብትወጪ፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው፡” አለቻት።
ሩት 3:1-18
1አማትዋም ኑኃሚን አለቻት፦ “ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን?
2አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል።
3“እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው።
4በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል።”
5ሩትም፦ “የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡ አለቻት።
6ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች።
7ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች።
8መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች።
9እርሱም፦ “ማን ነሽ?” አለ። እርስዋም፦ “እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ፡” አለችው።
10ቦዔዝም አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል።
11አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።
12“የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ።
13ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ።”
14እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም፦ “ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ፡” ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች።
15እርሱም፦ “የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው፡” አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት፡ አሸከማትም። እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ።
16ወደ አማትዋም መጣች፥ አማትዋም፦ “ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ?” አለቻት፤ እርስዋም ሰውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት።
17ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ አለቻት።
18እርስዋም፦ “ልጄ ሆይ፥ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ፡” አለች።
ሩት 4:1-17
1ቦዔዝም ወደ ከተማይቱ በር አደባባይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። እነሆም፥ ቦዔዝ ስለ እርሱ ይናገር የነበረው የቅርብ ዘመድ ሲያልፍ ቦዔዝ፦ “አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ፡” አለው። እርሱም ቀረብ ብሎ ተቀመጠ።
2ቦዔዝም ከከተማይቱ ሽማግሌዎች አሥር ሰዎች ጠርቶ፦ “በዚህ ተቀመጡ፡” አላቸው። እነርሱም ተቀመጡ።
3ቦዔዝም የቅርብ ዘመዱን፦ “ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ኑኃሚን የወንድማችንን የአቤሜሌክን ጢንጦ ትሸጣለች።
4እኔም በዚህ በተቀመጡት በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት እንድትገዛው አስታውቅህ ዘንድ አሰብሁ። መቤዠት ብትወድድ ተቤዠው፤ መቤዠት ባትወድድ ግን ከአንተ በቀር ሌላ ወራሽ የለምና፥ እኔም ከእአንተ በኋላ ነኝና እንዳውቀው ንገረኝ፡” አለው። እርሱም፦ “እቤዠዋለሁ፡” አለው።
5ቦዔዝም፦ “እርሻውን ከኑኃሚን እጅ በምትገዛበት ቀን፥ ለሞተው በርስቱ ስሙን እንድታስነሣለት ከምዋቹ ሚስት ከሞዓባዊቱ ከሩት ደግሞ ትገዛለህ፡” አለ።
6የቅርብ ዘመዱም፦ “የራሴን ርስት እንዳላበላሽ መቤዠት አልችልም፤ እኔ መቤዠቱን አልችልምና አንተ ከእኔ መቤዠቱን ውሰደው፡” አለ።
7በጥንት ጊዜም፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ። ይህም በእስራኤል ምስክር ነበረ።
8የቅርብ ዘመዱም ቦዔዝን፦ “አንተ ግዛው፡” አለው፤ ጫማውንም አወለቀ።
9ቦዔዝም ሽማግሌዎችንና ሕዝቡን ሁሉ፦ “ለአቤሜሌክና ለኬሌዎን ለመሐሎንም የነበረውን ሁሉ ከኑኃሚን እጅ እንደ ገዛሁ እናንተ ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።
10ደግሞም የምዋቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል ከአገሩም ደጅ እንዳይጠፋ፥ የምዋቹን ስም በርስቱ ላይ እንዳስነሣ የመሐሎንን ሚስት ሞዓባዊቱን ሩትን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወሰድሁአት፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ፡” አላቸው።
11በከተማይቱ በር አደባባይም የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ሽማግሌዎቹም፦ “እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ ባለ ጠጋ ሁን፥ ስምህም በቤተ ልሔም ይጠራ።
12ቤትህም እግዚአብሔር ከዚህች ቈንጆ ከሚሰጥህ ዘር ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤት ይሁን፡” አሉት።
13ቦዔዝም ሩትን ወሰደ፥ ሚስትም ሆነችው፤ ደረሰባትም፥ እግዚአብሔርም ፅንስ ሰጣት፥ ወንድ ልጅም ወለደች።
14ሴቶችም ኑኃሚንን፦ “ዛሬ ዋርሳ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ ስሙም በእስራኤል ይጠራ።
15ከሰባትም ወንዶች ልጆች ይልቅ ለአንቺ ከምትሻል ከምትወድድሽ ምራት ተወልዶአልና ሰውነትሽን ያሳድሰዋል፥ በእርጅናሽም ይመግብሻል፡” አሉአት።
16ኑኃሚንም ሕፃኑን ወሰደች አቀፈችውም፥ ሞግዚትም ሆነችው።
17ሴቶችም ጎረቤቶችዋ፥ ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት እያሉ ስም አወጡለት፤ ስሙንም፡ ኢዮቤድ፡ ብለው ጠሩት። እርሱም የዳዊት አባት የእሴይ አባት ነው።