ለቄሳር ይክፈሉ።

12 ቁጥሮች2አማርኛ

ማር 12:13-17

13በንግግርም ሊያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን የሆኑትን ወደ እርሱ ላኩ።

14መጥተውም፦ “መምህር ሆይ፥ የሰውን ፊት ሳትመለከት በእውነት የእግዚአብሔር መንገድ ታስተምራለህና እውነተኛ እንደ ሆንህ ለማንምም እንዳታደላ እናውቃለን፤ ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? እንስጥን ወይስ አንስጥ?” አሉት።

15እርሱ ግን ግብዝነታቸውን አውቆ፦ “ለምን ትፈትኑኛላችሁ? አየው ዘንድ አንድ ዲናር አምጡልኝ፡” አላቸው።

16እነርሱም አመጡለት። “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው፤” እነርሱም፦ “የቄሣር ናት፡” አሉት።

17ኢየሱስም መልሶ፦ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” አላቸው። በእርሱም ተደነቁ።

ማር 12:28-34

28ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ “ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው።

29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ ‘እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥

30አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፡’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

31ሁለተኛይቱም፦ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፡’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።”

32ጻፊውም፦ “መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤

33በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ፡ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው፡” አለው።

34ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ፦ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።