1እንደ ገናም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ እነሆ አራት ሠረገሎች ከሁለት ተራራ መካከል ሲወጡ አየሁ፤ ተራሮቹም የናስ ተራሮች ነበሩ።
2የመጀመሪያው ሠረገላ መጋላ፣ ሁለተኛው ዱሪ፤
3ሦስተኛው አምባላይ፤ አራተኛውም ዥጒርጒር ፈረሶች ነበሯቸው፤ ሁሉም ጠንካሮች ነበሩ።
4እኔም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውን መልአክ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት።
5መልአኩም እንዲህ አለኝ፤ “እነዚህ አራቱ ቆመው ከነበሩበት ከምድር ሁሉ ጌታ ፊት የወጡ የሰማይ መናፍስት ናቸው።
6የባለ ዱሪ ፈረሶች ወደ ሰሜን፤ የባለ አምባላይ ፈረሶች ወደ ምዕራብ አገር፣ የባለ ዥንጒርጒር ፈረሶች ወደ ደቡብ አገር ይወጣል።”
7ጠንካሮቹ ፈረሶች ሲወጡ፣ በምድር ሁሉ ለመመላለስ አቈብቍበው ነበር። እርሱም፣ “ወደ ምድር ሁሉ ሂዱ” አላቸው፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ሄዱ።
8ከዚያም ጮኾ እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ወደ ሰሜን አገር የሚወጡት፣ መንፈሴን በሰሜን ምድር አሳርፈውታል።”
9የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
10“ከባቢሎን ከመጡት ምርኮኞች ከሔልዳይና ከጦብያ ከዮዳኤም ወርቅና ብር ውሰድ፤ በዚያው ቀን ወደ ሶፎንያስ ልጅ ወደ ኢዮስያስ ቤት ሂድ።
11ወርቁንና ብሩን ወስደህ አክሊል ሥራ፤ በኢዮሴዴቅ ልጅ በሊቀ ካህኑ በኢያሱ ራስ ላይም አድርገው፤
12ለእርሱም እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል ብለህ ንገረው፤ ‘እነሆ፤ ስሙ ቅርንጫፍ የተባለው ሰው ይህ ነው፤ እርሱም በቦታው ይንሰራፋል፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ይሠራል።
13የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሚሠራው እርሱ ነው፤ ክብርን ይጐናጸፋል፤ በዙፋኑ ተቀምጦ ይገዛል፤ በዙፋኑም ላይ ካህን ይሆናል፤ በሁለቱም መካከል ስምምነት ይኖራል።
14አክሊሉም ለሔሌምና ለጦብያ፣ ለዮዳኤና ለሶፎንያስ ልጅ ለሔን በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መታሰቢያ ይሆናል።
15እነዚያ በሩቅ ያሉት መጥተው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲሠራ ያግዛሉ፤ እናንተም እግዚአብሔር ጸባኦት እንደ ላከኝ ታውቃላችሁ። ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በጥንቃቄ ብትታዘዙ ይህ ይሆናል።”