1ምነው አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ፣ እንደ ወንድሜ በሆንህ! ከዚያም ውጭ ባገኝህ፣ እስምህ ነበር፤ ታዲያ ማንም ባልናቀኝ!
2እኔም ወደ አስተማረችኝ፣ ወደ እናቴም ቤት፣ እጅህን ይዤ በወሰድሁህ ነበር፤ የምትጠጣውን ጣፋጭ የወይን ጠጅ፣ የሮማኔን ጭማቂም በሰጠሁህ።
3ግራ እጁን ተንተርሻለሁ፤ ቀኝ እጁም ዐቅፎኛል።
4እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፤ ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት እማጠናችኋለሁ።
5ውዷን ተደግፋ፣ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኰይ ዛፍ ሥር አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ፀነሰችህ፤ በዚያም ታምጥ የነበረችው አንተን ወለደችህ።
6በልብህ እንዳለ፣ በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች፣ ቅናቷም እንደ መቃብር ጨካኝ ናትና፤ እንደሚንቦገቦግ እሳት፣ እንደ ኀይለኛም ነበልባል ትነዳለች።
7የውሃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፣ ፈሳሾችም አያሰጥሟትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይናቃል።
8ትንሽ እኅት አለችን፤ ጡትም ገና አላወጣችም፤ ስለ እርሷ በምንጠየቅበት ቀን ምን ማድረግ እንችል ይሆን?
9እርሷ ቅጥር ብትሆን፣ በላይዋ የብር መጠበቂያ ማማ እንሠራባታለን፤ በር ብትሆን፣ በዝግባ ዕንጨት እንከልላታለን።
10እነሆ እኔ ቅጥር ነኝ፤ ጡቶቼም እንደ ማማ ግንቦች ናቸው፤ እኔም በዐይኖቹ ፊት፣ ሰላምን እንደሚያመጣ ሰው ሆንሁ።
11ሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ተክል ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ተክል ቦታም ለአትክልተኞች አከራየው፤ እያንዳንዳቸውም የፍሬውን ዋጋ፣ አንድ አንድ ሺህ ሰቅል ብር ያመጡለት ነበር።
12የወይኔ ተክል ቦታ የራሴ፣ የግሌ ነው፤ ሰሎሞን ሆይ፤ አንድ ሺሁ ሰቅል ለአንተ፤ ፍሬውን ለሚጠብቁ ደግም ሁለት መቶ ይሁን።
13አንቺ በአትክልቱ ቦታ የምትኖሪ ሆይ፤ ባልንጀሮቼ ድምፅሽን ይሰማሉ፤ እስቲ እኔም ልስማው።
14ውዴ ሆይ፤ ቶሎ ናልኝ፤ ሚዳቋን፣ ወይም በቅመም ተራራ ላይ የሚዘል፣ የዋልያን ግልገል ምሰል።