ትንቢተ ዘካርያስ 14

AMHNIVአማርኛ21 ጥቅሶች4:42 አዳምጥ
አዳምጥ 4:42 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እነሆ፤ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፤ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ።

2ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ አሕዛብን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከተማዪቱ ትያዛለች፤ ቤቶች ይበዘበዛሉ፤ ሴቶችም ይደፈራሉ፤ የከተማዪቱ እኩሌታ ይማረካል፤ የሚቀረው ሕዝብ ግን ከከተማዪቱ አይወሰድም።

3እግዚአብሔርም በጦርነት ጊዜ እንደሚዋጋ፣ እነዚያን አሕዛብ ሊወጋ ይወጣል።

4በዚያን ቀን እግሮቹ ከኢየሩሳሌም በስተ ምሥራቅ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይቆማሉ፤ የደብረ ዘይት ተራራም ታላቅ ሸለቆን በመሥራት የተራራውን እኩሌታ ወደ ሰሜን፣ እኩሌታውንም ወደ ደቡብ በማድረግ ምሥራቅና ምዕራብ ሆኖ ለሁለት ይከፈላል፤

5እናንተም በእግዚአብሔር ተራራ ሸለቆ በኩል በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን በምድር ትሸሻላችሁ፤ ሸለቆው እስከ አጸል ይደርሳልና። በምድር መናወጥ ምክንያት ሸሽታችሁ እንደ ነበረ ትሸሻላችሁ፤ ከዚያም አምላኬ እግዚአብሔር ይመጣል፤ ቅሆሳኑም ሁሉ አብረውት ይመጣሉ።

6በዚያ ቀን በረዶ ውርጭና ብርሃን አይኖርም።

7ቀኑም የብርሃን ወይም የጨለማ ጊዜ የሌለበት ልዩ ቀን ይሆናል፤ ያም ቀን በእግዚአብሔር የታወቀ ቀን ይሆናል፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።

8በዚያን ቀን የሕይወት ውሃ ከኢየሩሳሌም ይፈልቃል፤ እኩሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ እኩሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይፈሳል፤ ይህም በበጋና በክረምት ይሆናል።

9እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር አንድ፣ ስሙም አንድ ብቻ ይሆናል።

10ምድር ሁሉ ከጌባ አንሥቶ በኢየሩሳሌም ደቡብ እስካለችው ሬሞን ድረስ ተለውጣ ደልዳላ ሜዳ ትሆናለች፤ ኢየሩሳሌም ግን ከብንያም በር እስከ መጀመሪያው በር፣ ከማእዘን በርና ከሐናንኤል ግንብ እስከ ንጉሡ የወይን ጠጅ መጥመቂያ ድረስ በዚያው በቦታዋ ላይ ከፍ እንዳለች ትኖራለች።

11የሰው መኖሪያም ትሆናለች፤ ከቶም ዳግመኛ አትፈርስም፤ ኢየሩሳሌም ያለ ሥጋት በሰላም ትኖራለች።

12እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን የወጓትን አሕዛብ ሁሉ የሚመታበት መቅሠፍት ይህ ነው፤ ገና በእግራቸው ቆመው ሳሉ ሥጋቸው ይበሰብሳል፤ ዐይኖቻቸው በጒድጓዶቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ፤ ምላሶቻቸውም በአፎቻቸው ውስጥ እንዳሉ ይበሰብሳሉ።

13በዚያ ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በሰዎች ላይ ታላቅ ሽብር ይወርዳል፤ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፤ አንዱም ሌላውን ይወጋዋል።

14ይሁዳም ደግሞ ኢየሩሳሌምን ይወጋል። በዙሪያው ያሉ የአሕዛብ ሁሉ ሀብት፣ ብዙ ወርቅ፣ ብርና ልብስ ይሰበሰባል።

15ይህንኑ የሚመስል መቅሠፍት ፈረሶችን፣ በቅሎዎችን ግመሎችንና አህዮችን እንዲሁም በየሰፈሩ ያሉትን እንስሶች ሁሉ ይመታል።

16ከዚያም ኢየሩሳሌምን ከወጓት አሕዛብ ከሞት የተረፉት ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ለመስገድና የዳስን በዓል ለማክበር በየዓመቱ ይወጣሉ።

17የምድር ሕዝብ ሁሉ ለንጉሡ፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ሊሰግዱ ወደ ኢየሩሳሌም የማይወጡ ከሆነ ዝናብ አያገኙም።

18የግብፅም ሰዎች ወደዚያ ሳይወጡ ቢቀሩ፣ ዝናብ አያገኙም፤ እግዚአብሔር ወጥተው የዳስ በዓልን በማያከብሩ አሕዛብ ላይ የሚያደርሰውን መቅሠፍት በእነርሱም ላይ ያመጣል።

19የዳስን በዓል ወጥተው ለማያከብሩ ግብፃውያንና አሕዛብ ሁሉ የተወሰነው ቅጣት ይህ ነው።

20በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር” የሚል ጽሑፍ ይቀረጻል፤ በእግዚአብሔር ቤት ያሉ የማብሰያ ምንቸቶች ከመሠዊያው ፊት ለፊት እንዳሉ ሳሕኖች የተቀደሱ ይሆናሉ።

21በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ጸባኦት የተቀደሱ ይሆናሉ፤ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡ ሁሉ ምንቸቶቹን በመውሰድ ያበስሉባቸዋል፤ በዚያን ቀን በእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት ከእንግዲህ ወዲያ ከነዓናዊ አይገኝም።

ማብራሪያ

፲፬፡፩-፯

ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ በተደጋጋሚ በደብረ ዘይት ላይ ይቆም ነበር። ከዚያም ወደ ሰማይ ዐረገ፥ ከዚህም በኋላ በይሁዳ ሕዝብ ላይ ጥፋቶችና መከራዎች መጡ። ይህ ምሳሌያዊ አተረጓጎም ቢሆንም፤ ብዙዎች ግን ገና ያልተፈጸሙ ክስተቶች ማስታወቂያ እንደሆነ፣ እንዲሁም አሁን ሙሉ ግንዛቤ ሊኖረን ከማይችል ችግሮች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ። እያንዳንዱ አማኝ፣ እግዚአብሔር አምላኩ እንደመሆኑ ከእርሱ ጋር ዝምድና ስላለው፣ ክርስቶስ በኃይል እንደሚመጣ በመጠበቅ ሊደሰትና በደስታ ሊናገር ይችላል። ለረጅም ጊዜ የቤተክርስቲያን ሁኔታ በኃጢአት ይበላሻል፤ የእውነትና የስህተት፣ የደስታና የመከራ ቅልቅል ይኖራል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ልምድ እንዲህ ነው፤ የጸጋና የብልሹነት የተቀላቀለበት ሁኔታ። ነገር ግን፣ ጊዜው እጅግ የከፋና ተስፋ የሌለው በሚሆንበት ጊዜ፣ ጌታ ጨለማን ወደ ብርሃን ይለውጣል፤ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተስፋ ቆርጦ መጠበቁን ሲያቆም መዳን ይመጣል።

፲፬፡፰-፲፭ አንዳንዶች እንደሚመለከቱት፣ ከኢየሩሳሌም የጀመረው የወንጌል መስፋፋት ከዚያች ከተማ በሚፈሱት የሕይወት ውኃዎች የተገለጸ ነው። የወንጌልም ሆነ የጸጋ መንገዶች፣ እንዲሁም በእነዚያ መንገዶች በአማኞች ልብ ውስጥ በመንፈስ የሚሠራው ጸጋ፣ በስደት ትኩሳትም ሆነ በፈተና ማዕበል፣ ወይም በሌላ በማንኛውም መከራ ነፋሳት ምክንያት ፈጽሞ አይጠፉም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6