ወደ ሮሜ 15

AMHNIVአማርኛ33 ጥቅሶች5:38 አዳምጥ
አዳምጥ 5:38 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እኛ ብርቱዎች የሆን፣ የደካሞችን ጒድለት መሸከም እንጂ ራሳችንን ማስደሰት የለብንም።

2እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን ለማነጽ፣ እርሱንም ለመጥቀም ደስ የሚያሰኘውን ነገር ማድረግ ይገባናል፤

3ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘምና፤ ነገር ግን፣ “አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ደረሰብኝ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሆነበት።

4በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።

5ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ የአንድነትን መንፈስ ይስጣችሁ፤

6ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።

7እንግዲህ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሆን ዘንድ ክርስቶስ እንደተቀበላችሁ፣ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ።

8ለአባቶች የተሰጠውን የተስፋ ቃል ያጸና ዘንድ ለእግዚአብሔር እውነት ሲል ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ እንደሆነ እነግራችኋለሁና፤

9እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ።”

10ደግሞም፣ “አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።

11እንደ ገናም፣ “አሕዛብም ሁላችሁ ጌታን አመስግኑ፤ ሕዝቦች ሁሉ ወድሱት” ይላል።

12ኢሳይያስም እንዲሁ፣ “በሕዝቦች ሁሉ ላይ የሚነግሠው፣ የእሴይ ሥር ይመጣል፤ በእርሱም አሕዛብ ተስፋ ያደርጋሉ” ይላል።

13በእርሱ በመታመናችሁ የተስፋ አምላክ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ፤ ይኸውም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተስፋ ተትረፍርፎ እንዲፈስላችሁ ነው።

14ወንድሞቼ ሆይ፤ እናንተ ራሳችሁ በበጎነት የተሞላችሁ፣ በዕውቀት ሁሉ እንደ ተሞላችሁና አንዱ ሌላውን ለመምከር ችሎታ ያላችሁ መሆናችሁን እኔ ራሴ ርግጠኛ ሆኜ አለሁ።

15እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት፣ እንደ ገና ዐሳስባችሁ ዘንድ በአንዳንድ ጒዳዮች ላይ በድፍረት የጻፍሁላችሁ፣

16በእግዚአብሔር ወንጌል የክህነት ተግባር፣ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ለመሆን ነው፤ ይኸውም አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት እንዲሆኑ ነው።

17ስለዚህ እግዚአብሔርን በማገልገሌ በክርስቶስ ኢየሱስ እመካለሁ።

18በተናገርሁትና በአደረግሁት ነገር አሕዛብ ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ፣ ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም፤

19ይህም የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በምልክቶችና በታምራት ነበር። በዚህም ሁኔታ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ዙሪያ ድረስ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ ሰብኬአለሁ።

20ሌላው በጣለው መሠረት ላይ እንዳልገነባ ብዬ፣ ክርስቶስ ባልተጠራበት ስፍራ ወንጌልን መስበክ የዘወትር ምኞቴ ነበር።

21ይልቁንም፣ “ስለ እርሱ ያልተነገራቸው ያያሉ፤ ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

22በዚህም ምክንያት ወደ እናንተ እንዳልመጣ ብዙ ጊዜ ተከለከልሁ።

23አሁን ግን በእነዚህ አካባቢዎች የምሠራው ስለሌለ፣ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ እናንተን ለማየት እናፍቅም ስለ ነበር፣

24ይህን ዕቅድ ወደ እስጳንያ በምሄድበት ጊዜ ልፈጽመው አስባለሁ። በማልፍበትም ጊዜ ልጐበኛችሁና ከእናንተ ጋር ለጥቂት ጊዜ ቈይቼ ናፍቆቴን ከተወጣሁ በኋላ በጒዞዬ እንደምትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

25አሁን ግን በዚያ የሚገኙትን ቅዱሳን ለማገልገል ወደ ኢየሩሳሌም በመጓዝ ላይ ነኝ።

26ምክንያቱም መቄዶንያና አካይያ፣ በኢየሩሳሌም ካሉት ቅዱሳን መካከል የሚገኙትን ድኾች ለመርዳት ተነሣሥተዋልና።

27ርዳታ ለማድረግ ወደዋል፤ በርግጥም ባለዕዳዎቻቸው ናቸው። አሕዛብ የአይሁድ መንፈሳዊ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ፣ ያገኙትን ምድራዊ በረከት ከአይሁድ ጋር ይካፈሉ ዘንድ የእነርሱ ባለዕዳዎች ናቸው።

28ስለዚህ ሥራውን ከጨረስሁና ይህን ፍሬ መቀበላቸውን ካረጋገጥሁ በኋላ ወደ እስጳንያ እሄዳለሁ፤ እግረ መንገዴንም እናንተን አያለሁ።

29ወደ እናንተም ስመጣ፣ በክርስቶስ በረከት ሙላት እንደምመጣ ዐውቃለሁ።

30ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ የተጋድሎዬ አጋር እንድትሆኑ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ።

31በይሁዳ ካሉት ከማያምኑት እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ያለው አገልግሎቴም በዚያ ባሉት ቅዱሳን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ጸልዩልኝ፤

32ይኸውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደ እናንተ በደስታ እንድመጣና ከእናንተም ጋር እንድታደስ ነው።

33የሰላም አምላክ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።

ማብራሪያ

ሮሜ 15:1-7 ክርስትያናዊ ነጻነት የተፈቀደው ለራሳችን ደስታ ሳይሆን፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሌሎች ጥቅም ነው። ባልንጀራችንን ማስደሰት ይገባናል፤ ይህንንም የምናደርገው ለነፍሱ ጥቅም ሲባል ነው፤ ክፉ ፈቃዱን በማገልገልና በኃጢአት መንገድ በማስደሰት አይደለም። በዚህ መንገድ ሰዎችን ለማስደሰት ከፈለግን የክርስቶስ ባሪያዎች አይደለንም። የክርስቶስ መላው ሕይወት ራሱን የሚክድና ራሱን የማያስደስት ሕይወት ነበር። በክርስቶስ እጅግ የተመሰለ እርሱ እጅግ የላቀ ክርስቲያን ነው። ነውር የሌለበትን ንጽህናውንና ቅድስናውን ስናስብ፣ ስለ እኛ ኃጢአትና እርግማን ከመሆን፣ የእግዚአብሔርም ነቀፋዎች በእርሱ ላይ ከመውደቅ በቀር ከዚህ የበለጠ ለእርሱ ተቃራኒ የሚሆን ምንም ነገር የለም፤ ጻድቁ ስለ ዓመፀኞች። እርሱ የኃጢአትን በደልና እርግማኑን ተሸከመ፤ እኛ ግን ጥቂት ችግሩን እንድንሸከም ብቻ ነው የተጠራነው። እርሱ የትዕቢተኞችን ኃጢአት ተሸከመ፤ እኛ ግን የደካሞችን ጉድለቶች እንድንሸከም ብቻ ነው የተጠራነው። እርስ በርሳችን የአንድ አካል ብልቶች የሆንን እኛ፣ እንግዲህ ትሑቶች፣ ራሳችንን የምንክድና እርስ በርሳችን ለመተያየት ዝግጁዎች መሆን የለብንምን? ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት ለእኛ ጥቅም ሲባልና እንድንጠቀምባቸው ነው፤ በመጀመሪያ እንደተሰጡዋቸው ሰዎች ሁሉ ለእኛም ጭምር ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት እጅግ ብርቱዎች የሆኑት እነርሱ እጅግ የተማሩት ናቸው። ከእግዚአብሔር ቃል የሚመጣው መጽናናት እጅግ እርግጠኛና እጅግ ጣፋጭ ነው፤ ተስፋን ለመያዝም ትልቁ ድጋፍ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንደ አጽናኝ የርስታችን መያዣ ነው። ይህ አንድ አሳብ መሆን በክርስቶስ ትዕዛዝ፣ እንደ እርሱ ምሳሌና አርአያ መሆን አለበት። ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፤ እጅግም ውድ ስጦታ ነውና፣ ስለዚህም በእርሱ ዘንድ አጥብቀን መለመን አለብን። መለኮታዊው ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ይጋብዛል፤ ራሱንም በነፍሱ የዋህና ትሑት አድርጎ በማሳየት ያበረታታቸዋል። ተመሳሳይ ዝንባሌ የባሪያዎቹን ምግባር መገለጫ መሆን አለበት፤ በተለይም የብርቱዎች ለደካሞች ያላቸው ምግባር። በሁሉም ተግባራችን ውስጥ ታላቁ ዓላማ እግዚአብሔር እንዲከብር መሆን አለበት፤ ሃይማኖትን ከሚመሰክሩት ሰዎች የጋራ ፍቅርና ደግነት የበለጠ ይህንን የሚያራምድ ምንም ነገር የለም። በክርስቶስ የተስማሙት በመካከላቸውም ሊስማሙ ይችላሉ።

15:8-13 ክርስቶስ ስለ አይሁድ የተነገሩትን ትንቢቶችና የተሰጡትን ተስፋዎች ፈጸመ፤ አሕዛብ የሆኑት አማኞችም እነርሱን ለመናቅ ምንም ምክንያት ሊኖራቸው አይገባም። አሕዛብ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ፣ በትዕግስትና በመከራ አብረው ተካፋዮች ናቸው። እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባቸዋል። ሁሉንም አሕዛብ ጌታን እንዲያመሰግኑ መጥራት፣ ስለ እርሱ እውቀት እንደሚኖራቸው ያሳያል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6