1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጣልኸን፤ አንኰታኰትኸን፤ ተቈጣኸንም፤ አሁን ግን መልሰህ አብጀን።
2ምድሪቱን አናወጥሃት፤ ፍርክስክስ አደረግሃት፤ ትንገዳገዳለችና ስብራቷን ጠግን።
3ለሕዝብህ አበሳውን አሳየኸው፤ ናላ የሚያዞር የወይን ጠጅ እንድንጠጣም ሰጠኸን።
4ነገር ግን ከቀስት እንዲያመልጡ፣ ለሚፈሩህ ምልክት አቆምህላቸው። ሴላ
5ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፣ በቀኝ እጅህ ርዳን፤ መልስም ስጠን።
6እግዚአብሔር ከመቅደሱ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ደስ እያለኝ የሴኬምን ምድር እሸነሽናለሁ፤ የሱኮትን ሸለቆ አከፋፍላለሁ።
7ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራስ ቍሬ ነው፤ ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው።
8ሞዓብ የመታጠቢያ ገንዳዬ ነው፤ በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤ በፍልስጥኤም ላይ በድል እልል እላለሁ።”
9ወደ ተመሸገው ከተማ ማን ያመጣኛል? ማንስ ወደ ኤዶምያስ ይመራኛል?
10አምላክ ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰራዊታችን ጋር እኮ አልወጣ አልህ!
11በጠላት ላይ ድልን አቀዳጀን፤ የሰው ርዳታ ከንቱ ነውና።
12በእግዚአብሔር ክንደ ብርቱ እንሆናለን፤ ጠላቶቻችንን የሚረጋግጥልን እርሱ ነውና።